ኢሳት ( ግንቦት 1 ፥ 2008)
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከሶስት ሳምንት በፊት በጋምቤላ የተጠለፉትን ህጻናትን ለማስመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ወደ አገሪቷ ገብቷል በሚል የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ያቀረቡትን ዘገባ የተዛባ ወሬ ነው ሲል አስተባበለ።
የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ሰራዊት
(SPLA) ቃል አቀባይ የሆኑን ብርጋዴር ሉል ሩዋይ ኮዓንግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ጦር በደቡብ ሱዳን ገብቷል የሚለው የተዛባ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ፕሮፓጋንዳ ፍጹም ውሸት እንደሆነ ተናግረዋል።
ትክክለኛው ዜና የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል በአሁኑ ሰዓት ቲርኩልና ፖቻላ በተባሉ በኢትዮጵያ ድንበር በኩል ሰፍሮ ይገኛል ሲሉ በዚሁ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ጦር ሃይል ደቡብ ሱዳን አለመግባቱን አስተባብለዋል።
ይሁን እንጂ ቃል አቀባዩ ብርጋዴር
ሉል ሩዋይ ኮዓንግ በፖቻላ የተሰማራው የኢትይጵያ ጦርና የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ግንባር ሰራዊት የጋራ ሃይል ወደ ሙርሌ ግዛት በመግባት ታፍነው የተወሰዱትን ከአንድ መቶ የሚበልጡ ህጻናት ሊያስለቅቁ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥተዋል።
የደቡብ ሱዳን የጦር ሃይሎች አዛዥና የኢትዮጵያ አቻቸው ሰራዊቶቻቸው ተጠልፈው የተወሰዱትን ህጻናት እና የቀንድ ከብቶች ለማስመለስ ወታደራዊ ዘመቻ በጋራ እንደሚያካሄዱም ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 50 የሚሆኑ ተጨማሪ ተጠልፈው የተወሰዱ ህጻናት በሙርሌ ማህበረሰብ መገኘታቸውን የደቡብ ሱዳን ኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ማኩዌ ሉዌት ለሪፖርተሮች መገለጻቸውን ሱዳን ትሪቢዩን የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል።
እነዚህም ህጻናት ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው እንደሚሰጡም ለማወቅ ተችሏል። ተጨማሪ ተጎጂ ህጻናት ከሙርሌ ማህበረሰብ ካልተሰጡም በጋራ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚመለሱ እኚሁ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የሙርሌ ብሄረሰብ አባላት የሆኑን የደቡብ ሱዳን የምክትል መከላከያ ሚንስትሩ ዴቪድ ያው ያው እና የቦማ ግዛት ገዢ የሆኑት ቤዳን ባባ በጋምቤላ ክልል በግፍ ከተገደሉት ወላጆችና፣ ከተጠለፉት ህጻናት ጋር በተያያዘ እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ እንደነበር በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።
Source: Esat News
No comments:
Post a Comment