ከ33ቱ ፓርቲዎች “የኃይል እርምጃ ለህዝብ ጥያቄ መቼውንም መልስ አይሆንም !!” በማለት መግለጫ ሰጡ
የኃይል እርምጃ ለህዝብ ጥያቄ መቼውንም መልስ አይሆንም !!
ከ33ቱ ፓርቲዎች ትብብር በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሠላማዊ ትግል በወሰዳቸው እርምጃዎች ላይ የተሰጠ መግለጫ
ትብብራችን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በህገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የእምነት ነጻነት መብቱን ተከትሎ ጣልቃ አትግብቡኝ ሲል ያቀረባቸውን ሦስት ጥያቄዎች በሚመለከት መንግሥት ከሰለጠነ የመፍትሄ ውይይት ፋንታ ከሚወስዳቸው ህገወጥ እርምጃዎችና ፍረጃ እንዲቆጠብ፣ በፈጠራ የሽብር ወንጀል ያሰራቸውን የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንዲፈታና ለጥያቄዎቹም ፍትሀዊ ምላሽ እንዲሰጥ የካቲት 05/2005 ባወጣነውና ሌሎች መግለጫዎች በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ገዢው ፓርቲና መንግሥት ግን በሙስሊሙ ማኅበረሰብ፣ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አልፎም ጥያቄው ይመለስ በሚሉ ወገኖች ላይ አፈና ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ጥያቄዎችን በኃይል ለማፈን በያዘው መንገድ ገፍቶበታል፡፡ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻው ከውንጀላው ባለፈ በሙስሊምና ክርስቲያን አማንያን መካከል ያለመተማመን በመፍጠር አገራችን የምትታወቅበትን የኃይማኖት መቻቻልና የህዝቡን በመከባበር ላይ የተመሠረተ የዘመናት ቁርኝትና ታሪክ አብሮነት የሚፈታተን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት ድርጊት የቱንም ያህል አሰቃቂና ዘግናኝ ቢሆንም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የተነጠቀውን መብት ለማስመለስ የተያያዘውን ፍጹም ሠላማዊ ትግል ዛሬም ቀጥሎበታል፡፡ የትግሉ ሠላማዊነት በኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሣይሆን የዓለም ማህበረሰብ ምስክርነት ያገኘ ሲሆን በተቃራኒው የመንግሥት እርምጃ ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ በመምጣቱ የዜጎች እሥራት፣ ድብደባ፣ ግድያና በአጠቃላይም ሥቃይ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው፡፡
‹‹በጀሃዳዊ ሃረካት›› ፊልም እንደታየው በየጊዜው በሚፈበረኩ የፕሮፖጋንዳ ዘዴዎች መንግሥት የሙስሊሙ ማኅበረሰብንና የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በአሸባርነት ቢፈርጅም በመረጃና ማስረጃ የተደገፈ የሽብር ድርጊት ቀርቶ አንዳች ጠጠር ሲወረወር እንኳ ለማሳየት ባለመቻሉ በአብዛኛው ወገን ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህንን ፕሮፓጋንዳ የሚያራግቡ በዜጎች ሀብት የሚተዳደሩ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃንም ያተረፉት ትዝብት ብቻ ነው፡፡ በቅርቡም የተቀደደ ባንዲራ በማሳየትም ሆነ በህዝብና በምዕራባዊያን ላይ ሥጋት በመርጨት ሙስሊሙን ከሌላው ለመለየት የተደረገው ጥረት የተፈለገውን ውጤት አላመጣም፡፡ በአንፃሩ በአርኣያነት የሚጠቀሰው የ18 ወራት ኮሽታ ያልተሰማበት የሚሊዮኖች ሠላማዊ የትግል ጉዞ ዛሬም ቀጥሏል፡፡
እነዚህ በውንጃላ፣ ፍረጃ፣ እስራት፣ አካል ማጉደል፣ ግድያ ማስፈራራት የታጀቡ በተለያዩ ጊዜና ቦታዎች ( አዲስ አበባ፣ አሳሳ፣ገርባ፣ ኮፌሌ፣ደሴ ፣ሀረር…)፣ የተወሰዱ የኃይል እርምጃዎችና መጠነ ሰፊ ፕሮፖጋንዳዎች ጥቂቶችን ግራ አላጋቡም ባይባልም የተፈለገውን ውጤት ባለማስገኘታቸው በታላቁ ኢድ አል ፈጢር በዓል መባቻ ሰሞንና በበዓሉ ዕለት ተመሳሳይ የኃይል እርምጃ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንግሥት መወሰዱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በዚህ በሞራልም ሆነ በማናቸውም መለኪያ በዜጎች ላይ ሊታሰቡ የማይገባቸው አሰቃቂና ዘግናኝ ህገወጥ እርምጃዎች ህጻናትን፣እናቶችንና አረጋዊያንን ጨምሮ በአስሮች ተገደለዋል፣ በመቶዎች ቆስለዋል፣በሺዎች ታስረዋል፡፡ ሆኖም ከጅምር የተመለከትነው የኃይል እርምጃና የሥነ ልቡና ጦርነት እያየለ ቢመጣም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በኃይማኖታችን ጣልቃ አትግቡ ከሚለው ዓላማቸው በጽናት በመቆም የሠላማዊ ትግል አርኣያ ሆነዋል፡፡
መንግሥት በኃይልና በሴራ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ጥያቄዎችን ለማፈን የሚከተለው አካሄድ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመራና አገራችንና ህዝቧን የበለጠ የከፋና ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል መስጋት ክፉ ምኞት ወይም መርዶ ነጋሪነት አይደለም፡፡ ይህን አስጊ ሁኔታን ለመከላከል የሚቻለው ዜጎች በኃይማኖት ሳይከፋፈሉ የመንግሥትን የኃይል እርምጃ በጋራ ሲቃወሙና ሲያወግዙ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔውም የችግሩ ባለቤት የሆነውን አምባገነናዊ የአገዛዝ ሥርዓት በምርጫ መለወጥ እንደሆነ ትብብራችን ያምናል፡፡
ስለሆነም ትብብራችን በትግሉ ላለፉት ቤተሰቦች መጽናናትን፣ ለተጎጂዎች ጥንካሬንና ጤንነትን እየተመኘ በሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን የኃይል እርምጃ አጥብቆ የሚያወግዝ መሆኑን በድጋሚ እያረጋገጠ፡-
1) መንግሥት የመረጠው አካሄድ ችግሮችንና ጥያቄዎችን በሰለጠነ የውይይት መድረክ ከመፍታት ይልቅ ጠያቂዎችን በመፈረጅ ‹‹ከፋፍለህ/ነጣጥለህ ምታ›› አማራጭ በመሆኑ በሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በዜጎች ህገመንግሥታዊ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ላይ የተፈጸመ ህገወጥ አምባገነናዊ ድርጊት ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የኃይል ድርጊቱን እንዲቃወሙና እንዱያወግዙ፡፡
2) በአገር ቤትና በውጪ ያላችሁ መገናኛ ብዙኃን፣ የነጻው ፕሬስ አባላት፣ማኅበራዊ ድረ-ገጾች… በተያያዛችሁት አማራጭ የመረጃ ምንጭነታችሁ በመግፋት ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ በማድረስ በህዝበ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል ያለመተማመን ለመፍጠር ከሚሰራጨው አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሰለባነት የመታደግና የዘመናት አብሮነቱን የማጠናከር የሙያና የዜግነት ግዴታችሁንና አገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ፤
3) መንግሥት/ገዢው ፓርቲ የተያያዘው አፍራሽ አምባገነናዊ አካሄድ በአገራችንና በዜጎቿ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ተገንዝቦ ከድርጊቱ እንዲታቀብ፣ የሙስሊም ወገኖቻችንን ጥያቄ በኃይል ለመፍታት የሚያደርገውን ህገወጥ እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ የእምነት ነፃነታቸውን በሠላማዊ መንገድ ስለጠየቁ የታሰሩ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣የህገወጥ ድርጊቱ ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ እንዲያደርግ፤
4) የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ተቆሪቋሪዎችና የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አባላት መንግሥት ለሠላማዊ ትግሉ የአሸባሪነት ታፔላ በመለጠፍ የሚወስደውን ህገወጥ እርምጃና መሰረተቢስ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እንድታወግዙና የህዝብ ወገንተኝነታችሁን እንድታረጋግጡ፤
ጥሪያችንን አበክረን እናቀርባለን፡፡
የተቀናጀና የተባበረ ህዝባዊ ትግል በአምባገነኖች ኃይል አይቀለበስም!!!
ነሐሴ 4/2005 አዲስ አበባ
Zehabesha
No comments:
Post a Comment