ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2008) በአለማችን ግንባር ቀደም የመገናኛ ብዙሃን አፋኝ ተብለው ከተፈረጁ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን በሃገሪቱ ያለው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትም እየተባባሰ መምጣቱን የተለያዩ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋማት ገለጡ። በየአመቱ በአለም ዙሪያ የሚከበረውን የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ ሪፖርታቸውን ያወጡት እነዚሁ ተቋማት በኢትዮጵያ 14 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ሃገሪቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መቀመጫ ብትሆንም ጋዜጠኞች መረጃ የማግኘት መብታቸውና ሃሳባቸው በነጻነት የመግለጽ መብታቸው ተገድቦ እንደሚገኝ ሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ የፍሪደም ሃውስ እና የድንበር የለሽ የሪፖርተሮች ቡድን (Reporters Without Borders) መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ለንባብ ባበቃው እትሙ አስነብቧል። ከ20 አመት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው የኢህአዴግ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት አዋጆችን በማውጣት የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን እያፈነ እንደሚገኝም ጋዜጣው ዘግቧል። በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት የማሳተሚያ ተቋማትን በብቸኝነት በመቆጣጠር ለህትመት በሚበቁ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ቁጥጥርን እያደረገ መሆኑንም አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል። ከአመታት በፊት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የሃገሪቱ የፀረ-ሽብርተኛ አዋጅ ህግም ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ መቀጠሉን ሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ በሪፖርቱ አስፍሯል። ግብፅ 23 ጋዜጠኞችን በማሰር፣ እንዲሁም ጎረቤት ኤርትራ 17 ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የመገናኛ ብዙሃን አፋኝ ሃገራት መሆናቸውንም የጋዜጠኞች ተከላካይ ድርጅት (Committee to Protect Journalist, CPJ) ገልጿል። የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ መልዕከትን ያስተላለፉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪ ሙን በበኩላቸው ሃገራት የመገናኛ ብዙሃንና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲያከብሩ አሳስበዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየአመቱ እንዲከበር የተወሰነው የዘንድሮው የፕሬስ ነጻነት ቀን በፊንላንድ መዲና ሄሊሲንኪ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን፣ በሙያቸው ግድያ የተፈጸመባቸውና ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችም ልዩ አክብሮት ተሰጥቷቸዋል።
No comments:
Post a Comment