Monday, August 12, 2013

ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ! – ታደለ መኩሪያ

ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ! – ታደለ መኩሪያ

Dr. Tedros Adhanom Ghebreyesus, Minister of Health, Ethiopia, speaking at the London Summit on Family Planning (7556214304) (cropped).jpg
በሞያቸው አንቱ የተባሉ፣ በኤቺ አቪ ኤድስ ላይ ብዙ የሠሩ፣ ከቀ ሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆርጅ ቡሽ አድናቆት የተቸራቸው፤የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣የዛሬው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር አባልና የውጪ ጉዳይ ተጠሪ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኖም በታሪክ የሚያስወቅሳቸው ሥራ ሰሩ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን እንደዛሬዎቹ በጋንቤላ ኤቺ አቪ አድስ የተሰፋፋው ወንዶች ባለመገረዛቸው፤ወጣት ሴቶች ወንዝና እንጨት ለቀማ ሲሄዱ በአጋዚ ጦርና በፌደራል ፓሊስ አንዳልተደፈሩ ከቄያቸው ተፈናቅልው በካንፕ ሕዝቡ እንዲኖሩ እንዳልተደረገ ሲነግሩን ፤ ጤፍ የተወደደው
የመካከለኛ ገቢ የሚገኘው በማደጉ፤ ስኳር የተወደደው ገበሬ በስኳር ቡና መጠጣት ስለጀመረ የተባሉትን ወያናዊ ፌዞች ሰምተናል። እርሶ ግን ከዚያ ነፃ ነበሩ። ምን ነካዎት? በአደባባይ ወጥተው በዓለም ሕብረተሰብ ፊት ለፍትህ የቆሙትን፣ ድምፃችን ይሰማ ያሉትን የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችንን፤ ሰላሳ ሦስት ወራት በሙሉ አንዲት ጠጠር ሳይወረውሩ፤ የዓለም ሕዝብ በአንክሮ የተከታተለውን የሕዝብ የመብት ጥያቄ፣ የአሸባሪነት ጥላት ለመቀባት መሞከሮ ለሃገርም በግልም ለያዙት የሥራ አላፊነት ግምት ማሣጣት አይሆንም? የሃገራችን የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችንን ጥያቄ፣ የአሸባሪ ሥራ ነው ፣ ለማለት መሞከር በተዘዋዋሪ እስራትን ፣ግድያን ሕጋዊ ነው ማለት አይሆንም?
በአዲስ አበባ ለሚኖሩት የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ከአሸባሪዎች ጥቃት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በዓለም ዙሪያ ለሚሰራጩ የዜና አውተሮች ይህን ማሳሰቢያ ሲያደርጉ በሚያገለግሉት ግንባር ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ተረድተውት ይሆን? ይህ በምንም ማስረጃ ያልተረጋገጠ ፡ ልፈፋ፣ ለሃገሪቱ መጥፎ ገጽታን አይፈጥርም? የውጪ ጎብኝዎች አቅጣጫቸውን ይለውጣሉ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፋሪ ያጣል፣ሆቴሎች ባዶቸውን ያድራሉ፣የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይፈጠራል፤ በዚህ መስክ ብዙ ማለት ይቻላል።
ሆኖም ግን የዶክተር ቴዎድሮስ አዳኖምን መግለጫ ዴፕሎማቶ ቁብ አይሰጡትም። ውሸት መሆኑን ያውቃሉ። ስለዚህ ከላይ ያልኩት ችግሮች ላይደርሱ ይችላሉ፤ ለምሳሌ የአውሮፓውያን ልዑካን በአሸባሪነት ስም የታሰሩትን የነፃነት ታጋዮች ለመጠየቅ ነበር፤ መንግሥት ነን ባዮቹ ጋንግስተሮች ግን አንፈቅድም አሉ፤ ይህ የአውሮፓ ልዑክ በየመን እስረኞችን ጎብኝተዋል፣በቅርቡ በግብፅ የታሠሩትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር መሐመድ ሙርሲን እንዲጎበኝ ተፈቅዶላቸዋል፤ የሚገርመው በጋግስተሮች መሣሪያ ተደቅኖባቸው የሚያገለግሉት ኃይለማሪያም ደሳለኝ ፣ ግብፅን እየመራ ያለውን ስብስብ
በ ፀረ ዴሞክራሲነቱ መፈረጃቸው ነው፤ ‘ያሉሽን በሰማሽ ገበያ ባለወጣሽ’ ይላል የሃገሬ ሰው! ሌላው ደግሞ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች በመካከለኛው ምስራቅ፣ በጥቂት የአፍሪካ አገራትና ኢሲያ የኢንባሲ ጽሕፈት ቤታቸውን እንዲዘጋ ሲያደርጉ እንዴት ኢትዮጵያን ዘለሏት? ዶክትር ቴዎድሮስ አድኖም እዚች ላይ አንዴት ነገር ለሕዝባችን ቢነግሩት፣መልካም ነበር። የስለላ መረባችሁ እንደ አትሌቱ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሪኮር የሰበረ መሆን አለበት፤ ከአሜሪካና ከአውሮፓ የስለላ መረቦች ልቆ መገኘቱ አጀብ ጉድ የሚያሰኝ ነው። ‘ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ይሏታል’ ይሏል እንዲህ ነው! ይህ ሁሉ ውዥንብር የእስልምና ሃይማኖት ተከታዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመብት ጥያቄ ለማሸዋረር መሆኑን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፤ አካፋን አካፋ ከማለት፤የጎኝዮሹ መሄዱ ለምን አስፈለገ?
ከዚህ ቀደም የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስፍን ሥዩም በአደባባይ ሲዋሹ ለከት አልነበራቸውም፤ ባድሜ ለኢርትራ ተስጥታ ለትግራይ ተከለለች ብለው በአዲስ አበባ የሚኖሩትን የትግራይ ማህበረሰብ በመስቀል አደባባይ ከበሮ ሲያስደልቁ ቆይተው፤ ወሸት ሆኖ ሲገኝ አንገታቸውን ደፉ፤ በሱማሊያ አልካይዳ ገባ ብለው ሠራዊት ወደ መቅድሾ እንዲዘምት አስደረጉ፤ የሠራዊቱ እሬሳ በመቅድሾ ጎዳና ሲጎተት በእፍረት የሟቾቹን ቁጥር ለመናገር ድፍረት አጡ፣ ሌላውን ግን ሂድ ሙት ለማለት ደፈሩ።
ሌላው የሕዝብ ግንኙነቱ በረከት ስሞዖን ነው፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አርፈው አስኬሬናቸው በሬሣ ቤት እንደለ እየታወቀ ለዘመን መለወጫ ሥራ ይጀምራሉ ሲሉን ቆዩ፤ አቶ በረከት ሲያስነጥሳቸው የሚያስላቸው ሸመልስ ከማል ደግሞ ኢሳት የአቶ መለስን ማረፍ ሲያበስር መገናኛ ብዙሃኑን ወሸታም ነው በማለት ሲያጣጥሉ ተሰሙ፤ ውሎ አድሮ ግን እውነቱ ፍትው ብሎ ወጣ፤ ይህ ሁሉ ቅጥፈት በክርስትና በእስልምና ሃይማኖት ለዘመናት ተኮትኩቶ ለኖረ ሕዝብ አሣፋሪ ነው። በእርግጥ ይህን መሰል እኮይ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች ከጨዋ ሕብረተሰብ መካከል ሳይሆን ከደደቢት በረሃ፣ ከጫት
ጋራባ ተራ ለጥቅም የተሰባሰቡ መሆናቸውን የባንክ ሰነዳቸው የሚያሳየው ያንኑ ነው። ግን ዶክተር ቴዎድሮስ አዳኖምን የመሰለ፣በዓለም ዙሪያ እንዳሉ ዶክተሮች በተሰማሩበር ሞያ በሐቅ ሊሰሩ ካልሆነ ሊለቁ ሙሉ ነፃነት የተጎናጸፉ ቃለ ማህላ የፈጸሙ ታላቅ ሰው እንዴት ወርደው ተዋርደው ከነመስፍን ሥዩም ፣ ከረከት ስሞዖንና ከሸመልስ ከማል ጎራ በውሸታምነት ይፈረጁ? ‘ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ’ ይሏችኋል ይህ ነው።
የእስልምናም ሆነ የክርስትና ተከታዩ ሕዝባችን በታሪኩ የተከበረ ለብዙ አገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ በዘመነ ወያኔ አሸባሪ ሊሆን አይችልም። አሸባሪው መሣሪያ የታጠቀው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን በቆራጥነት፣ በትዕግስት፣ በአስተዋይነት፣ ይህን የጋግስተር ቡድን እናስወግደዋለን።የውሸት ወሬ ና ወያኔ ይህቺን ባለታሪክ አገር ሊፈታተናት አይገባም።
መልካም ኢድ አልፈጢር ፤ አሃሙዱሉላሂ ሃገራችን ሰላም ትሆናለች።
ታደለ መኩሪያ

No comments: