የአሜሪካ ፓሊስ ኢትዮጵያውያኑን በማደን ላይ ናቸው
ኢሳት ዜና :-የአሜሪካ ፖሊሶች ከኢትዮጵያ ለምስክርነት መጥቶ የጠፋን ኢትዮጵያዊ ዱካ ለማግኘት ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ሲአትል ኒውስ ዛሬ ዘገበ፡፡
ካሳይ ወልደ ፃድቅ የተባለው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊያኖቹ ጥንዶች ከኢትዮጵያ በማደጎ ያመጧትን ልጅ ገድላችኋል ተብለው ለተከሰሱበት ወንጀል አቃቢ ህግ ለምስክርነት ማስረጃ ይሆን ዘንድ ብለው ነበር ከኢትዮጵያ ያመጡት፡፡
ካሳይ በፍርድ ሂደት ላይ ላለው ጉዳይ ባለፈው አርብ በማውንት ቬርኖን ካውንቲ ፍርድ ቤት በመቅረብ የመጀመሪያ ዙር ምስክርነቱን ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በሚቀጥለው ቀን ከተያዘለት ማረፊያ ክፍል መጥፋቱን አቃቢ ህጎች ለፖሊስ አስታውቀዋል፡፡
አሜሪካዊ ጥንዶቹ ወደ አሜሪካ ላመጧት የ13 ዓመቷ ታዳጊ ሀና ዊሊያምስ ካሳይ የቅርብ ቤተሰብ ሲሆን የምስክርነት ቃሉን ሳይሰጥ መጥፋቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ለማስረጃነት ይረዳናል ብለው ከኢትዮጵያ ያመጡት አቃቢ ህጎች ጉዳዩን ለፖሊስ ካሳወቁ ጀምሮ ፖሊስ የተጠናከረ አሰሳ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የሰባት ቀን ቆይታ ብቻ የተፈቀደለት ኢትዮጵያዊ እስከ እሁድ ድረስ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ በፍርድ ሂደት ላይ የነበሩት ዳኛ ወስነውበታል፡፡ ካሳይ የግሉ የነበሩ እቃዎቹን በማረፊያ ክፍሉ በመተው የተሰወረ ሲሆን ፖሊሶች የዳኛን ፍርድ ለማስፈጸም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማድረግ በፍለጋ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሁለቱ አሜሪካዊ ጥንዶች ከኢትዮጵያ በማደጎ ያመጧትን የ13 ዓመት ታዳጊ ምግብ በመከልከልና በማሰቃየት ገድላችኋል በሚል ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡
በማደጎ ያመጧት ሀና ዊሊያምስ አሜሪካዊያኖቹ ጥንዶች ግቢ ውስጥ ነበር በ2011 በመጣች በሶስት አመቷ ሞታ የተገኘችው፡፡
በአካሏ ላይ የድብደባ ምልክት የሆኑ ጠባሳዎች በወቅቱ የተገኘባት ሲሆን አሳዳጊዎቹ ከፍተኛ የሆነ በደልን ሲያደርሱባት እንደነበር አቃቢ ህጎች ለፍርድ ቤት በማስረዳት ላይ ናቸው፡፡
አሜሪካዊያኖቹ ጥንዶች ሌላ መስማት የተሳነው ኢትዮጵያዊም ታዳጊ የድብደባና ከፍተኛ በደል በማድረስ በሚል ሌላ ተጨማሪ ክስ ተመስርቶባቸው ይገኛል፡፡
አቃቢ ህግ ለማስረጃነት ያመጣው ግለሰብ በመጥፋቱ አማራጭ ማስረጃን ለመጠቀም መገደዳቸውን ጉዳዩን የያዙት የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነዋሪነቱ በኖርዝ ካሮላይን የሆነ የ57 ዓመት ኢትዮጵያዊ አዛውንት ባለቤቱንና ልጆቹን በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ጉዳት በማድረሱ በፖሊስ ቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ምሩፅ ሀይሉ የተባለው ግለሰብ ባለፈው ሰኞ ነበር መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ባለቤቱንና ሁለት ህፃን ልጆቹን በስለት ጉዳት ያደረሰባቸው፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ምሩፅ በማግስቱ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን አሰቃቂ የተባለውን ድርጊት ለምን እንደፈጸመ እስካሁን የሰጠው ምክንያት የለም፡፡
ሚስቱና ልጆቹ በህክምና ላይ ሲሆኑ የፍርድ ሂደቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
ESAT
posted by Gheremew Araghaw
No comments:
Post a Comment