Saturday, March 21, 2015

ተቃዋሚዎች በምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰአት አጠቃቀም ተወቀሱ

  • ችግሩን የፈጠረው ሳንሱር ነው ብለዋል
  • “ኢህአዴግ የተመደበለትን ሰዓት በአግባቡ እየተጠቀመ ነው”
  ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ የተመደበላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ  በአግባቡ እየተጠቀሙ አይደለም ያለው የብሮድካስት ባለስልጣን፤ ኢህአዴግ ግን ከተመደበለት የሚዲያ ሰዓት 95 በመቶውን ተጠቅሞበታል ብሏል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው፣ ሳንሱር እየተደረግን ተቸግረን ነው እንጂ ወደ ቅስቀሳ የገባነው የተመደበልንን የአየር ሰዓትም ሆነ የጋዜጣ አምድ ለመጠቀም በቂ ዝግጅት አድርገን ነው ብለዋል - ለአዲስ አድማስ፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፤ የሁለት ሣምንት የፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀምን ገምግሞ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በአጠቃላይ በምርጫው ተወዳዳሪ የሆኑት ፓርቲዎች ከተመደበላቸው 90 ሰአት የሬዲዮና የቴሌቪዥን የአየር ጊዜ ውስጥ 57 ሠአት ብቻ መጠቀማቸውን አስታውቋል፡፡ ከጠቅላላው የአየር ሰዓት ውስጥም ከ64 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሳይጠቀሙበት እንደቀሩ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ መገናኛ ብዙሃኑ ለፓርቲዎቹ እየሰጡ ያሉት አገልግሎት መልካም የሚባል እንደሆነ የጠቆመው ባለስልጣኑ፤ በቀረፃ ስቱዲዮ በኩል በቂ ትብብር እንደሌለ በመግለፅ ሁኔታው  እንዲሻሻል አሳስቧል፡፡
ፓርቲዎቹ የተመደበላቸውን የቅስቀሳ ጊዜ ለምን በአግባቡ እንዳልተጠቀሙ ያብራራው ሪፖርቱ፤ የአቅምና ክህሎት ማነስ፣ በተፈለገው ጊዜ ስራቸውን አጠናቀው አለማቅረብ እንዲሁም የሚያዘጋጁት ፕሮግራም የይዘት ችግር ያለበት መሆን … እንደ ድክመት ጠቅሷል፡፡
በሁለት ሳምንት ውስጥ የቅስቀሳ መልዕክት በሚዲያ መተላለፍ የማይችል በመሆኑ እንዲያስተካክሉ የተነገራቸው ፓርቲዎች 10 ቢሆኑም መልዕክታቸውን አስተካክለው በማምጣት የተመደበላቸውን ጊዜ የተጠቀሙት ግን ሁለት ፓርቲዎች ብቻ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ኢህአዴግ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ለቴሌቪዥን የተመደበለትን 5 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ሙሉ ለሙሉ መጠቀሙን የገለፀው ሪፖርቱ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጠቃላይ ከተመደበላቸው 4 ሰአት ከ45 ደቂቃ ውስጥ የተጠቀሙት  ግማሽ ያህሉን ወይም 2 ሰዓት ከ33 ደቂቃ ብቻ ነው ብሏል፡፡
በሬዲዮ ከተመደበው የአየር ሰአት ኢህአዴግ ከ28 ሰአት ከ45 ደቂቃ ውስጥ 28 ሰአት ከ19 ደቂቃውን የተጠቀመ ሲሆን ተቃዋሚዎች ከተመደበላቸው 25 ሰአት ከ50 ደቂቃ ውስጥ መጠቀም የቻሉት 9 ሰአት ከ34 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ የግምገማው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ኢህአዴግ በአጠቃላይ ከተመደበለት የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ በሁለት ሳምንት ውስጥ 95 በመቶውን ተጠቅሟል ብሏል የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን፡፡
ለምን የተመደበላቸው የቅስቀሳ የሚዲያ መድረክ በአግባቡ እንዳልተጠቀሙ ከአዲስ አድማስ  ጥያቄ የቀረበላቸው የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢዴፓ የተመደበለትን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ሙሉ ለሙሉ እየተጠቀመ መሆኑን ጠቅሰው ሪፖርቱ የፓርቲያቸውን የሚዲያ አጠቃቀም በተመለከተ የገለፀው የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“እኛ የተሰጠንን የአየር ጊዜና የጋዜጣ አምድ ከአማርኛ በተጨማሪ በትግሪኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች ሁሉ መልዕክቶቻችንን በማቅረብ እየተሳተፍን ነው” ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ ኢዴፓ  የተሰጠውን የሚዲያ መድረክ ሁሉ በአግባቡ አሟጦ እየተጠቀመ ነው ብለዋል፡፡ ገዥው ፓርቲና ሚዲያው ፕሮግራም የላቸውም የሚል ክስ መሰንዘራቸውን የተቃወሙት አቶ ወንድወሰን ኢዴፓ በሚገባ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ወደ ምርጫው በተደራጀ አኳኋን የገባ ፓርቲ ነው ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የአየር ሰዓት አጠቃቀሙ ሲመዘንም ኢህአዴግን ለብቻው መዝኖ ተቃዋሚዎችን በጅምላ መመዘንም አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ለሚዲያዎች የምንልካቸው የቅስቀሳ መልዕክቶች በተደጋጋሚ ተመላሽ ይደረጉብናል” የሚሉት የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው፤ ፓርቲው የተሰጠውን የአየር ሰዓትና ጋዜጣ አምድ ድልድል ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚያስችል የቅስቀሳ ፓኬጅ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “እኛ የምናውቀው እስካሁን የተሰጠንን የሚዲያ መድረክ በአግባቡ መጠቀማችንን ነው” ያሉት ኃላፊው፤ “የምንልካቸው ፅሁፎችና ፕሮግራሞች ከሁለትና እና ከሶስት ጊዜ በላይ ተመላሽ እየተደረገ እንድናስተካክል መገደዳችን በሚዲያ አጠቃቀሙ ከገጠሙን ተግዳሮቶች ዋነኛው ነው” ብለዋል፡፡
የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ ከአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሳንሱር ችግር ከመጋፈጣችን በቀር ፓርቲያችን ከዋና ዋና የሚዲያ ተቋማት በተጨማሪም የተለያዩ የክልል ሚዲያዎችን በመጠቀም በየብሄረሰቡ ቋንቋ ጭምር የቅስቀሳ ስራውን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
“መልዕክቶቻችንን በአግባቡ ለመራጩ እንድናደርስ ተገቢ ያልሆነ ሳንሱር እየተደረገብን ተቸግረናል” ያሉት ኃላፊው ፓርቲው እነዚህን ተግዳሮቶች ሁሉ ተቋቁሞ የተሰጠውን የሚዲያ መድረክ በሙሉ አሟጦ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንዳለና ለወደፊት ከመጠቀምም ወደ ኋላ እንደማይል ተናግረዋል፡፡  
Source: addisadmassnews

No comments: