ጦርነት እልባት ወደ አላገኘባት የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ጉዳዩ አሳስቦት እንደሚገኝ የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ማክሰኞ አስታወቀ።
ድርጅቱ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ከሃገሪቱ መውጫን አጥተው የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን በማውጣት ላይ ቢሆንም በተቃራኒው ግን ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር መጨመሩን (IOM) ይፋ አድርጓል።
ባለፈው ወር ብቻ 10ሺ
424 ስደተኞች ወደ የመን ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚሁ ስደተኞች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሆነው መገኘታቸውን የስደተኞቹ ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
በተለያዩ ጊዜያት በየመን የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ተወካዮች ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ኣየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን ስደተኖችን ከየመን ለማውጣት ጥረት እያደረገ የሚገኘው አይ ኦ ኤም በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 1ሺ 220 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ሊመለሱ መቻላቸውንም አመልክቷል።
ይሁንና፣ ወደ ሃገሪቱ በመሰደድ ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር መጨመር ተጨማሪ ስጋት እንደፈጠረበት የስደተኛ ድርጅት አክሎ ገልጿል።
ከተመለሱት ስደተኞች መካከል አህመድ የሚል መጠሪያ የተሰጠውና የ21
አመት ስደተኛ ኢትዮጵያዊ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየመንግስት የተለያዩ የሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ተቀጣጣይ የሆኑ ነገሮች በአካላቸው ላይ እንዲፈስ ተደርጎ በእሳት ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞችን በአይኑ መመልከቱንም ወጣቱ አክሎ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በድንበር በኩል የሚደረግ ስደትን ለማስቀረት ቁጥጥርን ተግባራዊ ቢያደርግም፣ በርካታ ወጣቶች አሁንም ድረስ በመሰደድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ጎረቤት ኬንያን ጨምሮ ወደተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ የስደተኞች ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።
Source: Esat News
Source: Esat News
No comments:
Post a Comment