በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ
በድንገት “ሽብርተኛ” ሊባል የሚችልበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ተመቻችቷል።
በገፍና በግፍ
ማሰር ግራ የገባቸው አምባገነኖች ሁሉ የጋራ ጠባይ ነውን?
ዛሬ በአገራችን ሁሉም ሰው “የተለመደ ተጠርጣሪ” ሆኗል። አገሪቱ
በሽብርተኞች የተሞላች እስክትመስል ድረስ የሚያዙ “ሽብርተኞች” ዜናና ጉዳይ መነጋገሪያ እየሆነ ነው። ለመሆኑ መንግሥት ይህን ያህል
“ሽብርተኞችን” መያዝ ከቻለ፣ ያልተያዙት “ሽብርተኞች” ስንት ይሆኑ?
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ በድንገት “ሽብርተኛ” ሊባል የሚችልበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ተመቻችቷል።
ይህን ለማስፈጸም የሚችል ሕግ ከነዳኞቹ፣ ሠራዊት ከነመሣሪያው ተዘጋጅቷል። የወያኔ መንግሥት በብዙ መልኩ የመንግሥቱ ኀይለማርያምን
ስትራቴጂ ቃል በቃል መድገም ጀምሯል። እርግጥ መንጌ ሕግን የወያኔን ያህል መጠቀሚያ የማድረግ ብቃት አልነበራቸውም። አንዱ ማሳያ
የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን እስከመጨረሻው የመምታት፣ ከስራቸው ነቅሎና ገድሎ የመጨረስ ፖሊሲ ነው። በዚህ የደርግ ፖሊሲ ሕዝብና አገር
ቢጎዳም ሕወሓት እና ሻእቢያ ግን ተጠቃሚዎች ነበሩ። ደርግ ተቃዋሚዎቹን ያጠፋልኛል ያለው ፖሊሲ “ከሕወሃትና ከሻእቢያ ጋራ በማንኛውም
መንገድ ይገናኛሉ፣ የአማጽያኑን ሐሳብ የመደገፍ አዝማሚያ ሊኖራቸው ይችላል” ያለቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ማሰርና መግደል ነበር።
በመጨረሻ ውጤቱ ይህ ፖሊሲ እነሕወሓትን የሚጠቅም፣ ደርግን ደግሞ ከሕዝብ ፈጽሞ የሚነጥል ነበር፤ በተለይም ከትግራይና ከኤርትራ
ሕዝብ። አምባገነኖች ከታሪክ ለመማር ስለማይችሉ ታሪክን የደገሙ ሳይመስላቸው ታሪክን ይኖራሉ።
አሁን ወያኔ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥፋት
“በሽብርተኝነት” ስም የጀመሩት ዘመቻ የደርግ ግልባጭ ነው፤ በአፈጻጸሙም በውጤቱም። ደርግ “ዓሳን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” ይል
ነበር። ወያኔም ኦነግን እና ግንቦት 7ን ለማጥፋት “ባህራቸውን” ለማድረቅ ተነስተዋል። ወያኔ ባህሩን ለማድረቅ የተከተሉት
መንገድ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችን በሐሳብም ይሁን በተግባር፣ በሕልምም ይሁን በቅዠት መደገፍ አደገኛ ወንጀል እንዲሆን ማድረግ
ነው። ደርግም እንዲሁ ነበር ለማድረግ የሞከረው። ትግሬ (ትግራዋይ) መሆን በራሱ በሕወሓት/ሻእቢያ ደጋፊነት ለመጠርጠር የሚያበቃበት
ጊዜና ሁኔታ ነበር። አሁንም ስትራቴጂው አልተቀየረም። ኦሮሞ መሆን በራሱ የኦነግ አባልና ደጋፊ ተደርጎ ለመጠርጠር የሚበቃ እየሆነ
ነው። የኦነግ አባል የሆነ ዘመድ ያለው ሰው ዘመዱ ከአሜሪካ ደውሎለት ስለአካባቢው ሁኔታ ካወራ፣ ምሬቱን ከገለጸለት፣ ስለ የወያኔ
ካድሬዎች ድራማ ካወራለት አለቀለት። ለአሸባሪው ድርጅት መረጃ ሲያቀብል
ተገኘ ማለት ነው። የስልክ ንግግሩ ቅጂ ይቀርባል፤ ማስረጃ አለን ይባላል። “ማስረጃ” ለማግኘት ሰማይ ምድሩ ይቧጥጣል፡፡ የግንቦት
7 አባል የሆነ፣ ባይሆንም የሚጠረጠር የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛ ካላችሁ እንዳይደውልላችሁ መጸለይ አለባችሁ። ራስህ ደውለህ
“እንዳትደውልልኝ” እንዳትለው ይህን ማድረግ በራሱ የሚያስጠረጥር ነው፤ “የሚደብቁት ነገር ከሌለ ‘አትደውልልኝን’ ምን አመጣው?”
ብለው የሚጠይቁ አዳማጮች አሉ። አገር ውስጥ የሚገኝ ተቃዋሚ አባል ብትሆንም እንዲሁ እንደ እንቅስቃሴህ የዚሁ ወጥመድ ሰለባ ልትሆን
ትችላለህ። ጋዜጠኛ መሆንም እንዲሁ ከመቅሰፍቱ ላይሰውርህ ይችላል። (ከመቅሰፍቱ የሚሰውረውን ታውቀዋለህ!) አንድ ቀን ከቢሮ ወይም
ከቤት አጅበው ሊወስዱህ ይችላሉ። ክምር መረጃ አላቸው፤ ካስፈለገም ክምር መረጃ ይፈጥራሉ ወይም አንተ ራስህ በራስ ላይ ማስረጃ
ትፈጥራለህ። ማእከላዊ በገባህ በአራተኛው ቀን “24” የተባለውን ፊልም የሚያስንቅ የሽብር ድራማ ደርሰህ፣ ዋናው ገጸ ባሕርይም
አንተ ራስህ ሆነህ ትገኛለህ። ልክ እንደአገራችን ፊልመኞች ደራሲውም፣ ፕሮዲውሰሩም፣ ዋና ገፀ ባህርይውም አንተው ራስህ ሆነህ በቲቪ
ትቀርባለህ። ፊልሙን የተሟላ ለማድረግ ደግሞ ሌሎች “የባለሞያ” እገዛ ያደርጉልሃል።
ዛሬ “ሽብርተኛ” እየተባሉ የሚያዙት የብዙዎቹ ሰዎች ታሪክ ከዚህ የምርመራ ሂደት ድራማ የተለየ ስለመሆኑ
ማረጋገጫ የለንም። ጋዜጠኛ ውብሸትን ጨምሮ “በሽብርተኝት” የተጠረጠሩ ሰዎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቶች ተናግረዋል።
(የፍርድ ቤቶቹ ምላሽ አያስቃችሁም? “ከተፈጸመ እንዳይደገም”፣ ወይም ራሱ ደብዳቢው አካል ጉዳዩን እንዲያየው እግረ መንገድ ጠቅሶ
ማለፍ።) ደርግ አገርን ከሚጎዳ፣ ሕዝብን ከሚያሰቃይ ይልቅ “ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ነበረበት” እየተባለ እንደቀለድ
ይነገራል። ይህ ጥፋት የአገር ጥፋት፣ የትውልድ ጥፋት ነበር። ያቺው አገር፣ ያው ራሱ ትውልድ ግን ይህንኑ ጥፋት በባሰ መልኩ እየደገሙት
ነው። ዛሬም መመሪያው “የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች ክበቡ” ነው። ድሮ ደርግ “የተለመዱ ተጠርጣሪዎች” ነበሩት። በአገሪቱ ለሚያጋጥሙ
ማናቸውም ችግሮች ተጠርጣሪዎቹ እነዚሁ አካሎች ነበሩ። በሬዲዮ፣ በኢቲቪ፣ በአዲስ ዘመን፣ በፓርቲ ልሳን፣ በቀበሌ ስብሰባ፣ በሞያ
ማኅበራት፣ በጾታ ማኅበር…አብዮት/መስቀል አደባብይ፣ ናዝሬት፣ ነቀምት፣ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ…ሁሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ
የሚወገዙት እነርሱው ነበሩ። ዛሬም የማውገዣ ቦታዎቹና ተቋማቱ እንኳን አልተቀየሩም። የውግዘቱ ይዘትና ቋንቋም እንዲሁ። የይዘት
ሳይሆን የቃላት ለውጡን በምሳሌ እናስታውስ። ኢምፔሪያሊዝም ወደ ኒዎ ሌበራሊዝም፣ ሕወሃት/ሻእቢያ ወደ ኦነግ/አብነግ/ግንቦት 7፣
ተገንጣይ/አስገንጣይ ወደ ጠባብ/ትምክህተኛ፣ አልቱራቢ/በሽር ወደ ኢሳያስ..ተቀይረዋል።
የሚመራውን መንግሥት ከልቡ ያወጣ ሕዝብ ገበያ አይሄድም፣ ቢሮ አይገባም፣ በኢኮኖሚ አይሳተፍም፣ ለልማት
ስራ አያዋጣም ማለት ቂልነት ነው። በመንግሥቱም ጊዜ እኮ “ለእናት አገር ጥሪ” (ስሙ እንዴት ደስ ይላል!) ሕዝብ አዋጥቱዋል፤
ለልማት ዘመቻ ዘምቷል፤ እረ ለጦርነትም ዘምቷል። እነዚህ ሁሉ ግን ሕዝቡ በሙሉ ልቡ እስከ መጨረሻው ከመንግሥቱ ጋር ስለመሆኑ ማረጋገጫ
ሊሆኑ አይችሉም። አሁንም ልክ እንደድሮው ሕዝቡ በውድም በግድም ለአባይ ግድብ ስላዋጣ ወይም ቦንድ ስለገዛ የወያኔ አገዛዝ የሕዝብ ፍቅር ማሳያ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። “ለእናት አገር ጥሪ”
አለማዋጣት እና ለአባይ ግድብ አለማዋጣት በመሠረቱ ውጤታቸው ተመሳሳይ ነው። ደርግም ኢሕአዴግም የየራሳቸው መቅጫ አላቸው። ለጊዜው
መዋጮው ከቅጣቱ የተሻለ እስከሆነ ድረስ ሕዝቡ የሚመርጠው መዋጮውን ነው። በተጨማሪ ደግሞ “የእናት አገር ጥሪውም” ይሁን “የአባይ
ግድብ” በመሠረቱ ሊደገፉ የሚገባቸው ዓላማዎች ናቸው። ወያኔ እና ኮሎኔል መንግሥቱ ሕዝቡ ለአገሩ ወይም ለግል ጥቅሙ ብሎ የሚያደርገውን
ሁሉ ለእነርሱ ፍቅር ሲል ያደረገ እየመሰላቸው ሳይሞኙ አልቀሩም።
ተቃዋሚዎችን ወይም የተለየ ሐሳብ ያላቸውን
ሁሉ በጥርጣሬ የሚመለከት ፖለቲካ ፈጽሞ ሊረጋጋ አይችልም። የዴሞክራሲያዊ ስርአት መነሻ መሰረት መተማመን እና ይህንኑ ተቋማዊ የሚያደርግ
አመራር ነው። አሁን የምንታዘበው ግን እርስ በርስ መጠራጠርን የፖለቲካ ሥርአቱ መለያ የሚያደርግ፣ መጠራጠርን ተቋማዊነት የሚያላብስ
ፖለቲካነው።
ከአንድነት ብሎግ
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment