ከወራት በፊት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ መነሻ በነበረችዉ ጊንጪ ከተማ ዳግም ተቃውሞ ተቀስቅሶ በትንሹ አንድ የ9ኛ
ክፍል ተማሪ ተገደለ።
ሰሞኑን የከተማዋ ነዋሪዎች በፅጥታ ሀይሎች ቀጥሎ ያለን የሀይል ድርጊት በመቃወም ወደ አደባባይ በወጡ በጊንጪ ከተማ ሰፍረዉ የሚገኙ የፌደራል የፅጥታ ሀይሎች በነዋሪዉ ላይ ተኩስ መክፈታቸዉን እማኞች ለኢሳት ገልፅዋል።
የፅጥታ ሀይሎች በወሰዱት በዚሁ የተኩስ እርምጃ እሸቱ ወርቁ የተባለ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አንገቱን በጥይት ተመቶ ህይወቱ ሊያልፍ መቻሉን አባቱ አቶ ወርቁ ዋሮዳ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ሟች ልጃቸዉ አምስተኛ ልጄ ነበር ሲሉ በሀዘን የገለፁት አቶ ወርቁ ልጃቸዉ በተገደለ ጊዜ በከተማዋ ነዋሪዋች ዘንድ ተቃዉሞ ሲካሄድ እንደነበር አስታውቀዋል።
በዞን እና በከተማዋ ያሉ የፀጥታ ሀይሎች ተቃዉሞዉን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃ የ9ኛ
ክፍል ተማሪ የነበረው ልጃቸዉ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ሊያልፍ መቻሉን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልፅዋል።
የወጣት እሸቱ ወርቁ የቀብር ስነ-ስርአት እሁድ በከተማዋ የተፈፀመ ሲሆን በተማሪዉ ግድያ ቅሬታ ያደረባቸዉ ነዋሪዎች በቀብር ስነ-ስርዓት ዕለት ተመሳሳይ ተቃውሞ ማካሄዳቸዉ ታውቋል።
ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ባካሄዱ ጊዜ የፀጥታ ሀይሎች አስለቃሽ ጢስን በመጠቀም በቀብር ስነ-ስርአት በሚመለሱ ነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ እርምጃ መዉሰዳቸዉን ለመረዳት ተችሏል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ደቡበ ምዕራብ በ80
ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኘዉ የጊንጪ ከተማ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች ተካሂደዉ በርካታ ሰዋች መገደላቸዉ ይታወሳል።
ከወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል ተካሂዶ በነበረዉ በዚሁ ተቃዉሞ ጊንጪ ከተማ የዚሁ መነሻ መሆኗ የሚታወስ ሲሆን በከተማዋ አሁንም ድረስ አለመረጋጋት መኖሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በክልሉ ለወራት ዘልቆ በቆየዉ ተቃውሞ ወደ 400 የሚደርሱ ሰዎች በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ግድያ እንደተፈፀመባቸዉ ሂዩማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ይፋ ባደረገዉ ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።
ኢሳት
No comments:
Post a Comment