Wednesday, October 28, 2015

የሐይለማርያም ደሳለኝ ጅል ፖለቲካ ሕወሓት ከሚተገብረው ሐቅ የተለየ ነው::



Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) - እንደኔ ሐይለማርያም ደሳለኝ የሚናገረው ንግግር ሁሉ ጊዜውን ያላገናዘበ ሕዝብ የሚያውቀውን ጉዳይ ያልመዘነ በእውነት ላይ ያልተመሰረተ በደመነፍስ የሚናገረው የጅል ፖለቲካ ድምር ውጤት ነው::የተመከረውን እና የተባለውን ሁሉ መልሶ የሚያስተጋባ በጥቂት ቡድናዊ ማፊያዎች የሚነዳ የአገር መሪ አለ ብሎ መናገር አንድም እርግማን ሰፋ ሲልም አንገትን የሚያስደፋ ነው::ሃይለማርያም እንደ ጠ/ሚኒስትር ብንወስደው እንኳን በፖለቲካ ያልበሰለ ገና እንጭጭ በራሱ የማይተማመን ራሱን ያላገኘ ከርታታ (ፖለቲከኛ?) ነው::

በየመድረኩ ቀርቦ የሚናገረው በጭንቀት መሆኑ ያሳብቅበታል::ለጋዜጣዊ መግለጫ ሲቀርብ የሚተነፍሳቸው ትንፋሾች ሰው ሰራሽ እንደሆኑ ራሱ በራሱ ላይ ያቃጥራል::ለሚመልሳቸው መልሶች ሁሉ ሃይል የተቀላቀለ ድምጽ በማውጣት ራሱን እንደ ባለስልጣን አድርጎ ለመሳል መሞከሩ ውሸታምነቱን ይናገርበታል::ለሚጠየቀው ጥያቄ እንኳን በፊት ለፊት ይቅርና ዙሪያ ጥምጥም ለመመለስ አለመቻሉ ልምድ አልባ እና ሰነፍ መሆኑን ያሳያል::በፖለቲካው አለም ይህን ያህል አመቶ ኖሮ ለራሱ የማይገዛ ሕዝብን ማሳመን ያልቻለ በነዱት የሚሄድ ሰው ቢኖር ሃይለማርያም ነው::በፍጹም መሻሻል አይታይበትም ያው እንደተርመጠመጠ ዛሬም አለ::

በትጥቅ ትግል መንግሥት ለመቀየር እየሠሩ ያሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ውጤት እንደማያመጡ እርግጠኞች ነን በማለት መናገሩ ምን ያህል ስለ ኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መረጃ እንዳሌለውና አስተላልፍ ይተባለውን ጥላቻ ከማሳየቱም በላይ እርግጠኛ ነው ማለት በውስጥ አለመተማመኖች እንዳሉ ግልጽ ያደርጋል::በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ተቃዋሚዎች ውጤት ማምጣት ካልቻሉ በመንግስት መሪዎች ዘንድ አሊያም በጠ/ሚ ዘንድ ቃላቶችን እና አትኩሮቶችን ማግኘት ቻሉ?ካለምንም ምክንያት የፍራቻ ቃላቶችን ለመተንፈስ ለምን በወያኔ በኩል ተፈለገ?የሕወሓት ፖለቲካ ችግሩ ተከታይ ጥያቄዎችን የሚያስከትሉ የላሞኛችሁ ጉዳዮችን መናገር ላይ ነው::ሕወሓት በፍርሃት ስለራደ መሰሪ እና ገዳይ ቡድን ነው::በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ተቃዋሚዎች ምን ያህል ስጋት እንደሆኑ በገሃድ የወያኔ ድርጊቶች እና ቃላቶች እያመለከቱን ነው::

በፖለቲካ ጫና የተሽመደመዱ ዜጎች ምድር በተጭበረበረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለድህንነት የተዳረጉ ሕዝቦች በሞሉበት አገር ዜጎች በአስተሳሰባቸው ብቻ ተይዘው ወህኒ የሚወረወሩበት ያልታጠቁ ዜጎች እንደ ጦር ወንጀለኛ አሸባሪ ተብለው እስከሞት የሚፈረድባት ፍትህ አልባ አገር ጥቂት ባለስልጣናት ባደራጁት የዘረፋ ቡድኖች የሃገር እና ሕዝብ ሃብት በሚበዘበዝባት አገር የፖለቲካ መሪዎች እና የሃይማኖት ምሁራን ካለወንጀላቸው በሚሰቃዩባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሃገር እየበለጸገ እያደገ ነው ማለት በሕዝብ ላይ ያለውን ንቀት ያሳያል::የሃሳብ ልዩነት ያላቸው በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡ እስር ቤት እንደሆኑ ሃይለማርያም ዘንግቶታል::በእጁ ሊገባለት ያልቻለውን እና በዳበረ መረጃ ማንነቱን ያወቀውን ዲያስፖራውን ለማታለል ሕወሓት የማይቧጥጠው ነገር የለም::ሃይለማርያም ተመክሮ የሚዘላብደው እና ሕወሓት የምታራምደው እኩይ ተግባር የተለያዩ ናቸው::

No comments: