Saturday, December 19, 2015

ኦህዴድ ኢህአዴግን ከዳ

በትግራይ ወጣቶች ለውትድርና እየተጠሩ ነው
tplf

በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ንቅናቄ የኦህዴድን መክዳት የሚያሳይ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ ህወሃት/ኢህአዴግ ጥቅሙን ለማስከበር የትግራይ ወጣቶችን ብሔራዊውትድርና እየጠራ መሆኑ ተሰማ፡፡
ሳምንታት ያስቆጠረውና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ምክንያት በማድረግ የተነሳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመጠኑም ሆነ በዓይነቱ ልዩ እየሆነ መሄዱ ኦህዴድ ኢህአዴግን የመክዳቱ ማስረጃ ነው ሲሉ በኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ ለጎልጉል መረጃ የሚያቀብሉ አመራር አስታውቀዋል፡፡
በኢህአዴግ የአንድ ለአምስት ጥርነፋ፤ ስለላ፤ ሕዝባዊ አደረጃጀት፤ ቁጥጥር፤ መዋቅሮችን ሁሉ አልፎ ይህንን ያህል ሕዝብ ያለአንዳች ከልካይ መውጣቱ አገዛዙ ሕዝቡን ለመጠርነፍ የተጠቀመበት አሠራር መልሶ ራሱን እየጠረነፈው እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ታማኝ ተብሎ የተቀመጠው ካድሬም ሆነ የጥርነፋው መዋቅር ሕዝቡን ሊያስቆም አለመቻሉ የኦህዴድ እምቢተኛነትና ለአገዛዙ ድጋፍና እገዛ ከማድረግ ይልቅ ከሕዝቡ ጋር ለመቆሙ እንደ ዓይነተኛ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የተዛባ አመራር እንዲሁም የኃይል (የሥልጣን) ሚዛን አለመስተካከል በኦሮሚያ ውስጥ ኢህአዴግን ተቀባይነት እያሳጣው ከመሄዱ ባሻገር ሕዝቡን ኦነግ፤ አሸባሪ…” በማለት ህወሃት/ኢህአዴግ እስርቤቱን ኦሮምኛ ተናጋሪ እንዳደረገው በስፋት ሲነገር የቆየ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በተመለከተ የቀረበውን ዕቅድ ከደገፉት ሙክታር ከድርና አስቴር ማሞ በስተቀር የተቀረው የኦህዴድ አመራር በኢህአዴግ እምነት የሚጣልበት ባለመሆኑ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ኦህዴድ ኦሮሚያን የማስተዳደር ውክልናው ቆሞ ክልሉ ህወሃት በሚቆጣጠረው ደኅንነት እየተመራ መሆኑ አብሮ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ኦህዴድ የሚታመን ባለመሆኑ ክልሉን የማረጋጋትም ሆነ የመምራት ኃላፊነት በመነፈጉ ኦህዴድ እና ኢህአዴግን የሚያስተሳስረው የመጨረሻ ገመድ ተበጥሷል፤ ከዚህ ሕዝባዊ ንቅናቄ ኢህአዴግ ማንሰራራት ቢችል እንኳን በአዲስ የሚፈጥረው ኦህዴድ ከቀድሞው ፍጹም የተለየ እንደሚሆን ይህንን ለማድረግ በራሱ ለህወሃት/ኢህአዴግ ፈታኝ እንደሆነ አብሮ ተጠቁሟል፡፡
ከኦህዴድ መክዳት ጋር በተያያዘ ህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተነሳውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚችል የሚያምነው ኃይል ባለመኖሩ የትግራይ ወጣቶች እንደ ብሔራዊ ውትድርና ዓይነት ግዳጅ መጠራታቸው ተሰምቷል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃት የጥቅም ተጽዕኖ ግልጽ በመሆኑ ይህንን ጥቅም ለማስጠበቅ የትግራይ ወጣቶች መስዋዕትነት የሚከፍሉበት ግዳጅ አሁን ነው በማለት ለአገልግሎት ተጠርተዋል፡፡
አገርህን አድንበሚል ዓይነት ጥሪ ወንድሟ ወደ ውትድርና መሄዱን በለቅሶ የተናገረች በአውሮጳ የምትገኝ እንዳለችው ከሆነ ይህ ዓይነቱ ግዳጅ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ምንም መረጃ እንደሌላት ተናግራለች፡፡ ወንድሟ በምን ዓይነት ለህይወት የሚያሰጋ ግዳጅ ላይ እንደሚሰማራም ካሁኑ ለማወቅ እንደማይቻል በማስረዳት እሷም ሆነች ቤተሰቧ በከፍተኛ ሃዘንና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ በመረበሽ አስረድታለች፡፡ ከትግራይ የተገኙ መረጃዎች እንዳመለከቱትም ወጣቶች ለተመሳሳይ ወታደራዊ ግዳጅ እየተጠሩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በኦሮሚያ ሕዝቡ ያስነሳው የተቃውሞ ንቅናቄ ቀጥሎ በዛሬውም ዕለት በተለያዩ ቦታዎች በስፋት ቀጥሏል፡፡ በህወሃት/ኢህአዴግ የሚወሰደው እርምጃ የዚያኑ ያህል የቀጠለ ሲሆን በኦፊሺያል ከሚሰጠው ቁጥር በበለጠ መልኩ እስካሁን ከመቶ በላይ ሰዎች መገደላቸው በስፋት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይነገራል፡፡ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የተመረሩ ኃይሎች በሁሉም ክልሎች የሚኖረው ሕዝብ እንዲሁም በውጭ አገር ያለው በኅብረት መንቀሳቀስ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

Source: goolgule

No comments: