Thursday, March 19, 2015

136 መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መቱ

 ‹‹ከአሁን በኋላ ለመምህራን ማህበርና ለአልማ አንከፍልም!››
በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 136 መምህራን ዛሬ መጋቢት 10/2007 ዓ.ም የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለፁ፡፡ መምህራን ላይ እየተፈፀመ ያለውን የአስተዳደር በደል ተከትሎ 92 መምህራን ‹‹እኛ በደል እየደረሰብን ቢሆን መምህራን ማህበር ችግራችን እየፈታልን ባለመሆኑ ከአሁን በኋላ አባል እንዳልሆንን እንዲታወቅ፣ በየወሩ ከደመወዛችን እንዳይቆረጥብን›› በሚል ፊርማ አስገብተዋል፡፡ ከመምህራን ማህበር በተጨማሪ በየወሩ ከደመወዛቸው ለአልማ የሚቆረጠው ገንዘብም እንዲቆም መምህራኑ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ባለፉት የመምህራን ስልጠናዎች የምስራቅ ጎጃም መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበት ማሳሰቢያ ተሰጥቶ እንደነበር የገለጹት መምህራኑ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ የሆነው አቶ ዘላለም ጌታነህ የወረዳው መምህራን ማህበር ፀኃፊ ከሆኑ በኋላ ጫናዎች እንደበዙባቸው ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና መምህራን ማህበር ፅ/ቤት የሚሰራው አቶ ዘላለም ዕጩ መሆኑ ከታወቀ በኋላ መምህራኑ አራት ጊዜ እንዲፈርሙ የተጠየቁ ሲሆን ይህም አቶ ዘላለም ለመምህራን ማህበሩ እያደረገ ባለው አስተዋጽኦና በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት እየተፈፀመ ያለ በደል ነው ብለዋል፡፡
የመምህራኑን ፊርማ ተከትሎም መጋቢት 9/2007 ዓ.ም የወረዳው ምክር ቤት 18 ያህል መምህራንን ብቻ ጠርቶ ‹‹እንወያይ›› ባለበት ወቅት መምህራኑ ‹‹ካወያያችሁ ሁላችንም አወያዩን እንጅ እኛን ብቻ ነጥላችሁ ልታወያዩን አይገባም፡፡›› በማለታቸው ምክር ቤቱና መምህራኑ ሳይግባቡ ተለያይተዋል፡፡ መምህራኑ በትናንትናው ዕለት ስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ተጠርተው ‹‹እንወያይ›› ቢባሉም በዝምታ ተቃውሟቸውን በመግለፃቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ገሰሰ ‹‹አንወያይም ብላችሁ አምጻችኋል፡፡ ስለዚህ ነገ ስራ እንዳትገቡ፡፡ ስራ ገብታችሁ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሰው ነፍስ ቢጠፋ ተጠያቂዎቹ እናንተ ናችሁ፡፡›› በሚል እንደዛቱባቸው መምህራኑ ገልጸዋል፡፡ የወረዳው የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረአዲስ ሙሉሰው በበኩላቸው ‹‹ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ለአንድ ወርም መግባት የለባቸውም›› በሚል መምህራኑ ላይ ቅጣት እንዲወሰን መጠየቃቸው ተገልጾአል፡፡
መምህራኑም ለምክር ቤቱ ‹‹በቃል የነገራችሁንን ውሳኔ በጽሁፍ ስጡን›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ውሳኔው በጸሁፍ ሊሰጣቸው እንዳልቻለና የወረዳውን ባለስልጣናት ውሳኔ የሰሙት 136 መምህራን ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የስራ ማቆም አድማው ዛሬ ጠዋት ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎች 3፡20 ላይ ክፍል ጥለው በመውጣት መምህራኑን መደገፋቸው ተገልጾአል፡፡
ደብረወርቅ የሰማያዊ ፓር ሊቀመንበር የኢ/ር ይልቃል ጌትነት የትውልድ ቦታ መሆኑን ተከትሎ የብአዴን ካድሬዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

No comments: