የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሆኑት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው ትናንት መጋቢት 21 አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው 28 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡ ፖሊስ እነ ብርሃኑ ተክለያሬድን ‹‹ለግንቦት 7 አባላትን መልምለው ወደ ኤርትራ በመላክና ቡድኑን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ተይዘዋል›› ብሏል፡፡
ጠበቃው እነ ብርሃኑ ተ/ክለያሬድ ለግንቦት ሰባት ሲመለምሉም ሆነ አባል ሲሆኑ የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ፖሊስ ‹‹ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምመረምራቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ሌሎች የምንይዛቸው ግብረ አበሮችም አሉ፡፡ መረጃ ያጠፉብናል፡፡›› በሚል ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ 28 ቀን ተፈቅዶለታል፡፡ ሚያዚያ 19 ፍርድ ቤትይቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ፖሊስ ሌሎች ሰዎች ይዘውት የተነሱትን መሳሪያ በማሳየትም እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ እንደነበር ለማሳየት በመረጃነት አቅርቧል፡፡ ጠበቃው በበኩላቸው ‹‹የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምርመራ ለማድረግና መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጠርጣዎቹን ማሰር ተገቢ አልነበረም፡፡ ሌሎች ሰዎች የያዙትን መረጃ እነሱን ለመክሰስ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡›› ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ የታሰረበት ቤት መብራት ስለማይጠፋ አይኑ ላይ ለከፍተኛ ችግር እንዳደረሰበት ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ለ15 ደቂቃ ፀኃይ እንዲሞቁ ከሚፈቀድላቸው ውጭ ወደ ከታሰሩበት ቤት ውጭ መውጣት እንደማይፈቀድላቸውና ቤተሰቦቻቸውም እንዲጠይቋቸው እየተደረገ አለመሆኑን በቅሬታ አቅርበዋል፡፡
No comments:
Post a Comment