Thursday, October 31, 2013

የመን ሌላኛዋ የኢትዮጵያዊያን የዋይታ ምድር

ለኢትዮጵያዊያን የዋይታ ምድር ያልሆነ የትኛው አገር ነው?  የተሻለ ኑሮን ፍለጋ እንደ አፈር የተበተኑ ኢትዮጵያዊያን በባዕድ ምድር ክብራቸውን ለሚያዋርድ ጥቃት የመጋለጣቸው ዜና ከስደት ታሪካችን ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ነው ፡፡ ለተሻለ ህይወት የመሸጋገሪያ ድልድይ ተደርጋ በምትወሰደው የመን ዘግናኝና ኢ-ሰብአዊ የሆኑ በደሎች በኢትዮጵያዊያኑ ላይ መፈፀሙንና አሁንም እየተፈፀመ እንደሚገኝ ‹‹ተበዳዮቹን›› የአገራችን ልጆች ዋቢ በማድረግ ተከታዩ ዘገባ ይተርካል፡፡
     ከአፍሪካ ቀንድ በዛ ያሉ ስደተኞች በየአመቱ ወደ የመን ይጎራፋሉ፡፡ ከየመን ባሻገር በሚገኙት ሳውዲ አረቢያና የገልፍ አገራት የተሻለ ህይወት ለማግኘት በመቋመጥ የመንን እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙት ስደተኞች ህልማቸውን ሳያሳኩ በየመን በረሃ ቀልጠው የሚቀሩባቸው አጋጣሚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ እየተስተዋለ ነው፡፡
     ከቅርብ አመታት ወዲህ የየመንን ምድር ከረገጡ ስደተኞች መካከል  የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ቀይ ባህርን በማቋረጥ በ2012 በስደተኝነት ከተመዘገቡ 107,000 ሰዎች ውስጥ 80,000 የሚሆኑት ዜግነት ኢትዮጵያዊ እንደነበር የአለም የስደተኞች ድርጅት ያወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
     የአሁኑ ቴሌቪዥን ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን የነገሩትን አራት ስደተኞችን በየመን ስለሚመሩት ህይወት ጠይቋቸው ነበር፡፡ የስደተኞቹ ታሪክ የተለያየ ቢሆንም የሚጋሩት የስደተኝነት ልምድ አንድ አድርጓቸዋል፡፡ ሊጨብጡት የናፈቁት ተስፋ ተንኗል፣ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል፣ ተደፍረዋል፡፡ እነዚህ መጥፎ ገጠመኞቻቸው የህይወታቸው አንድ አካል በመሆናቸው አንድ አድርገዋቸዋል፡፡
     ማርታ ኢትዮጵያን የለቀቀችው በ2002 ነበር፡፡ ማርታና ቤተሰቦቿ የመንግስት ተቃዋሚ የሆነውን ኦነግን ትደግፋላችሁ በመባላቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ አገራቸውን ለቅቀዋል፡፡ ‹‹መንግስት እናንተ የኦነግ ደጋፊዎች ናችሁ አለን፡፡ ስለዚህም ከአገራችን እንድንወጣ አደረገን፡፡ የቤተሰቦቼ መጨረሻ ግን ምን እንደሚሆን አላውቅም፡፡›› ብላለች፡፡ ማርታ በመጀመሪያ ያቀናችው ወደ ጁቡቲ ነበር ‹‹ለአንድ አመት ከአጋማሽ በጁቡቲ ተቀመጥኩ፡፡ በዚያ እያለሁም የመጀመሪያየ የሆነችውን ሴት ልጅ ተገላገልኩ፡፡ የልጄ አባት መጥፋቱን ተከትሎ ወደ የመን አቀናሁ፡፡ 15 የሚሆኑ ሰዎችን በጫነች ጀልባ ወደ የመን ለማምራት ለደላሎች 55 የአሜሪካን ዶላር ከፍያለሁ፡፡ ቀይ ባህርን ለማቋረጥ በጀልባዋ በምሽት የምናደርገው ጉዞ እስከመጨረሻው ፀጥታ የሰፈነበት ነበር፡፡ የየመንን ክልል እየተጠጋን ስንመጣ የጀልባ ባለቤት ሰዎችን ወደ ባህሩ መወርወር ጀመረ፡፡ ማንኛችንም እንዴት መዋኘት እንዳለብን አናውቅም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ያለው ወንዝ እንጂ ባህር አይደለም፡፡ ደላሎችና አጋሮቻቸው ከባሕሩ ስንወጣ ይጠብቁን ነበር፡፡ እኔንና ሌሎች ሴቶችን ከባሕሩ እንደወጣን ደፈሩን፡፡ በዚያ ምሽት በደረሰብኝ የወሲብ ጥቃት በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ ወር ፅንስ ይዣለሁ፡፡››
     ማርታ በእንባ እየታጠበች የደረሰባትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መተረክ ቀጠለች፡፡ ሰንዓ እንደደረስን በጣም በመዳከሜ የተነሳ በከተማዋ ለመቆየት ወሰንኩ፣ ለሰባት ወራት ያህል በቤት ሰራተኝነት ተቀጠርኩ፡፡ ነገር ግን አሁን በእርግዝናው የተነሳ ተቀጥሬ መስራት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ምንም ገቢ የሌለኝ ሰው ሆኛለሁ፡፡ በሰንዓ የሚኖሩ የአገሬ ልጆች ይመፀውቱኛል፡፡›› የ18 ዓመቷ አሊማ ከምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ጁቡቲ ያቀናችው የኦነግ ደጋፊ በመሆኗ ከመንግስት ሊደርስብኝ ይችላል ያለችውን አደጋ በመፍራት ነው፡፡ ‹‹ለአንድ አመት ያህል በጁቡቲ ሰርቺያለሁ፡፡ ህይወት በዚያ ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባል አልነበረም፡፡ ሌቦች በወሩ መጨረሻ የምናገኘውን  ደሞዝ እየዘረፉን ሲያስቸግሩን ወደ የመን ለማምራት ወሰንኩ፡፡ ለደላሎቹ 110 ዶላር ክፍያ በመፈፀም ወደ የመን የሚወስደኝን ጀልባ እንዲያገናኙኝ አደረግኩ፡፡ ሃዩ የተባለችው ደሴት ስንደርስ ዘራፊዎች ያዙን፡፡ ገንዘብ ከሰጠናቸው እንደሚለቁን ነገሩን፡፡ እኔ ገንዘብ ስላልነበረኝ ደፈሩኝ፡፡ ገንዘብ የሌላቸውን ወንዶች ደብደቧቸው፡፡ ሴቶቹን ደፈሩ፡፡ ቤተሰቦቼን በመገናኘት 200 ዶላር እንዲልኩልኝ በማድረጌ ወደ የመን ማምራት ቻልኩ፡፡››
     120 ስደተኞችን በጫነች ጅልባ ወደ የመን ሰሜን ያቀናችው አሊማ ከሌላ ስቃይ ጋር ተፋጠጠች፡፡ ባብ አል ማዳብ እንደደረስን መሳሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች ያዙን፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ዘራፊዎቹ ወንዶቹን ደበደቧቸው፡፡ የምንበዛውን ሴቶች ደግሞ ደፈሩን፡፡ ገንዘብ የሌላቸውን ሴቶች ዘራፊዎቹ ለደላሎች ይሸጧቸዋል፡፡ ደላሎቹ ሴቶቹን በመውሰድ በየመናዊ ቤቶች እንዲቀጠሩ ያደርጋሉ፡፡ እኔን የገዛኝ ደላላ ወደ ራዳ ላከኝ፡፡ በዚያ ለሦስት ወራት በጽዳት ሰራተኝነት ተቀጥሬ ሰራሁ፡፡ እኔን ያፈቀረ አንድ ሰው ገንዘብ ከፍሎ ነጻ ካወጣኝ በኋላ አገባኝ፡፡ ባለቤቴ የሚሰራው በጫት እርሻ ላይ ነው፡፡ እኔ የቤት ስራ እሰራለሁ፡፡ ገንዘብ ማግኘት ብችል ወደተሻለ አገር ከመሄድ ወደ ኋላ አልልም፡፡››
     የ38 ዓመቱ መስፍን የደሴ ልጅ ነው፡፡ ‹‹የተወለድኩትና ያደግኩት በማደጎነት ነው፡፡ ቤተሰብ የለኝም፣ የሚረዳኝም አልነበረም፡፡ ህይወት ለእኔ አሰልቺ ነበረች፡፡ ስለዚህ ለመሰደድ ወሰንኩ፡፡ ጁቡቲ ከመድረሴ በፊት ለአምስት ቀናት ያህል በአውቶብስና በባቡር ተጓጉዣለሁ፡፡ በቀጥታ ከደሴ በመነሳት ቀይ ባህርን ማቋረጥ እችል ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም አደገኛ በመሆኑ በዚያ መንገድ መሄድ አልፈለግኩም፡፡ ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን በዚያ አሳልፈዋል፡፡ ደላሎች የኢትዮጵያ 1000 ብር ከከፈልኳቸው የመን እንደሚያደርሱኝ ቃል ገብተውልኝ የነበረ ቢሆንም ሃዩ ደሴት እንደደረስኩ 400 ብር እንድጨምር ተደርጊያለሁ፡፡ ቀይ ባህርን ያቋረጥነው 80 ሰዎችን በጫነች እጅግ አነስተኛ ጀልባ ነበር፡፡ ጉዟችንን አጠናቅቀን መሬት እደረገጥን ያመጡን ደላሎች መሳሪያ ከታጠቁ ሰዎች ጋር አገናኙን፡፡ ታጣቂዎቹ ‹‹ገንዘብ እድንሰጣቸው ጠየቁን፡፡ ገንዘብ እንደሌለን ስንነግራቸውም ይደበድቡን ጀመር፡፡ ሴቶቹን በአይናችንፊት ለፊት ደፈሯቸው፡፡ እኔንና የተወሰኑ ስደተኞችን ታጣቂዎቹ ወደ እስር ቤት ወሰዱን፡፡ ከዚህ ቦታ መውጣት የምንችለው ገንዘብ ከተላከ ብቻ እንደሆነ በመንገር ለቤተሰቦቻችንን እንድንደውል አደረጉን፡፡ ሴቶቹ በእስር ቤት ውስጥ በየቀኑ ይደፈራሉ፡፡ እኔን በተከታታይ አምስት ቀናት ደበደቡኝ፡፡ በአምስተኛው ቀን ምሽት ሌሎቹን እስረኞች እንድመግብ የእጄን ሰንሰለት አወለቁልኝ፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀምም ከእስር ቤቱ አመለጥኩ፡፡›› ያሲን የ23 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ወደ ስቃይ ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ ከቤተሰቦቹ ጋር በአዲስ አበባ ይኖር ነበር፡፡ ያሲን አገሩን የለቀቀው የነበረበትን የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡ ‹‹ምንም አይነት የፖለቲካ አመለካከት የለኝም፡፡ አባቴን በልጅነቴ በማጣቴ ያደግኩት በእናቴ ረዳትነት ነው፡፡ ምንም አይነት ገቢ ስላልነበረኝ እድገቴ ችግር ያልተላቀቀው ነበር፡፡ እህቶቼንና ወንድሞቼን ለመርዳት የነበረኝ አማራጭ አገር ጥሎ መሰደድ በመሆኑ መጀመሪያ ያቀናሁት ወደ ጁቡቲ ነበር፡፡ በጁቡቲ ጥሩ ስራ ባለማግኘቴ 1000 የኢትዮጵያ ብር በመክፈል ወደ የመን በጀልባ አቀናሁ፡፡››
     ያሲን 45 ሰው አጭቃ በያዘች አነስተኛ ጀልባ ተሳፍሮ በምሽት ወደ የመን እያቀና ነው፡፡ እኛ በጀልባ መሄድ እንደጀመርን 25 ሰው ለመጫን የተሰራች ነገር ግን ከ50 ሰው በላይ የጫነች የእንጨት ጅልባ በፍጥነት አለፈችን፡፡ ጀልባዋ ብዙ ርቀት ሳትጓዝ ለሁለት ተሰነጠቀች፡፡ በምሽቱ ውስጥ ጀልባዋ ላይ የነበሩ ሰዎች በባህሩ እየሰመጡ የድረሱልን ጩኸት ያሰሙ ነበር፡፡ የሚበዙት ህይወታቸውን ያጡት በቅጽበት ነበር፡፡ እኛም ማቾቹን ቀበርናቸው፡፡ ባብ አል ማንዳብ  ደሴት እንደደረስን ታጣቂዎች ወደ ሰማይ መተኮስ ጀመሩ፡፡ ታጣቂዎቹ በመኪና ጭነው እስር ቤት አስገቡን፡፡ ገንዘብ የሌላቸውን ወንዶች በብረት ይደበድባሉ፡፡ የእጅና የእግር ጣቶችን ይቆርጣሉ፣ በእሳት የጋየ ብረት አይናቸው ውስጥ እየከተቱ አይናቸውን ያጠፋሉ፣ ሴቶቹን ይደፍራሉ፣ ፕላስቲኮችን በእሳት እያቀለጡ ገላቸው ላይ ያፈሳሉ፡፡››
     የቢቢሲው ጋዜጠኛ ያልዳ ሃኪም በኢትዮጵያዊያኑ የተገለጸውን የማሰቃያ ስፍራ በመጎብኘት እውነታውን አረጋግጦ ተመልሷል፡፡ ጋዜጠኛው በእስር ቤቱ በዛ ያሉ ወንዶችንና ሴቶችን አግኝቷል፡፡ ሴቶቹ በደረሰባቸው የቀን ተቀን መደፈር ተዳክመው ከሰውነት ተራ ወጥተዋል፡፡ ወንዶቹ በድብደባና ርሃብ ተዳክመው የደረሰባቸውን ለመናገር የሚያስችላቸውን አቅም አጥተዋል፡፡
     ኢትዮጵያዊያን በየመን እየደረሰባቸው የሚገኘውን ስቃይ የአገሪቱ ጋዜጦች ይፋ እስከማውጣት ደርሰዋል፡፡ በአንጻሩ በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ የሚታይ የዲፕሎማሲ ስራ ለመስራት አለመድፈሩ ሐዘኑን የከፋ ያደርገዋል፡፡

No comments: