Thursday, March 26, 2015

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የትብብሩን ሰልፍ እውቅና ነፈገ

• ‹‹ህገ መንግስታዊ መብታችን ከቦሊ ቦል ስፖርት በታች ሆኗል›› አቶ አዲሱ ጌታነህ
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር እሁድ መጋቢት 20/2007 ዓ.ም የ9ኙን ፓርቲዎች ትብብር በባህርዳር ከተማ ሊያደርገው የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና እንዳልሰጠውና ሰልፉን ማድረግ እንደማይቻል የትብብሩ አባልና የባህርዳር ሰልፍን አስተባባሪ ለሆነው ሰማያዊ ፓርቲ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
አስተዳደሩ ለሰልፉ እውቅና እንዳልሰጠ የገለፀው ‹‹ሁለተኛውን አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር እያስተናገድን በመሆኑ›› እና ‹‹የህዳሴውን ግድብ የቦንድ ሳምንት በከተማችን በየማዕከሉ እየሰራን በመሆኑ›› ሰልፉን ለመጠበቅ የሚያስችል የፀጥታ ኃይል የለም በሚል ነው፡፡
የሰልፉ አስተባባሪዎች ወደ ከተማው ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በተደጋጋሚ ባቀኑበት ወቅት አመራሮቹ ሲጠፉ እንደቆዩ የገለፀው የሰልፉ አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጌታነህ በመጨረሻ ሁለቱን ጥቃቅንና የፀጥታ ኃይል ለመላክ የማያግዱ ጉዳዮችን ጠቅሰው ሰልፉ እንዳይደረግ ወስነዋል ብሏል፡፡
የምርጫ ወቅት እንደመሆኑ ለሰላማዊ ሰልፉ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ ነበር ያለው አቶ አዲሱ ‹‹በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል በሚካሄድ ስፖርት ይህ ነው የሚባል የፀጥታ ኃይል አያስፈልግም፡፡ ቦንድም ቢሆን በባንኮች በኩል ነው የሚሸጠው፡፡ ያም ሆኖ ባህርዳር የክልሉ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፖሊስና መከላከያ አለ፡፡ በመሆኑም ምንም አይነት የፀጥታ ኃይል እጥረት የለም፡፡›› ሲል ውሳኔው ትክክል አለመሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
አቶ አዲሱ አክሎም ‹‹በእነዚህ ጥቃቅን ምክንያቶች ሰልፉን ሆን ብለው ማገድ ፈልገዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስፖርት ውድድር ተጠቅሶ ሰልፍ እንዳይደረግ መወሰኑ ህገ መንግስታዊ መብታችንን ከቦሊ ቦል ስፖርት በታች እንዳደረጉት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡›› ብሎአል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትብብሩ መጋቢት 20/2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ጊዜ ሰልፍ ለማድረግ ባቀደባቸው 14 ከተሞች የሚደረገው ሰልፍ እንደተጠበቀ ሲሆን የአዲስ አበባው ካሳንቺስ ከሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ተነስቶ በአራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ሸዋ ዳቦና ግንፍሌ አድርጎ ወደ ቤልየር ሜዳ እንደሚያቀና ታውቋል፡፡

No comments: