Saturday, August 3, 2013

የነጋዴው ኢህአዴግ ኢንዶውመንቶች

Addis Guday
አዲስጉዳይ በዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2005 ዕትሙ
በዐብይጉዳይ አምድ “የነጋዴው ኢህአዴግ ኢንዶውመንቶች” በሚል ርዕስ ሰፊ ዘገባ ይዞ ወጥቷል።
በዚህ ዘገባ የገዢውን ፓርቲ የንግድ ኢምፓየር ጉዳይ ይዳስሳል። የኢትዮጵያ ህግ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በማንኛውም የንግድ ሥራ ላይ እንዳይሰማራ የሚያግደው ሆኖ ሳለ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ግን በህወሓት ትዕምት፣ በኢህዴን ጥረት፣ በኦህዴድ ቱምሳ እና በደኢህዴን ወንዶ የሀገሪቱን ዋና ዋና የንግድ ዘርፎች ተቆጣጥሯቸዋል። አዲስጉዳይ በዛሬ ዘገባው ይህ ከህግ ጋር የሚጣረስ የፓርቲ ነጋዴነት ተግባር የግሉን ዘርፍ የሚያዳከም ብቻ ሳይሆን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ ነው ይላል።
በታፈኑ ዕውነቶች አምድ “ባቡሩ ገና ሳይመጣ ገጨን” በሚል ርዕስ በቅርቡ ጎጃም በረንዳ የደረሰው የህንጻ መደርመስ ጉዳት ኃላፊነት የሚወስድ አካል መኖር አለበት የሚል ዘገባ ይዞ ወጥቷል።
ጽሁፉ ለባቡር መስመር ግንባታ ተብሎ የሚፈርሱ ቤቶች ያለባለሙያ ጥናት መካሄዳቸው የመንግሥት ቸልተኝነት መሆኑን በመተቸት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችም ከተጠያቂው አካል ካሳ እንደሚገባቸው የተጎጂዎቹንና የተቆርቋሪ ዜጎችን ድምጽ ዋቢ አድርጎ ያትታል። መንግሥት ለዜጎቹ ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚገባውና ተጠያቂውን አካል ማሳወቅ እንዳለበትም ያሳስባል።
በቃለምልልስ አምዱ ከዶክተር መረራ ጉዲና ጋር ስለኢህአዴግ ኢንዶውመንቶች፣ ስለስለቀድሞ ፖለቲካ አካሄድ እና ስለመድረክ የወቅቱ እንቅስቃሴ ቆይታ አድርጓል።
በወቅታዊ ጉዳይ አምዱ “የኢትዮጵያ መንግሥት በእብሪት አካሄዱ እንዲቀጥል መፈቀድ የለበትም” የሚለውን የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን መልዕክት ያስነብባል።
በስፖርት አምዱ ኢብራሂም ሻፊ “ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮንነቱን ተነድፎ አልቋል?” ብሎ ይጠይቃል።
በኃይሉ ገብረእግዚአብሔር፣ አሌክስ አብርሃም እና ህይወት እምሻው አዝናኝ ጽሑፎቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሌክቸረር አበባው አያሌው “እማ ቀበጢና ታጥቃ በዘጠና” የሚል ጽሑፉን ይዞ ቀርቧል። የኢራፓ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በነጻ መድረክ አምድ “ከሁሉ በፊት ብሔራዊ መግባባት ይቀድማል” ሲሉ የወንጀል አምድ ደግሞ “የልጅቷን 40 ቀን” ታሪክ ያስነብበናል። ሌሎች ቋሚ አምደኞችም እንደተለመደው በምርጥ ጽሑፎቻቸው መጥተዋል። የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሰሞነኛ ጉዳዮች ዜናና ወቅታዊ መረጃዎችንም ይዘውላችሁ ቀርበዋል።

ዝግጅት ክፍሉ ለአንባቢያን ከአዲስ ጉዳይ ጋር መልካም ቅዳሜ ይመኛል።


No comments: