Wednesday, October 30, 2013

የቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ታሰሩ

-በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስና ግለሰቦችን በመጥቀም ሙስና ወንጀል ተከሰዋል
ሥልጣን ሳይኖራቸው ከአሠራር ውጪ እየወሰኑ በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ፣ ግለሰቦችን ያላግባብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል
የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ጐሳዬ ታሰሩ፡፡ 
መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም. በተጻፈ ክስ ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው አቶ ተፈሪ፣ ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያት ግልጽ ባይደረግም፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ከነምክትላቸው ከሥራ ገበታቸው መታገዳቸው ይታወሳል፡፡ 
አቶ ተፈሪ በውጭ ምንዛሪ ተከራይቶ የነበረውን በቀድሞ ወረዳ 23 ቀበሌ 12 የሚገኝንና የቤት ቁጥሩ 106 የሆነውን የመንግሥት ቤት ለኢትዮጵያውያን ለማከራየት የተወሰነውን 1,998 ብር የኪራይ ተመን፣ የኤጀንሲውን መመርያ አንቀጽ 13(5) በመጣስ 1,500 ብር እንዲከራይ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 
በመሆኑም መንግሥት ከቤቱ ኪራይ ሊያገኝ ይገባ የነበረውን የዓመት ክፍያ 17,420 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውንም ያክላል፡፡ 
ዋና ዳይሬክተሩ በ7,650 ብር ለመኖሪያ ቤት የተከራየን የመንግሥት ቤት ተከራዮቹ እንዳልተመቻቸው አድርገው ማመልከቻ እንዲያስገቡ በማድረግ፣ የድርጅት የነበረውን ቤት በመኖሪያ ቤትነት ተቀይሮ እንዲሰጣቸውና ለድርጅት የነበረው የቤት ኪራይ ከ5,126 ብር ወደ 1,093 ብር ዝቅ እንዲልላቸው ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በዓመት ሲሰላም 244 ሺሕ ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያክላል፡፡ 
አቶ ፍቅሬ በወር 4,033 ብር ይከራይ የነበረን የመንግሥት ቤት ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ 129,056 ብር በመቀነስ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ በወረዳ 18 ቀበሌ 06 የሚገኝን የመንግሥት ቤት አንድ የፓርላማ አባል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተጻፈላቸው ደብዳቤ ሳይኖር ከእሳቸው ጋር የግል ቀረቤታ ስላላቸው፣ ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ልዩነት በመፍጠርና ኃላፊነታቸውን ያላግባብ በመጠቀም ቤት እንዲቀየርላቸው ማድረጋቸውን፣ ክሱ ያብራራል፡፡ ኪራዩም ከ7,650 ብር ወደ 650 ብር ዝቅ እንዲል በማድረግ የ7,000 ብር ቅናሽ እንዳደረጉላቸው ክሱ ይጠቁማል፡፡ 
የቤቶች ኤጀንሲ ከሚያስተዳድራቸው የመንግሥት ቤቶች ውስጥ ለተወሰኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች፣ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ተመድበው የነበሩ በቀድሞው ወረዳ 17 ቀበሌ 25 ውስጥ የሚገኙ ከ40 በላይ የመኖሪያ ቤቶች፣ በአዋጅ ቁጥር 555/2000 አንቀጽ 11(2) መሠረት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማፅደቅ እየተገባው፣ አቶ ፍቅሬ በራሳቸው ተግባራዊ በማድረግ ከሥልጣናቸው በላይ በመሥራትና በመወሰን፣ በግለሰቦች ስም በማዞርና በማከራየት ግለሰቦችን ያላግባብ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 
አቶ ፍቅሬ የተጠረጠሩበት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ከተነበበላቸው በኋላ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁም፣ ክሱን እየተመለከተው ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የወንጀል ችሎት የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ አዟል፡፡ 

No comments: