እውነት ነው “ምርጫ” ዲሞክራሲ በሰፈነበት አገር ከጦር መሳርያ በላይ ይፈራል፣ ይከበራልም። “ፍትሃዊ ምርጫ” ትልቅ ሰላማዊና ህጋዊ የትግል መስክ ነው። እርግጥ ነው ህዝብ መብቱ መከበሩን የሚያረጋግጥበት አይነተኛ ዜዴ“ህጋዊ ምርጫ” ነው። ህዝብ በምርጫ የሰጠው ድምጽ ሲከበርለት መብቱ ሊከበር እንደሚችል ማሳያ ምልክት ነው።
“ምርጫ” በሃገሪቱ የሚካሄደው አንድ ድርጅት ለስልጣን የሚበቃበትንና ስልጣን የሚያራዝምበትን አንድ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ እንዲካሄድ አድርጎ ስልጣን ለመጨበጥም ሆነ ስልጣን ለማስያዝ አይደለም። በዚያች ሃገር የሚካሄዱ ሁሉም ምርጫዎች ዲሞክራሲያዊ እንዲሆኑ ነው እንጂ። በአገሪቱ በስልጣን ላይ የሚቀመጠው አካል ሁልጊዜም በህዝብ ይሁንታ በሰላማዊና ህጋዊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲመነጭ ለማድረግ “ህጋዊ ምርጫ” ዋና መሳሪያ ነው። ይህን ህጋዊ ምርጫ ለማካሄድ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት፣ ህጋዊ መንግሥት፣ ለሃገርና ለህዝብ የቆመ መንግሥት፣ነጻና ህጋዊ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት ያለው እና በምርጫ መሸነፍና ማሸነፍ እንዳለ የሚገነዘብ መንግሥት ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ምርጫ ፌዝ፣ ጭዋታና ቀልድ ነው የሚሆነው።
ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አምባገነናዊ፣ ዘረኛ፣ ጨቋኝና አረመኔ ሥርዓት በአለበት አገር ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። ቢሞከርም ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ውጤታማ ሊሆን አይቻልም። እንዲህ አይነት መንግሥት በአለበት አገር ምርጫ ማካሄድ በፍቃደኝነት አምባገነን መንግሥትን ለዘመናት ማንገስና በሃገሪቱ ላይ ለረጅም ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነትና በማን አለብኝነት እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። ለእንዲህ አይነት ለይስሙላ ምርጫ ትልቅ ዋጋ ያለውን እና የመብታችን ማስከበርያ የሆነውን ድምጽ መስጠት አገርንና ህዝብን መበደል ነው፤ እንዲሁም ምንም በማያውቁ የነገ ሃገር ተረካቢ ህፃናት ላይ አምባገነን መንግሥትን በመከራና በጭቆና እንዲያሳድጋቸው መሾም ነው። ህጋዊ ላልሆነ ምርጫ ድምጽን መስጠት እና በማነኛውም መንገድ ተሳታፊ መሆን የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል።
የወያኔን አምባገነናዊነት፣ማንአለብኝነት፣ ጨቋኝነት፣ ብሄርተኝነት፣ ወንበዴነት፣ አገር ሻጭነት፣ ታሪክ አጥፊነት፣
ትውልድ ገዳይነት ላይ ጥያቄ አለን ብየ አላምንም፤ ምክንያቱም የወያኔን ወሮበላነት በሚታይ ገሃዳዊ እውነታና
አለም አቀፍ የሰባዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በትክክለኛ መረጃ የመሰከለሩለት እና የወያኔ ዋነኛ መገለጫ
ባህሪው ስለሆነ። ህጋዊና ፍትሃዊ ምርጫ በወያኔ ዘመን የሚታሰብ አይደለም። ለአራት ተከታታይ ምርጫዎች
በሚገባ አይተነዋል። የአገራችን ኢትዮጵያ የይስሙላ ምርጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወያኔን የበላይነት እያረጋገጠ
እንጂ የህዝብን መብትና ድምጽን ማስከበር አልቻለም፤ ወደፊትም ወያኔ እስካለ ድረስ የህዝብ ድምጽ ሊከበር
አይችልም።
ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት በሃገሪቱ ዲሞክራሲ አለመኖር እና አምባገነናዊ ስርዓት መስፈኑ ነው። በሌላ
መልኩ ነጻ የሆነ የፍትህ ስርዓት፣ የሚዲያ አገልግሎት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የመከላከያ የደህንነትና የፖሊስ ሃይል
ተቋም አለመኖሩ ህጋዊ ምርጫ እንዳይካሄድ እና እንዳይኖር አድርጎታል። እነዚህ ነጻ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ
ሃገራዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፤ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ፓርላማ
መገንባት አይቻልም። ጠንካራ የሆነ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት በሃገሪቱ እንዲኖር ማድረግ ከባድና አስቸጋሪ
ነው። ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶችም በወያኔ እጅ የተያዘ የሻማ መብራት ናቸው። ወያኔ ሲፈልግ ያጣፋቸዋል
ሲፈልግ ደግሞ ጊዜያዊ ብርሃን እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል ነገር ግን ብርሃናቸው ለወያኔ እንጂ እነርሱ እንኳ
እንዳይጠቀሙ ጥቁር መጋረጃ ከልሎባቸዋል።
የህዝብን መብትና የህግ የበላይነትን ሊያስከብሩ የሚችሉ ነጻ ተቋማት በኢትዮጵያ እስካልተቋቋሙ ድረስ እና
እነዚህን ተቋማት ለመገንባት ወያኔ ፈቃደኛ እስካልሆነ ድረስ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እናደርጋለን ብሎ መሞኘት
አሁንም ለተጨማሪ አምስት አመታት በፍቃደኝነት ወያኔ በአምባገነንነት አገዛዝ ስልጣን ላይ እንዲቆይ እድል
መስጠት ነው። በተጨማሪም ወያኔ የህዝብን ድምጽ እንዲሰርቅ ተባባሪ መሆን ነው። ምናልባት ለማታለያ 2
እና 3 ወንበር ለተቃዋሚ ሊሰጥ ይችል ይሆናል ሆኖም ግን ዋናው ዓላማችን የዲሞክራሲ ስርዓት በሃገራችን
ለመገንባት እንጂ ስልጣን ላይ ለመንጠልጠል አይደለምና የህዝብን ድምጽ ሊያስከብር የሚችል ፍትሃዊ ምርጫ
እስካላካሄድን ድረስ በምርጫ መሳተፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅጉ ያመዝናል።
እንደሚታወቀው በ1997 ዓ.ም ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ይወክሉኛል ላላቸው ወኪሎች በይፋ ሰጦ ነበር፤
ፍጻሜው ግን በአደባባይ ድምጹ ተነጠቀ፤ ብዙዎችም ሰማትነትን እንዲቀበሉ ተደረገ። የቅንጅት አመራር
ከወያኔ አፈና ተርፋ ያገኟትን ወንበር ይዘው ፓርላማ ላለመግባት የወስኑት ለእነዚህ መሰረታዊ የዲሞክራሲ
ዋስትና ለሆኑ ተቋማት ምስረታ ነበር። ለህዝቡም ጥሪ ያደረጉት የህዝብን ድምጽ ሊያስከብሩ የሚችሉ ነጻ
ተቋማት በቅድሚያ ይገንቡ በማለት ጥሪ በማቅረባቸው ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ በህይወቱ መስዋትነትን
ሲከፍል፣ መሪዎቹ ደግሞ ለአሰቃቂ መከራና እስር ተዳረጉ።
ቅንጅት ስለ ነጻ ተቋማት ጥያቄ ከአነሳበት ወቅት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በሃገራችን ኢትዮጵያ የታየው ሁኔታ
እውነትም እነዚህ ነጻ ተቋማት ስማቸው ብቻ እንጂ ምንም አይነት ነጻ ህልውና የሌላቸው ወያኔ ሰራሽ ሳንባ
ተገጥሞላቸው በወያኔ መልካም ፍቃድ ብቻ የሚተነፍሱ መሆናቸውን በሚገባ ተረድተናል፤ አውቀናልም።
ለአብነት ያክልም የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማርያንን፣ በማነኛውም መልኩ ሥርዓቱን
የሚቃዎሙትን፣ የእምነት ተቋማት መሪዎችን እና ንጹኃን ዜጎችን በወያኔ የሃሰት ክስ ተከሰው ፍርድ ቤት
ሲቀርቡ ፍርድ ቤት ተብየው የሚበይነውን ቅንጣት ታክል እውነትነት የሌለውን ብይን ማየቱ ነጻ የፍትህ
ተቋም ፍጹም አለመኖሩን መረዳት ይቻላል። እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነትና የፖሊስ ሃይል አባላት
የወያኔ አገልጋይነታቸውን በህዝብ ላይ በተለያየ ጊዜ የሚያደርቱትን ኢሰባዊ ድርጊት መመልከቱ ከበቂ በላይ
ማስረጃ ነው፤ የወያኔ እውነተኛ አሽከርና አሻንጉሊት መሆኑንም በሚገባ አረጋግጧል። ሰራዊቱ ከፖለቲካ ጌቶቹ
በሚሰጠው ትዕዛዝ ሴት፣ወንድ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ አረጋዊ ፣የተማረና ያልተማረ ሳይል በግፍ ወደ እስር ቤት
ወርውሯል፣ ዛሬም ካለምንም ርህራሄ በማጎር ላይ ይገኛል። የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችን በማሰርና
ለአምባገነን ስርዓቱ እንዲመች ተደርጎ በረቀቀው ጸረ-ሽብር ህግ በመታገዝ በሽብርተኝነት በመፈረጅ የእድሜ
ክ እስራት ሲያስፈርድባቸው እናያለን። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እራሱ ወያኔ ሞኝ መስሎት አሸባሪ እያለ
ለማጥላላት ሲሞክር እያየን ነው።
መገናኛ ብዙኃንም የጠነዛ እጅ እጅ የሚለውን የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ብቻ እንደ ገደል ማሚቶ ሲያስተጋባ
ይውላል። የመገናኛ ብዙኃን ተቋሙ ከእስር የተረፉ እውነተኛ ጋዜጠኞችን ለስደት በመዳረግ የወያኔ
ተላላኪዎችና የአድር ባይ ጥቅመኞች ስብስብ ሁኗል። የምርጫ ቦርድ ተቋሙም ከምስረታው ጀምሮ ነጻ ተቋም
ሳይሆን የወያኔ ምርጫ አስፈጻሚ አካል እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ለወያኔ ስጋት የሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች
እጭዎችን እንዳይመዘገቡ በማድረግ ከምርጫ ይሰርዛል፤ ይደልዛል። ሌላው ቀርቶ የውጭ ታዛቢዎች እንኳ
እንደ 97ቱ ገብተው እንዳይታዘቡ መንገዶችን ዘግቷል። እነሱም ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንደማይኖር እርግጠኛ
በመሆን ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ከማባከን ተቆጥበዋል። “ ነጻ ተቋማት ተመስርተው ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ
ቢደረግ በመላ ሃገሪቱ ልክ በ1997ቱ ምርጫ በአዲስ አበባ እንደታየው አንድም ሰው አይመርጠኝም” የሚል ጽኑ
ፍራቻ ወያኔ ስላደረበት እውነትም ስለሆነ ነጻ ተቋማትን ወያኔ በጥብቅ ቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
ታዲያ ይህ ከሆነ በወያኔ ዘምን “ፍታዊና ህጋዊ ምርጫ” እንዴት እውን ይሆናል ብሎ ጊዜን፣ ጉልበትንና
ገንዘብን በከንቱ ለይስሙላ ምርጫ ማጥፋት ይቻላል የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ይሻል። እንደ
እኔ ህጋዊና ፍትሃዊ ባልሆነ ምርጫ ተሳትፎ ድምጽን በፍቃደኝነት ከመሸጥ ይልቅ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል
መልኩ ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ እራስን ማዘጋጀትና ቢያንስ የሚከተሉትን ተግባራት ህብረትን ፈጥሮ
በአንድነት መተግበር በእጅጉ ያስፈልጋል፤ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
1. ድምጽን ሊያስከበሩ የሚችሉ ነጻ ተቋማትን ለመገንባት ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ (የነጻ ተቋማትን
ምንነትና ተግባር ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ከመፍጠር ይጀምራል)
2. ከምርጫ በፊት የህግ የበላይነት እንዲከበር ሃገራዊ ጥሪ ማድረግ (የህግ የበላይነት ሳይኖር የህዝብ ድምጽ
ሊከበር አይችልምና)
3. የህሌና እስረኞች እንዲፈቱ “ምርጫን” ትልቅ መከራከርያ ነጥብ አድርጎ በጽኑ መታገል
4. ተቃዋሚዎች በትብብር መስራትና ለአባሎቻቸው ሙሉ ዋስትና ሊኖራቸው እንዲችል ስልታዊ እቅድ ነድፎ
ትልቅ ሥራ መስራት(ተመራጭ እጭዎች እንኳ ዋስትና ሳይኖራቸው ምን አይነት ምርጫ ለማካሄድ ነው ጊዜ
የምናጠፋው)
5. ለፍትህ ስርዓት፣ ለብዙኃን መገናኛ/ሚዲያ አገልግሎት፣ ለምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ፣ ለመከላከያ የደህንነትና
የፖሊስ ሃይል አባላት በሙሉ ከወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚነት ተቆጥበው ለህዝብና ከህዝብ ጋር እንዲቆሙ ግልጽ
ደብዳቤ መጻፍ(መልእክቱ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው አማካኝነት እንዲደርሳቸው ማድረግ)
6. ጸረ-ሽብር ህጉን የወያኔ መንግሥት እንዲፈትሽና ለንጹኃን ዜጎች የእስር ማጎርያ ዜዴ ማድረጉን እንዲያቆም
በአጽንኦት ማሳሰብ
7. እያንዳንዱን የህዝብ ጥያቄ ለሰባዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችና ለተባበሩት መንግሥታት ማሳወቅ
ወያኔ ከላይ በጥቂቱ የተገለጹትን ጥያቄዎች ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ካልቻለ በህብረትና በአንድነት ነጻነት፣
ፍትህና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዲሰፍን በቀጥታ ወደ ቀጣይ ህዝባዊ እምቢተኝነት መሸጋገር፡
- በመጀመርያ ብሄራዊ አንድነትን መስበክና የህዝብን አንድነት ማጠናከር
- ህዝባዊ አመጾችን በሁሉም አቅጣጫ ማነሳሳት
- ማንኛውንም አገልግሎት በሚሰጡ የመንግሥት ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣል
- የተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች (ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት) ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ አቅጣጫ ማሳየት ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል የሃገሪቱ ወሳኝ አካል መሆኑን ተረድቶ ለመብቱ እንዲቆም ማድረግ
- የሥራ ማቆም አድማ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ማድረግ
- በአደባባይ የምርጫን ካርድ ማቃጠል
- የውጭ እምቢተኝነትን አጠናክሮ መቀጠል በአጠቃላይ በሃገራችን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነጻነት፣ ሰላምና እኩልነት እንዲሰፍን ከተፈለገ ከይስሙላ ምርጫ እራሳችንን አቅበን አምባገነን የወያኔ ወሮ በላ አገዛዝን ከኢትዮጵያ ህዝብ ትክሻ ላይ ለማሶገድ በጋራ ጠንካራ ህብረት በመፍጠር ሁሉንም የተለያዩ የትግል ስልቶችን በተለያየ ቦታና ጊዜ መጠቀም። ውጤቱ ቀድሞ በታወቀ ምርጫ ከመሳተፍ ተቆጥበን ጸረ-ዲሞክራሲ፣ ጸረ-ህዝብና ጸረ- ኢትዮጵያ የሆነውን የወያኔ ህገ ወጥና አምባገነናዊ አገዛዝን ከስሩ ነቅሎ በመጣል እውነተኛ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እንጎናጸፍ። ህገ ወጥ ምርጫን በመቃወም የህዝብን ድምጽ እናስከብር! ከይስሙላ ምርጫ ይልቅ ነጻ ተቋማት ግንባታ ላይ ጊዜያችንን እናጥፋ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment