Friday, August 2, 2013

የቀድሞ የአዲስአበባ መሬት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ በኮበለሉ በአንድ ወራቸው ተያዙ

የቀድሞ የአዲስአበባ መሬት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ በኮበለሉ በአንድ ወራቸው ተያዙ

ሐምሌ 26 ቀን 2005ዓ/ ኢሳት ዜና :- ያለመከሰሰ መብታቸው በፓርላማ እንዳይነሳ ከተወሰነ በኋላ እንደገና ፓርላማው ውሳኔውን በማጠፍ ያለመከሰስ መብታቸው
የተነሳውና ወዲያውኑ ባልታወቀ ሁኔታ ከአገር እንዲወጡ ተደርገው የነበሩት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት
ልማትና አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር ዋሉ፡

የኦህዴድ አባልና የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ ከመሬት ጋር በተያያዘ ያለመከሰሰ መብታቸው እንዲነሳ ፓርላማው ሰኔ 28 ቀን 2005 . ከወሰነ በኋላ የፌዴራል የስነምግባርና የጸረሙስና ኮምሽን ሰውየውን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሞከረበት ወቅት ሊያገኛቸው እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ ኮምሽኑ ባደረገው ማጣራትም ተፈላጊው ወደቻይና መውጣታቸውን ማረጋገጡ የኮምሽኑን ከፍተኛ ባለሰልጣናትን አደናግጧል፡፡

የአቶ ቃሲም ያለመከሰሰ መብት ጉዳይ ለፓርላማ የቀረበው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን ተጨማሪ ማጣራት ለማድረግ
ኮምሽኑ በጠየቀው መሰረት ጉዳዩ ለፓርላማው ሳይቀርብ መዘግየቱን ምንጫችን ጠቁሟል፡፡ በወቅቱ ሰውየው ከአገር
እንዳይወጡ ለኢምግሬሽን ደብዳቤ መጻፉን ምንጮቹ አስታውቀው ደብዳቤው ባልተነሳበት ሁኔታ ሰውየው እንዴት ከአገር ሊወጡ ቻሉ የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ከመሆኑም በላይ ሙስናን ለመዋጋት ስርዓቱ ቁርጠኝነት አለው ወይ የሚል ጥያቄም በብዙ ወገኖች ዘንድ አስነስቷል፡፡
በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ትላንት የተሰራጨው ዜና እንዳመለከተው አቶ ቃሲም ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በኋላ ከአገር የወጡት ለስልጠና ነው፡፡ በሙስና የተጠረጠረና የሚፈለግ ግለሰብ ለስልጠና ነው የተላከው ማለት የማይታመን ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ የእሳቸው ከአገር መውጣት በስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ውጥረት በመፍጠሩ በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው ያለበት ባለስልጣናት ግለሰቡ ወደአገር እንደሚለሱ ሳያግባቡዋቸው እንዳልቀረ ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል ፡፡
አቶ ቃሲም በኮምሽኑ የቀረበባቸው ክስ እንደሚያትተው 1987 . በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ /ከተማ ወረዳ 3 ውስጥ የሚገኘውን ስፋቱ 500 ካሬሜትር ቦታ ሕንጻ እንዲገነቡበት ለኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ
ተሰጥቶ ግብር ሲከፍሉበት መቆየታቸውን ቦታው ላይ ለነበሩ ተነሺዎች በራሳቸው ወጪ በሌላ ቦታ ገንብተው ማስፈራቸው እየታወቀ የኢንጅነሩ ካርታ መክኖ ቦታውን ከኋላ መጥተው ላመለከቱት ለአቶ ዮሐንስ ደርሰህ የአሌክሳንደሪያ ሆቴል ባለቤት እንዲሰጥ አድርገዋል የሚል ነው፡፡
ተጠርጣሪው በዛሬው ዕለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ይጠየቅባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል

No comments: