ሕዝብን በፍቅር እንጂ በኃይል ማንበርከክ አይቻልም – ግርማ ካሳ
ሁልጊዜ እንደምናደረገው ብሄራዊ እርቅን፣ ሰላምን እንሰብካለን። እስከአሁን ሰሚ አላገኘንም። ቢሆንም ለአገርና ለህዝብ ይበጃል የምንለዉን የሰላም ጥሪ እየደጋገምን፣ ሰሚ ኖረም አልኖረም እንጻፋለን። እንናገራለን። የጥበብና የማስተዋል መንፈስ ይለቀቅልን ዘንድ፣ በተለይም ሌላውን ጋኔን የሚሉ ግን ነርሱ ጋኔን የሰፈረባቸው መሪዎች ልቦና እንዲሰጣቸው፣ በኣጠቃላይ አገራችን ወደ ደም መፋሰስና ረብሻ እንዳትሄድም እንጸልያለን። ነገሮች በመክረራቸው ማንም አይጠቀምም፤ ምናልባት እንደ ግብጽና ሻእቢያ ያሉት ካልሆኑ።
አዲስ አድማስ እንደዘገበው ወደ 18 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል። እንደ ህዝብ እንደ ኣገር ትልቅ ችግር ላይ ነው ያለነው። በኦሮሚያና በጎንደር የተነሳው ቀዉስ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ነው የመጣው። ችግሩ ስር የሰደደ እንደሆነ ራሳቸው ስልጣን ላይ ያሉት ያውቁታል። በአሁኑ ጊዜ ለነርሱም ፣ ለሕዝቡ ለሁላችንም የሚያስፈለገው ሰላማና መረጋጋት ነው። “ነገሮች ይስተካከላሉ “ ብሎ ቃል በመግባት ሰላምና መረጋጋት የሚመጣ አይደለም። ይቅርታ ይደረግልኝና አገዛዙ ቃል የሚገባዉን እንኳን እኛ፣ እነ ሪፖርተርም አይምኑትም። ሰላምና መረጋጋት በጠመንጃና በጉልበት የሚመጣም አይደለም። ሰላምና መረጋጋት የሚመጣው መተማመን ባለበት የፖለቲካ መፍትሄ ነው።
በመሆኑም ከዚህ በፊት እንደጻፍኩት ደግሜ እጽፋለሁ። የሕወሃት/ኢሕአዴግ አመራሮች በርጋታ ቁጭ ብለው ይምከሩ። ሕዝቡም ሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ እነርሱ ላይ በግለሰብ ደረጃ ጸብ የለውም። ጸቡ በዘረጉት የአፈና ስርዓት ላይ ነው። በቅርቡ በሜዲያ ላይ ይፋ እንዳደረጉት፣ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር አለባቸው። የአምስት ዓመት እቅድ ብለው ያወጡት እንደሚጠበቀው ተግባራዊ አልሆነም። ሌላ የአምስት አመት እቅድ አውጥተዋል። ይሄን አዲስ ፕላን ያለ ህዝብ ተሳትፎ ዉጤት እንደማያመጣም ራሳቸው ደጋግመው ተናግረዋል::
እንግዲህ ሕዝብን ያስቆጣው፣ ራሳቸውም ያመኑበትን የፍትህ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራታይዜሽን ችግር በተጨባጭ ለመፍታት ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው። የፖለቲካ መፍትሄ መፈለግ አለባቸው። የፖለቲካ መፍትሄ ማለት ደግሞ ህዝብን ከጎን ማሰለፍ መቻል ማለት ነው። በኦሮሚያና በጎንደር የተነሳው ህዝብ ነው። እነርሱ እንደሚሉት ኦነጎች ወይንም ግንቦት ሰባቶች አይደሉም። ይሄንን ሕዝብ ላይ ጦርነት ከማወጅ፣ ሕዝቡን ማዳመጥ ያስፈልጋል።
በመሆኑም የሚከተሉትን ምክሮች እለግሳለሁ፡
1. በጎንደር እና በኦሮሚያ በሕዝቡ ላይ የተሰማራው ጦር ወደ ካምፑ እንዲመለስ ትእዛዝ መሰጠት አለበት
2. የሕሊና እስረኞች በሙሉ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው፡
3. ገዢዎች ለብሄራዊ እርቅ ዝግጁ እንደሆኑ በመገልጽ አገር ቤት ካሉ በዋናነት ከሰማያዊ፣ መድረክ፣ ኤዴፓና መኢአድ ጋር፣ እንዲሁም በእሥር ቤት ካሉና በተራ ቁጥር 2 መሰረት ከሚፈቱ እንደ አንዱዋለም አራጌ፣ ሃብታሙ አያሌው ካሉ አንጋፋ የፖለቲክ መሪዎች ጋር በአስቸኳይ በመነጋገር፣ አዲስ ምርጫ መደረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው። ሕገ መንግስቱ ጠ/ሚኒስትሩ አዲስ ምርጫ መጥራት እንደሚችል ይደነግጋል። ካለኝ መረጃ የጠቀስኳቸው ደርጅቶች ሁሉ ቁጭ ብለው የጋራ መፍትሄ ይገኝ ዘንድ፣ ሰላምና መረጋጋት ይመጣ ዘንድ ለመወያየት ዝግጁ ናቸው። አላስተዋሉትም እንጂ ከማንም በላይ እነዚህ ደርጅቶች ናቸው አገር በማረጋጋቱ አንጻር ሊረዷቸው የሚችሉት።
4. ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ከኢሕአዴግ እና ከተቃዋሚዎች የተወጣጣ የአንድነት መንግስት ወይንም የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት። ይህ መንግስት ዋና አጀንዳው አገሪቷ ተርጋግታ በሰለም እንድትቀጥል ማድረግ ሲሆን፣ መጪው ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ የሚሆንበት ሁኔታ ያመቻቻል። የተጀመሩትም የልማት እንቅስቃሴዎችን ያስቀጥላል።
ኢሕአዴጎች ባለፈው ምርጫ 100% አሸንፈናል ብለዋል። ስለዚህ ዳግም ምርጫ ሊያስፈራቸው አይገባም። ለአገር ደህንነትና ሰላም ሲባል ወደዚህ አቋም መምጣት ካልቻልይ በራሳቸው ላይ እባብ እንደመጠምጠም ነው።
የተለያዩ ባለስልጣናት ሜዲያ ላይ እያስወጡ መግለጫ መስጠት መፍትሄ አይደለም። ቶሎ ተነጋግረው ፣ ነገሮች ሳይባባሱ ለአገር፣ ለህዝብ፣ ለትዉልድ የሚጠቅመዉን የብሄራዊ እርቅ አጀንዳ ያስቀድሙ። ህዝብን በፍቅር እንጂ በኃይል ማንበርከከ አይቻልም። ከሕዝብ ጋር ተስማምተው እስካልሄዱ ድረስ፣ ህዝብን እስካላከበሩ የሚሻሻል ነገር አይኖርም። አወድዳደቃችው እጅግ በጣም የከፋ ነው የሚሆነው።
የሕዝብ ጥያቄ ደግሞ፣ አንዳንድ አክራሪዎች እንደሚሉት የዘር ጥያቄ አይደለም። የዴሞክራሲ፣ የሰላም፣ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው። እነርሱም ራሳቸው ቆመንለታል፤ ታግለንለታል የሚሉት ጥያቄ ነው።
ይሄን ስጽፍ አንዳንዶች ግርማ ካሳ በአቋራጭ ስልጣን ፈልጎ ነው የሚሉ ደካሞች ይኖራሉ። በተለይም አፍቃሪ ሕወሃቶች። የምንም የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ማሀበር አባል እንዳልሆንኩ ይታወቅልኝ። በአሜሪካን አገር ቤተሰብ ያለኝ፣ በጣም ጥሩ ኑሮ የምኖር፣ መብቴ ተጠብቆ፣ እነ ኦባማን በነጻነት እየተቸው፣ ያለ ፍርህት፣ ቀና ብዬ የምኖር ሰው ነኝ። የምጽፈው ቢያንስ እኔ በአሜሪካን አገር መጥቼ ያገኙሁት መብት፣ በአገሬ ያለው ወገኔ እንዲያገኝ፣ በሶሪያ ያየነው በኢትዮጵያ እንዳይደገም ነው።
No comments:
Post a Comment