-ኢዴፓ ድርጊቱ ካልቆመ ራሴን ከምርጫ አገላለሁ አለ
በመጪው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በምርጫ ቅስቀሳ መልዕክታቸው ላይ የቅድሚያ ምርመራ (ሳንሱር) እየተደረገ ነው ሲሉ ከሰሱ፡፡
ኢዴፓ ቅድመ ምርመራው ከተደገመ ራሴን ከምርጫ አገላለሁ ብሏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚዘልቀው የምርጫ ቅስቀሳና ዘመቻ የጊዜ ሰሌዳ የተለያዩ መልዕክቶቻቸውን በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚዲያ ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ከለላውን በመጣስ የቅድመ ምርመራ በማድረግ መልዕክቶቻችንን አናስተላልፍም አሉን በማለት ፓርቲዎቹ ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29(3) (ሀ) ላይ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መጋቢት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ቅስቀሳዎቹ እንዳይተላለፉ በመደረጉ፣ በምርጫ ተሳትፎው ላይ ትልቅ ተግዳሮት እንደፈጠረበት ገልጿል፡፡
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) እንዳይተላለፍ የተከለከለው የቅስቀሳ ፕሮግራም ይዘት ሕግን የተፃረረ አለመሆኑንም አስምሮበታል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱ ድርጊት ግን ሕግን የሚፃረርና በሕገ መንግሥቱ የተከለከለውን የቅድሚያ ምርመራ ያለመደረግ መብት የሚጥስ ሆኖ እንዳገኘው ፓርቲው አስገንዝቧል፡፡
‹‹በዘንድሮው ምርጫ የመወዳደሪያ ሜዳው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየጠበበ መምጣቱን የሚያሳይ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲል ያሰፈረው የኢዴፓ መግለጫ፣ መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፋናና ለኢብኮ የላከው የቅስቀሳ መልዕክት እንዲስተካከል የቀረበው ጥያቄ አሳማኝ ምክንያት እንዳላካተተ አመልክቷል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር እንዲሁም ኢብኮ ለኢዴፓ በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹በአገሪቱ አሉ የሚባሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሁሉ የኢሕአዴግ ሥልጣን መጠቀሚያና መጠበቂያ ብቻ እንዲሆኑ በማድረጉ፣ ተቋማቱ በገለልተኝነት እንዳይሠሩና ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ነፃነት ብቻ ሳይሆን አቅምም እንዳይኖራቸው አድርጓል፤›› በማለት ኢዴፓ መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከሩ ሕገ መንግሥቱን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን፣ የምርጫ ሕጉን፣ የመገናኛ ብዙኃን ሕጉን፣ እንዲሁም የተቋማቸውን ኤዲቶሪያል ፖሊሲና ሌሎች ሕጎችን የሚጥስ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በተለይ በኢብኮ የምርጫ ዴስክ ሰብሳቢ በአቶ ሰለሞን ተስፋዬ መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣው የኢብኮ ደብዳቤ፣ ‹‹ይህ መልዕክት በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ የዴሞክራሲ ተቋማትን ሁሉ ህልውና የሚክድና ተግባራቸውን የሚያንቋሽሽ፣ ሕዝቡ በተቋማቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ መልዕክት በመሆኑና ሕገ መንግሥቱን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉን አንቀጽ 29(1) እንዲሁም የድርጅታችንን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚፃረር ሆኖ አግኝተነዋል፤›› በማለት ገልጿል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 29(1) ማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፣ ግንባር፣ ጥምረት፣ ንቅናቄ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፣ ኃላፊ፣ ዕጩ፣ አባል፣ ወኪልና ተጠሪ የምርጫ ዘመቻውን ሰላም የሚያናጋ ወይም ግጭት የሚቆሰቁስ ወይም ስም የሚያጠፋ ወይም አመፅ የሚጋብዝ ወይም ሥጋት የሚፈጥር ንግግር ካደረገ የሥነ ምግባር ጥሰት እንደፈጸመ እንደሚቆጠር ይደነግጋል፡፡
ኢዴፓ በመግለጫው፣ ‹‹ለዴሞክራሲ ተቋማት ያለንን ተቆርቋሪነት ኢሕአዴግ በነፃነት እንዳይሠሩ እያደረጋቸው መሆኑን መግለጽና ተቋማቱ ለተቋቋሙለት ዓላማ ግብ መምታት ኢሕአዴግ እንቅፋት መሆኑን መግለጽን፣ እንዴት የተቋማቱን ስም ማጥፋት እንደሆነ ሊገባን አልቻለም፤›› ብሏል፡፡
ኢዴፓ ይህ የመብት ጥሰት የማይቆም ከሆነ ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ ከምርጫ ተሳትፎው ራሱን ሊያገል እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡ የኢዴፓ የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፣ ‹‹ሐሳቦቻችንን በነፃነት ካልገለጽን ተሳትፎአችን የይስሙላ ስለሚሆን ድርጊቶቹ የሚቀጥሉ ከሆነ በምርጫው መሳተፋችን ከማጀብ ስለማይለይ ራሳችንን ከምርጫው ልናገል እንችላለን፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ዋሲሁን ፋናና ኢብኮ አላስተናግድም ያሉት ጽሑፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስተናገዱ ከክልከላው ጀርባ የግለሰቦች ፍላጎት ይኖር ይሆን እንዴ ብለው እንዲጠራጠሩ እንዳደረጋቸውም አመልክተዋል፡፡ ጉዳያቸውን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቅርበው በችግሩ ላይ ስምምነት መፈጠሩን ግን እንደ ጥሩ ምልክት ወስደውታል፡፡
በተመሳሳይ ኢብኮንና ፋናን በቅድሚያ ምርመራ ከከሰሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊና መድረክም ይገኛሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ እስካሁን ፓርቲው ስምንት የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች እንደተሰረዘበት ገልጸዋል፡፡ ፓርቲያቸው ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ባሰፈረው የቅድሚያ ምርመራ ክልከላ ላይ እንደማይደራደር ያስታወቁት አቶ ዮናታን እንደ ኢብኮ፣ አዲስ ቲቪና ኤፍ ኤም 96.3 ሬዲዮ ያሉ ተቋማት መልዕክቶቹን እንዲያስተካክሉ መጠየቃቸው ሕገወጥ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና በጋዜጦች ላይ ግን የከፋ ችግር እስካሁን እንዳልገጠማቸው ገልጸዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢብኮ እንዲተላለፍ የላከው የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት የጎሳ ፌዴራሊዝም ለግጭት መንስዔ ነው ማለቱ፣ አንዱን ብሔር ከሌላ ብሔር የሚያጋጭ ነው በሚል ውድቅ እንደተደረገበት መግለጹ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት/መንግሥት›› የሚለውን አጠራር እንዲያስተካክል ጥያቄ እንደቀረበለት ገልጿል፡፡ ከዚህ አስቀድሞ ኢሕአዴግ ‹‹ፖሊስን፣ ሚዲያውን፣ መከላከያ ሠራዊቱንና ደኅንነቱን ሰማያዊና ሌሎች ፓርቲዎችን ለማጥፋት ሲጠቀምባቸው ቆይቷል››፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤትና ሌሎችም ተቋማት ሕግ አክብረው አይሠሩም››፣ የሚሉትን ጨምሮ ሌሎች መልዕክቶች የአገሪቱን ሕጎች የሚፃረሩ በመሆኑ እንደማያስተናግድ ኢብኮ ለሰማያዊ በጻፈው ደብዳቤ ገልጾ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ይዘቶች የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉና የሌላ ፓርቲን ስም የሚያጎድፉ በመሆናቸው፣ ለውጥ ካልተደረገ እንደማያስተናግድ ገልጾ ለሰማያዊ ፓርቲ ደብዳቤ ጽፏል፡፡
መድረክ በበኩሉ የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶቹ ላይ በተመሳሳይ የቅድሚያ ምርመራ እንደተደረገበት ይገልጻል፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድና የፍትሕ አካላት ነፃና ገለልተኛ አይደሉም በማለት ያቀረባቸው መልዕክቶች ውድቅ እንደተደረጉበት፣ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ገልጸዋል፡፡
ኢብኮ፣ ፋናና አዲስ ኤፍ ኤም እነዚህ ተቋማትና የመንግሥት ሚዲያን ነፃነት አስመልክቶ መድረክ ያቀረበው ትችት እንዲወጣ መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡ መድረክ የፖለቲካ እስረኞች እንዳይኖሩ ያደርጋል በማለት ያቀረበው አማራጭም አሁን የፖለቲካ እስረኛ እንዳለ የሚያመለክት ስለሆነ አናስተናግድም እንደተባሉ አመልክተዋል፡፡ የኦሮሚያ መገናኛ ብዙኃንም ገዥው ፓርቲን ያለመረጃ እየተቻችሁ ነው በሚል መልዕክታቸውን ሳያስተላልፉ እንደቀሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሥርዓቱን አትንኩ የሚል አዝማሚያ ነው ያለው፡፡ ሥርዓቱ ላይ የሚነካ ነገር ከሌለ የእኛ ጥቅም ምንድነው?›› ሲሉም አቶ ጥላሁን ጠይቀዋል፡፡
ኢዴፓ፣ ሰማያዊና መድረክን ጨምሮ በቅድሚያ ምርመራ መገናኛ ብዙኃኑን የሚከሱ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውንና ቦርዱ ምላሽ እንዳልሰጠም ተችተዋል፡፡ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ፣ የኢዴፓን ቅሬታ ገና ያልተመለከቱት ቢሆንም በሰማያዊና በመድረክ ላይ በሕጉ መሠረት ማስተካከያ አድርጉ ማለት ቅድሚያ ምርመራ ተደረገ የሚያስብል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎቹ ጋር ባደረጉት የጋራ ውይይት አሠራሮቹ ላይ ስምምነት ተደርጓል፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች ጉዳይ ከዚያ ያፈነገጠ ነው፡፡ መልዕክታችን ትክክል ስለሆነ ሕጉን አይፃረርም የሚል አቋም ወስደዋል፡፡ ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃኑ ደግሞ ኃላፊነት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፌስቡክ ይፋዊ ገጹ ላይ አንዳንድ ፓርቲዎች የተከለከሉ ይዘቶችን በምርጫ ቅስቀሳ እንደሚጠቀሙ የጠቀሰ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል የምርጫ ቦርድን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ የፍርድ ቤቶችንና የፍትሕ አካላትን ገለልተኝነትና ነፃነት ማጣጣል፣ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ የሚያጋጩ፣ አመፅ የሚቀሰቅሱ፣ ስም የሚያጠፉ እንደሚገኙበት ጠቅሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ከመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ጥቂት ፓርቲዎች ሕገወጥ የቅስቀሳ ይዘት ማምጣታቸውን ያቁሙ ብለዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሕግ ባለሙያ ግን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የቅድመ ምርመራ ክልከላን የሚፃረሩ ሕጎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የሕጎቹ ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ጥያቄ ሳያነሱ ሕገ መንግሥቱን ብቻ በመጥቀስ መከራከር፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የራሱ ችግሮች አሉት ብለዋል፡፡
Source: ethiopianreporter
Source: ethiopianreporter
No comments:
Post a Comment