Tuesday, May 10, 2016

የኢትዮጵያ መንግስት የሚደርስበትን ተቃውሞ በሃይል እና በፍርድ ቤት ለመቆጣጠር እየሞከረ እንደሆነ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ከተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት የሚገልጹትን ዜጎች በጥይት ብቻ ሳይሆን፣ ፍርድ ቤቶችን ጭምር በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ማፈን መጀመሩን የሰብዓዊ መብቶች ተመልካች ድርጅት (Human Rights Watch) ገለጸ።
እንደ Human Rights Watch ገለጻ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በታዋቂ ሰዎች፣ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና በሌሎች ሰዎች ላይ ሽብርተኝነትን ጨምሮ አዳዲስ የፖለቲካ-ነክ ክሶች ማቅረብ እንደጀመረ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አቅርቧል። ባለፈው ሳምንት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ  የሽብር ተግባር ለመፈጸም  እቅድ በማውጣት፣ በማዘጋጀትና በማሴር እና ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት በሚል የሽብርተኝነት ክስ መከሰሱ መንግስት ፍርድቤትን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ያወጣው አዲስ አካሄድ መሆኑንም አመልክቷል። የመንግስት ባለስልጣናት ለክሱ ያቀረቡት መረጃ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፌስ ቡክ የጻፈው ጽህፍ ብቻ መሆኑን Human Rights Watch ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ባለፈው ሚያዚያ ወር የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ  እንዲሁም ሌሎች የኦሮሞ ፌዴራሊት ኮንግሬስ አመራር አባላትን ጨምሮ  21 ሰዎች በዚሁ በሽብርተኝነት ክስ እንደተከሰሱ Human Rights Watch ባወጣው መግለጫ አስታውሷል።
በአስከፊው በማዕከላዊ እስር ቤት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ሲናገሩ የነበሩት አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች ታሳሪዎች እንደ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው እንተከሰሱ ተገልጿል። ሆኖም አቶ በቀለ ገርባ በተደጋጋሚ ጊዜ በምርጫ ሲሳተፉ የነበሩና በሰላማዊ መንገድ በመታገል አስፈላጊነት ላይ  አቋም የሚያራምዱ መሆናቸውንም ገልጿል።
ባለፈው መጋቢት ወር 20 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአዲስ አበባ አሜሪካ ኢምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡየፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱበማለታቸው መታሰራቸውን ያሰታወሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች  በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለክሱ የቀረበው መረጃም ተማሪዎቹ የጠየቋቸው  መሰረታዊና ትክክለኛ ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ ለክሱ የቀረበው ሌላው መረጃ ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የሚያሳይ ቪዲዮ መሆኑን አመልክቷል። ተማሪዎቹ ጥፋተኛ ናቸው ከተባሉ ቢያንስ በሶስት አመት የሚያሳስራቸው ሊሆን እንደሚችልም Human Rights Watch  ሰኞ ዕለት ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት እንደ አቶ በቀለ ገርባን የመሳሰሉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በሽብርተኝነት ሲያስር አንድ ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ አላማ አድርጎ ነው ያለው Human Rights Watch ዘገባ፣ ይህም መልዕክት ማንም ሰው በማህበራዊ ሚዲያ፣ በምርጫ ካርድ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞ ማሰማት ወይም በመንግስት በኩል በቸልታ የማይታለፍ ወንጀል መሆኑን ማመላከት ነው ሲል በዘገባው አስፍሯል።

 Esat News

No comments: