Monday, December 7, 2015

"ብሶት የወለደው" የባሰ የብሶት ምንጭ ሆነ - ዘሪሁን ገሰሰ


"ቀይ ሽብር" በኢትዮጵያውያን ህሊና ውስጥ የማይረሳ አስከፊ ገፅታን ትቶ ማለፉን ማንም የማያወላዳበት ሀቅ ነው። እውነታው እንዳለ ሆኖ የድሮው ስርአት አልፎ በአዲስ ሲተካ፣ አዲሱ ስርአት በቀድሞው አገዛዝ የተፈፀሙ አሉታዊ ተግባራትን ነቅሶ በማውጣት የፓለቲካ ትርፍ ለማግበስበስ ሲጠቀምባቸው ማየት በተለይ ለእኛ የተለመደ ነገር ነው። ኢህአዲግ ደርግን አስወግዶ መንበረ ስልጣኑን ሲቆናጠጥ ህዝቡም ካለፈው የተሻለ እንጂ ያለፈውን የሚደግም እንደማይሆን ተስፋ ሰንቆ ነበር። ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ የአፍሪካ መሪዎች ወደስልጣን ሲመጡ ለህዝብ በጅምላ የሚያከፋፍሉትን ተስፋ መንበረ ስልጣኑን ከተቆናጠጡ በኃላ የገቡትን ቃል፣ የሰጡትን ተስፋ ሁሉ፣ ከወንበሩ ስር ይቀመጡበትና ከስልጣን በፊት ሲታገሉት የነበረውን አገዛዝ ድርጊትና አላማ በአዲስ መልክ አሰፍተው ወደ ህዝቡ መጫን ይጀምራሉ። "አልሸሹም ዘወር አሉ" እንደማለት ማለት ነው።
ለአብነት ያህል ኢህአዲግ ሀገሪቱን ሲረከብ ቀይ ሽብርን ተከትሎ በግፍ ለተጨፈጨፉ ወገኖቻችን የመታሰቢያ ሀውልት በመዲናችን አዲስ አበባ አስገንብቷል። ሌሎች ሀውልቶችን ማፍረሱም እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው። በዚህ የመታሰቢያ ሀውልት ላይ "መቼም፣የትም እንዳይደገም!" ወይም "Never Ever Again!" የሚል ፅሁፍ ተፅፎበታል። ሀውልት ማሰራት ቀላል ነገር ሊሆን ይችላል ነገር ግን ሀውልቱ ለቆመለት አላማ መስራት ግን ይፈትናል። እናም ሀውልት ሰሪዎቹ እራሳቸው "ቀይ ሽብር" አስወግደው፣ ወደፊት ሌላ ሀውልት የሚሰራለት ሌላ ሽብር፣ሌላ ጭፍጨፋ፣ ሌላ ግፍ፣……… መፈፀማቸው ፣የሀውልቱን መቆም ፌዝነትና የእነሱን "ብሶት የወለደው፣……" አላማ ፉርሽ አያደርገውምን???
የግፍ ጭፍጨፋው ይቁም!
የህዝብ አምላክ ህዝባዊ መሪ ይስጠን!


No comments: