Saturday, March 28, 2015

የኢህአዴግ መርዛማ ዘር በቅሎ ፍሬ አፈራለት

ባለፈው ሁለት አመት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ላይ ጥሩ ለውጥ ያየንበት ጊዜ እንደሆነ ሁላችንንም የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ ተጫዋቾቹ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ የተቀላቀለበትን ማሊያ አድርገው ሜዳ ሲገቡ ስመለከት ደስታን አገኝ ነበር ምንም እንኳ በዚህ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የቆየ ታሪካዊ ባንዲራችን ላይ የሆነ ያለቦታው የተቀመጠ ያአንድ ክልል ባህላዊ ምግብ ማለትም አንባሻ ምስል ተለጥፎበት ውበቱን ቢቀንሰውም ያን ያህል አላሳሰበኝም ነበር፡፡ ከዚያ ይልቅ እጅግ ያሳሰበኝ ነገር ለአገራችን ብሔራዊ መዝሙርና ለሀገራችን ያለን ብሄራዊ ስሜት ማነስ ነው፡፡ ታዝባችሁ ከሆነ ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ በገቡ ቁጥር የሀገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር ይዘመራል፡፡ የሌሎች አገራት ተጫዋቾቹ የሀገራቸውን ብሄራዊ መዝሙር በስሜት ሲዘምሩት ተመልክቼ ቀናሁ፡፡ የኛዎቹ ተጫዋቾች ግን በካሜራ ፊት ተገትረው ከንፈራቸውን እንኳ ማንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ከንፈራቸውን ካንቀሳቀሱም ለመዝሙር ሳይሆን በሲዲ በሚንቆረቆረው መዝሙር መሀል የራሳቸውን ወሬ ለማስገባት ነበር፡፡ ለመዝሙር ሳይሆን ለፎቶ የቆሙ እስኪመስሉ ነው፡፡ ለምን ቢባል መዝሙሩን አያውቁትም፡፡ ለምን ቢባል ብሄራዊ መዝሙር ከሀገር ጋር ያለውን ቁርኝነት አያውቁትማ ይህ አጋጣሚ የጋራ ስሜት ብሄራዊ ክብር የሚሉት ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀዘቀዙና እየጠፉ መምጣታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ምን አልባት የደቡብ ኢትዮጵያ መዝሙርን ጠብቀው ይሆናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የአማራን መዝሙር ካልሆነ ሌላ ስሜት አይሰጣቸው ይሆናል፡፡ ሌሎቹ ከኦሮሚያ፣ ሌሎቹም ከጋንቤላ፣ አልያም ከቤንሻንጉል ወይም ደግሞ ከትግራይ ያልሆነ መዝሙር ምናቸውም መስሎ ላይታያቸው ይችል ይሆናል፡፡ እነ ሀይሌ፣ ደራርቱ ድል አድርገው ሲያበቁ በከፍተኛ የሀገር ወዳድ ስሜት ባንድራ አቅፈው ሲዘምሩና ሲያለቅሱ የተመለከተ አይናችን በአሁኖቹ ትውልዶች ላይ እንዲህ ባንዴ ወርዶ መመልከት እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጎሳ፣ በቋንቋ ተከፋፍሎ በወያኔ ኢህአዴግ መንግስት የተዘራው ዘር ፍሬ ማፍራቱን ነው፡፡

የኢህአዴግ አላማ ትውዱን ራዕይ አልባ ማድረግ የሀገር ስሜት እንዳይኖረው ማድረግ በሀገሩ እንዳይኮራ ማድረግ እኔ ኦሮሞ እንጂ ኢትየጵያዊነት አይገባኝም፣ ጋምቤላዊ ካልሆነ ኢትዮጵያ ምንድነች፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ሀረሪ፣ ጉራጌ እንጂ ኢትዮጵያ ምትሏት ምኔ ነች የሚል ትውልድ ማፍራት ነው፡፡ እናም ተሳክቶለታል፡፡

ይህ አሁን የበቀለው ዘር ፍሬ እያፈራ ቢሆንም በጣም ስር ሰዶ መሰረቱን ከማጠናከሩ በፊት መድሃኒት ሊበጅለት ይገባል፡፡ መድሃኒቱ ደግሞ የኛው ትግል ነው፡፡ ተባብረን ሀገራችንን እናድን፡፡
Misrak Tesfay Dawit
Schluchtern

No comments: