Saturday, October 12, 2013

ከ15 ሺ በላይ የኢህአዴግ አባላት መልቀቂያ አስገቡ

ከ15 ሺ በላይ የኢህአዴግ አባላት መልቀቂያ አስገቡ

ESAT Amharic News
ጥቅምት (አንድ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ እያካሄደ ባለው የአባላት ግምገማ ወቅት ከ15 ሺ በላይ አባላት በአንድ ጊዜ መልቀቂያ ማስገባታቸው ይፋ ተደርጓል።
ስራቸውን ከሚለቁበት ምክንያቶች መካከል  በድርጅቱ አመኔታ ማጣት ፣ ተገቢውን አገልግሎት ክፍያ አለማግኘት፣ ለድርጅቱ የሚከፍሉት ገንዘብ ከፍተኛ መሆን እና የድርጅቱ አባላት ሹመት በወገን መሆኑ የሚሉት ተጠቅሰዋል።
ከፍተኛ የአባላት መልቀቂአ ቁጥር ከተመዘገበባቸው ክልሎች መካከል ኦሮሚያ በ9 ሺ 4 መቶ 56 አንደኛ ሲሆን ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልል እና ትግራይ በተከታታይ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል። በትግራይ በ2005 ዓ/ም 1 ሺ 1 መቶ 13 ሰዎች የህወሀት አባላት መልቀቂያ አስገብተዋል።
ኢህአዴግ 5 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ቢነገርም ፣ በንቃት የሚሳተፉት 2 ሚሊዮነቹ ብቻ ናቸው ተንብሎአል። ከእነዚህ መካከል 20 ሺ የሚሆኑት በስም ብቻ አባላት ተብለው ቢመዘገቡም፣ በአካል የሌሉ መሆናቸውም ተገልጿል።
በስብሰባው አብዛኞቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለደሞዝና ለስራ ሲሉ አባል እንደሚሆኑ የተገለጸ ቢሆንም በአለፉት አመታት ድርጅቱን ከተቀላቀሉት ተማሪዎች መካከል ስራ አገኙት ሩብ አይሆንም ተብሎአል።
በክልል ዋና ዋና ከተሞች በአዋሳ፣ ባህርዳር፣ እና መቀሌ ውጤት ያላቸው ተመራቂዎች ስራ ሳይዙ፣ ውጤት የሌላቸው የድርጅቱ ነባር አባላት በተቃራኒው ስራ መቀጠራቸው በአባላቱ ላይ ቅርታ እንዲፈጠር አድርጎአል ተብሏልም ።
ዛሬ ስራ ማግኘት የህልም እንጀራ ነው ያሉት አባሎች፣ ዲግሪ ይዘው ስራ ለማግኘት ከሶስት እስከ 4 አመታት የሚጠብቁ ተመራቂዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ኢህአዴግ መልቀቂያ ያቀረቡ አባላቱን ጥገኞች ሲል ሰይሞአቸዋል። የድርጅቱ አባላት ለኢሳት እንደገለጹት አብዛኞቹ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች በሙስና የተዘፈቁ ናቸው። ኢሳት በሚቀጥለው ሳምንት <<የድርጅት አባላት እንዲያውቁት>> በሚል የብአዴን የአመራር አባላት ሙስናን በተመለከተ የላኩትን ደብዳቤ ይፋ እንደሚያደርግ ለመግለጽ ይወዳል።
በተመሳሳይ ዜናም አክራሪነትና ጽንፈኝነትን አስመልክቶ ስልጠና ለመስጥት የፈዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከሐረማያ ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበር ትናንት ያደረገዉ ስብሰባ ያለዉጤት ተበትኗል።
መንግስት ንጹሀንን ያለምንም መረጋገጫ አክራሪ አሸባሪ ብሎ መፈረጁ ግዜ ያለፈበት ነው”ያሉት የስብሰባው ተሳታፊዎች፤”በመንግስት እየተባለ ያለውን ነገር+ እንኳን  የዩንቨርስቲዉ ማህበረሰብ ፤ሳይማሩ እያስተማሩ ያሉት እናት አባቶቻችንም አይቀበሉትም “ብለዋል።
ተማሪዎችና መምህራን  በማከልም፦”የመረጃ ምንጫችን ኢቲቪ ብቻ ነው ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ተሳስታችሗል” በማለት  የመንግስት ባለስልጣናትን ሞግተዋቸዋል።
“ጽንፈኛ” የሚለዉ ቃል በባርያ ፍንገላ ግዜ በባሪያ አሳዳሪዎች ላይ ያምጹ ለነበሩ ግለሰቦች የተሰጠ ስያሜ ነው በማለት የተናገሩት  አንድ ክርስቲያን የሆኑ የስብሰባው ታዳሚ፤ “መንግስት የእስልምና ሐማኖት ተከታዮች  በክርስቲያኑ ላይ ጦርነት ሊያዉጁ ነው ብሎ ቢናገር ፤ህዝበ ክርስቲያኑ አይቀበለውም”ብለዋል።
ግለሰቡ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፦ኢትዮጵያ ዉስጥ አክራሪ አለ ማለቱ አለማቀፋዊ እዉቅናን ያላገንኘና ተዓማኒት የሌለዉ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ቢ.ቢ.ኤን ዘገባ፤በስብሰባው ላይ በዩንቨርሲቲዉ ሶላትና ሂጃብን አስመልክቶ እገዳ ለማድረግ እቅድ እንዳለ የቀረበው ሃሳብ በሁሉም ተሳታፊዎች ከፍ ያለ ተቃውሞ ገጥሞታል።
“ኢትዮጵያን ልክ እንደ አፍጋኒስታንንና ፓኪስታን ችግር ያለባት ማስመሰሉ ተገቢ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተቻችሎ ያለ በመሆኑ ያንዱ ወገን ሐይማኖት መከበር ለሌላዉ ስጋት አይደለም፤”ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ ሰዎችአለባበሳቸዉን ከቀየሩ አመለካከታቸዉን ይቀይራሉ ማለቱ  ስህተት ስለሆነ “ሀይማኖታዊ አለባበስ ከዩኒቨርሲቲ በር መልስ”የሚለው ሃሳብና እቅድ ተቀባይነት የለውም”ብለዋል።
የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር  በሐረማያ ዩኒቨርስቲ” አክራሪነትንና አሸባሪነትን” አስመልክቶ ባዘጋጀዉ በዚህ  ስልጠና ላይ እስከ አስራ ሁለት ሺ የሚጠጉ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
ይሁንና በርካታ ተማሪዎች የመንግስት ባለስልጣናት የሚያቀርቡትን ሐሳብ ፊት ለፊት በንግግር ከመቃወማቸውም በላይ   ስብሰባዉን ረግጦ ወጥተዋል።

No comments: