Tuesday, July 5, 2016

የኢህአዴግ መንግስት አብዛኛውን ወታደራዊ ግዥ የሚፈጸመው ከቻይና ኩባንያዎች ጋር መሆኑን ሰነዶች አመለከቱ



ሰኔ ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- ለኢሳት የደረሱት ወታደራዊ የመሳሪያ ግዢን የሚያመላክቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መከላከያ ሰራዊት አብዛኛውን ግዢ የሚፈጽመውም ሆነ የእድሳት ስምምነትና እና የግንባታ ስራ የሚሰራው ከቻይናው North Industies Corporation ወይም በአጭሩ NORINCO ኩባንያ ጋር ነው።
መከላከያ ከዚህ ኩባንያ ጋር በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ 2013 ድረስ 440 ሚሊዮን 158 409 አሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የግዢ ኮንትራት የፈጸመ ሲሆን፣ በአማካኝ እስከ ግማሽ የሚሆነው እዳ ተከፍሏል።
መከላከያ ፖሊ ከተባለው ሌላ የቻይና ኩባንያ ጋር ደግሞ በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ 2013 ድረስ 724 ሚሊዮን 567 667 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ የግዢ ኮንትራት የተፈጸመ ሲሆን፣ ከዚህ ግዢ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው እዳ እስካሁን አልተከፈለም።
በሶስተኛ ደረጃ የፖላንዱ ALIT የተቀመጠ ሲሆን ፣ከዚህ ኩባንያ ጋር ደግሞ እስከ 2012 ድረስ 176 ሚሊዮን 34 876 ብር ግዢ ተፈጽሟል። ዩክሬን በአራተኛ ደረጃ የኢህአዴግ መንግስት የጦር መሳሪያ አቅራቢ ናት። እስከ 2013 ከዩክሬን ጋር 160 ሚሊዮን 970 704 የአሜሪካን ዶላር ግዢ መከናወኑን ሰነዱ ያመለክታል። ሩሲያ 6 ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ገዢው ፓርቲ በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን አለማቀፍ ማእቀብ ወደ ጎን  በመተው 2012 Formation of command and control center for air center for air defence በሚል ርእስ 3 ሚሊዮን 200 ዶላር ግዥ ፈጽሟል። በሰነዱ ላይ ገዢው ፓርቲ የገዛቸው መታደራዊ መሳሪያዎች ተዘርዝረው ቀርበዋል።

በሌላ በኩል አየር መንገድ የመለማመጃ ስልጠናውን ሙሉ በሙሉ ከድሬዳዋ በማስወጣት ወደ መቀሌ አዛውሯል። አየር ሃይል ለአስቸኳይ ግዳጅ ተፈልጓል በሚል አየር መንገድ የበረራ ስልጠናውን ከድሬዳዋ ወደ መቀሌ እንዲያዛውር ትእዛዝ መስጠቱን ኢሳት መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ሁሉም የበረራ መለማመጃ አውሮፕላኖች ነቅለው ወደ መቀሌ የሄዱ ሲሆን፣ በድሬዳዋ ላይ የቀረው በጥገና ምክንያት አንድ ዲያመንድ የተባለ የመለማመጃ አውሮፕላን ብቻ መሆኑ ታውቋል።

No comments: