በፃፈው ምክንያት የታሰረ የለም ሲል የነበረው መንግስታችን ፅሁፎቻችንን እንደማስረጃ በመቁጠር ለክስ አሰናድቶታል፤ ለማስከሰስ የሚያበቃ ጭብጥ በውስጣቸው የያዙ ባይሆኑም ውድቅ የሚያደርግበት ፍርድ ቤት በሌለበት ይህ ለአቃቤ ሕግ የሚያሳስበው አይመስለንም፤ በተጨማሪም ምጡቅ መርማሪዎቻችን በዱላ "አብዮት ልንቀሰቅስ ነበር" ብለው ያስፈረሙን "ሕገ-መንግስቱ ተከብሮ እያለ ‹‹ሕገ-መንግስቱ ይከበር!›› በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ" የሚለው ኑዛዜኣችን እና ሌሎችን ማስረጃቸውን ከብዙ ቀናት ስርዝ ድልዝ እና ምጥ በኋላ ለአቃቤ ሕግ አስረክበዋል ፤አቃቤ ሕግም ክስ ብሎ ከተባባሪው ባልደረባዎቹ ጋር የስራ አስፈጻሚውን ትእዛዛ ሊያስፈጽም ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ የእስከዛሬውን ታዝባችኋል በቀጣዩ ቀናት ከሰኞ ጀምሮ ከመንገድ የተሰበሰቡት ከዛን ቀን በቀር (ከተያዝንበት) አይተውን የማያውቁት ምስክሮች ቃላቸውን ያሰማሉ (እነሱም ከተገኙ) እኛም እንታዘባለን፡፡
የተመቻችሁ ከሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ‹‹የአምባገነኖች ቀልድ በንፁሃን ወጣቶቿ ላይ›› በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መጥተው ይከታተሉ፡፡
ከምንም በላይ በጉዳዩ የእነ ዞላን ምሁራዊ ምክር ለጨቅላው ፍርድ ቤት ሲያካፍል እንሰማለን ምርጦቹንም ዞላ፣ናቲ፣ማሂ፣ኤዲ፣አቤሎ፣በፌ፣አጥኔክስ፣ ቴስ እና አስሚቲን በአካል እናያለን፡፡
ንጹሃንን ነፃ ብሎ መልቀቅ የሃሰት ውንጀላ ከመደረት እጅጉን የቀለለ ነው፡፡
ዛሬም አልረፈደም፡፡
ጋዜጠኝነትም ሆነ መጦመር ወንጀል አይደለም፡፡
Zone9
No comments:
Post a Comment