Saturday, March 28, 2015

የ‹‹ነፃነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› ዝግጅትና ቅስቀሳ ተጠንክሮ አምሽቷል


መጋቢት 20/2007 ዓ.ም ለሚደረገው የ‹‹ነፃነት የፍትሓዊ ምርጫ›› ቅስቀሳ ማምሻውን በአዲስ አበባና በሌሎቹም ከተሞች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በደብረታቦር ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 10 ሰዓት ቅስቀሳው በሰላም እንደተካሄደ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ካድሬዎች የሞንታርቮውን ባለቤት አስፈራርተው ቀምተውታል፡፡ የሞንታርቮው ባለቤት ‹‹እንገድልሃለን›› ብለውኛል ብሎ እንደወሰደባቸው አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በደሴ ከተማ ቅስቀሳው በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ በደሴ ከተማ የስብሰባው አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ በቅስቀሳው ወቅትም ህዝቡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገልን ነው ሲሉ አስተባባሪዎቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በነገው ዕለትም ጠዋት 3 ሰዓት ጀምሮም በተለምዶ አራዳ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ተነስቶ ወቴ ስታዲየም እንደሚያቀና ገልጸዋል፡፡ በሌላ ዜና በአርባ ምንጭ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ቅስቀሳው በተሳካ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝ የሰልፉ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በጅማ ከተማ የኦህዴድ ካድሬዎች የነገውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማደናቀፍ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ከታማኝ ምንጭ መረጃ እንደደረሳቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ወጣቶችን በ1ለ5 አደራጅተው ሰልፉን ለማደናቀፍ እየሰሩ እንደሆነ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ለነገው ሰላማዊ ሰልፍ በሰማያዊፓርቲ ጽ/ቤቶች የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

No comments: