የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሽብርተኝነት ክስ በመሠረተባቸው ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ምስክሮቹን ከመጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ማሰማት ጀመረ፡፡
ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስያዘው ጭብጥ፣ በዕለቱ ያቀረባቸው ምስክሮች የደረጃ ወይም ታዛቢ ምስክሮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ የሚመሰክሩትም ፖሊስ በተከሳሾቹ ቤት፣ በቢሮአቸውና በማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ፣ ከተከሳሾቹ ላይ የተገኙ ማስረጃዎች የእነሱ መሆናቸውን አምነው ሲፈርሙ ማየታቸውንና እነሱም መፈረማቸውን መሆኑን ገልጿል፡፡
ታዛቢ ምስክሮቹ አንዳንዶቹ ለግል ጉዳያቸው በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ሄደው ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑለት ሲጠይቃቸው፣ በፈቃደኝነት የታዘቡ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ከራሳቸው ላፕቶፕ ላይ (አንዳንዶቹ) የአማርኛና እንግሊዝኛ ጽሑፎችን ማየታቸውንና ርዕስ ርዕሱን ማንበባቸውን ገልጸዋል፡፡ አቤል ዋበላ የተባለው ጦማሪ በራሱ የይለፍ ቃል (Pass Word) ላፕቶፑ ተከፍቶ የታተመ ‹‹አፍሪካን ሪቪው›› የሚል በእንግሊዝኛ የተጻፈ ነገር ማየታቸውን መስክረዋል፡፡ ‹‹ወያኔ ወይኔ ጉዱ›› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ደግሞ የበፈቃዱ ኃይሉ ላፕቶፕ ተከፍቶ ሲታተም ማየታቸውን መስክረዋል፡፡
አንድ ታዛቢ የታዘቡትና ምስክር የፈረሙት በጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ ላይ መሆኑን ቢገልጹም፣ አስማማውን ከስም በስተቀር በአካል መለየት አቅቷቸዋል፡፡
ቀረብ ብለው እንዲለዩት ቢደረግም ጦማሪ አቤል ዋበላን ‹‹እሱ ነው›› ብለው ደጋግመው ከመናገር ያለፈ አስማማውን መለየት ባለመቻላቸው የችሎት ታዳሚውን አስፈግገዋል፡፡ ሌሎቹም ምስክሮች ተመሳሳይ ምስክርነት በመስጠት ተከሳሾቹ ከፈረሙ በኋላ እነሱም በሰነዱ ላይ መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡
ስድስት ምስክሮችን መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ያሳማው ዓቃቤ ሕግ፣ መጋቢት 22 ደግሞ ስምንት ምስክሮችን አቅርቦ ሰባቱን አሰምቷል፡፡ ሁሉም ተመሳሳይነት ያለው ቃል መስክረዋል፡፡ ቀሪዎቹ ምስክሮች መጥሪያ ደርሷቸው ባለመቅረባቸው ታስረው እንዲቀርቡለት፣ ሌሎች ምስክሮችን ፖሊስ ፈልጎ ሊያገኛቸው ባለመቻሉ፣ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶት አፈላልጎ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡ ፖሊስ አፈላልጎ ስለማጣቱ ዓቃቤ ሕግ ምንም ማስረጃ ባላቀረበበት፣ ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡትም ቢሆኑ በአዳር እንዲቀርቡ እንዲታዘዝላቸው ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የሰነድን ማስረጃ በሚመለከት ስላልካዱ እነሱን በእስር አቆይቶ እንዲንገላቱ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ ስለሌለው፣ ዓቃቤ ሕግ ተመሳሳይነት ያላቸው ምስክሮቹን ማሰማቱን አቋርጦ ወደ ቀጣይ ማስረጃ መስማት እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ምስክሮቹን ከማሰማቱ በፊት አቤቱታ እንዳለው አመልክቶ ፍርድ ቤቱ ሲቀበለው፣ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652 2001 አንቀጽ 32 መሠረት ‹‹ምስክሮቼ ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ምስክርነቱ በዝግ ይታይልኝ፤›› ብሎ አመልክቷል፡፡
ዳኞቹ ተመካክረው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 መሠረት በዝግ የሚታዩ ጉዳዮች ተዘርዝረው ከመቀመጣቸው አንፃር፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው አቤቱታ አሳማኝ አለመሆኑን በመንገር አቤቱታውን ወድቅ አድርገውበታል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ ፖሊስ ያላገኛቸውን ምስክሮች ፈልጎ እንዲያቀርብና መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡት ምስክሮች ታስረው ለመጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጥሯል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment