Sunday, December 6, 2015

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ የሚነሳው ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ መሆን አለበት

def-thumbወያኔ አዘጋጀሁት የሚለውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አስመልክቶ የተነሳው ተቃውሞ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተለይም በተማሪዎች ዘንድ እንደገና ተቀስቅሷል። ባለፈው አመት ከዚህ ጋር ተያይዞ የፈሰሰው የበርካታ ንጹሀን ደም ገና ሳይደርቅ ካንዳንድ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁንም አዲስ ደም መፍሰስ ጀምሯል።
ሕዝብ በስፋት ሳይመክርበትና ፕላኑ በሚሸፍነው አካባቢ ሊያመጣ የሚችለውን ጥቅምም ሆነ ጉዳት ሳይወያይበት ስራ ላይ የሚውል ማስተር ፕላን መዘዙ ብዙ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የታወቀ ነው። በሰለጠኑ ሀገሮች የብዙ ሕዝብ ኑሮ ሊያቃውስ የሚችል ፕላን ቀርቶ አንዲት የመንደር ውስጥ መንገድ ለማስፋፋት እንኳን ህዝብ እንዲወያይበት ይደረጋል። ሕዝቡ መወያየት ብቻ ሳይሆን አይጠቅመኝም ካለ ምክንያቱን አቅርቦ እንዲሰረዝ ማድረግም ይችላል።
ሕዝቡ በጉዳዩ ላይ እንዲወያይ አለመደረጉ አንድ ነገር ሆኖ በማስተር ፕላኑ ግንባር ቀደም ተቃውሞ የተሰለፉት የኦሮሞ ተወላጆች በተለይ የኦሮሞ ወጣቶች ብቻ መሆናቸውና የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችን የጨመረ ሰፊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አለመሆኑ ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው። በሌላ አነጋገር  ከማስተር ፕላኑ ጋር የተያያዙ  ብሄረሰብ ዘለል የሆኑና ሁሉም የዴሞክራሲ ሀይል በጋራ ሊቆምላቸው የሚገባቸው ብዙ ጥያቄዎች ጎልተው መውጣት አልቻሉም።   በዚህ ጉዳይ ላይ አስፈላጊ የሆነ ሁሉን አቀፍ ውይይት በተገቢው መጠን አላደረግንም። በዚህም የተነሳ በጥያቄው ዙሪያ ግር የተሰኙና ዝርዝሩ ያልገባቸው ቅን ዜጎች በጣም ብዙ ናቸው። ብዙ ሰዎች አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ እንደመሆኗ መጠን ማስተር ፕላኑ አስፈላጊ እንደሆነና ተቃውሞውም ተገቢ እንዳልሆነ ያስባሉ።  እንደውም የኦሮሞ ብሔርተኞች ያነሱት ጥያቄ ጭፍን የግዛት ባለቤትነት ጥያቄ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህን ተቃውሞ በማስተባበር ላይ ያሉት የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ሌላው የብሔረሰብ ክፍል ጥያቄያቸውን በመደገፍ እንዲቀላቀላቸው ተገቢ ጥረት ሲያደርጉም አይታይም። ሰፊና ብሔረሰብ ዘለል ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ በመጨረሻው ውጤት ላይ ያለውን እንድምታ በቅጡ ያጤኑት አይመስልም።
የወያኔው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሹማምንት ይህን ማስተር ፕላን ስራ ላይ ካልዋለ ብለው የሚጣደፉበት አልፎም ጥያቄ ያነሳውን ሁሉ ካለርሕራሄ የሚጨፈጭፉበት ዋነኛ ምክንያት ለሁላችንም ግልጽ ሊሆን ይገባል። የወያኔ ባለስልጣናትና ሎሌዎቻቸው ቅጽበታዊ ሚሊዮነርና ሀብታም ቱጃር ያደረጋቸው የአዲስ አበባ ውስጥና ዙሪያ መሬት መሆኑ ይታወቃል። የወያኔው ሹማምንት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የገበሬ ቤተሰቦችን በማፈናቀል በተቀራመቱት መሬት ከብረው በእንደኛው አለም ሀገራት ላይ የማይታይ የቅንጦት ኑሮ ላይ ናቸው። ይህ የዘረፋ ልምዳቸው ደግሞ ብዙ መሬት ቢዘርፉና ቢሸጡ የራሳቸውና የዘመዶቻቸው ሀብት የት ሊደርስ እንደሚችል አሳይቷቸዋል።  ስለዚህ ብዙ መሬት መዝረፍ ይፈልጋሉ። የሚዘረፈው መሬት የትና የት ድረስ ሊሆን እንደሚችልም ያውቃሉ። የጥድፊያቸውና በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የሚያሳዩት ጭካኔ ሚስጥርም ይኸው ነው።
ይህን የግፍና የማናለብኝነት ዝርፊያ ዘርና ብሔረሰብ ሳንለይ ልንቃወመው፤ብሎም በጽኑ ልንታገለው ይገባል። የኦሮሞ ተወላጆች የተለየ ጥያቄ ብቻ ሊሆን አይገባም። ይህ ጥያቄ የኦሮሞ ጥያቄ ብቻ መስሎ የሚታያቸው ኦሮሞዎችም ይህ አስተሳሰብ የተሳሳተ እና ሊታረም የሚገባው እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥያቄው ውጤት ወደሚያመጣ ትግል የሚያድገው የሁላችንም ሀገራዊ ጥያቄ ሲሆን ብቻ ነው። ጥያቄውን የብሔር ወገንተኝነት ጥያቄ እንዲሆን ማድረግ የሚጠቅመው ዘራፊውንና አንዱን ብሔረሰብ በሌላው ላይ በመቀስቀስ ፤ በማናቆርና በማስፈራራት ለመቀጠል የወሰነውን ወያኔን ብቻ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሞ ወጣቶች እየተደረገ ያለው ተቃውሞ ሐገራዊ ፤ የጸረ ህዝብና የወያኔ ዝርፊያ ፕሮጀክትን እንደመቃወም ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ተቃውሞ እንደሆነ ይገነዘባል። በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ድምጻቸውን በሚያሰሙ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ኦሮሞዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋም በጥብቅ ያወግዛል። በጋራ ትግል በምንመሰርታት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያም እነዚህ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸውም በጽኑ ያምናል። መላው የዴሞክራሲና የፍትሕ ወዳጅ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህን ህዝብ ያላሳተፈ ፕላንና የዝርፊያ ፕሮጀክት እንዲቃወምና በትግሉ እንዲሳተፍ በዚያውም አንድነታችንን እንዲያጠናክር ጥሪውን ያቀርባል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ዴሞክራሲና የሕዝብ ወሳኝነት ባልተረጋገጠበት ስርዓት ውስጥ በሕዝብና በሐገር ልማት ስም የሚካሔድ ፕሮጀክት ሁሉ ሕግ የማይገዛቸው ዘራፊዎችን ከለላ ለመስጠት የሚደረግ ዝግጅት ነው ብሎ ያምናል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ 
አንድነት ኃይል ነው

No comments: