Thursday, October 8, 2015

ስመ ገናናው ዓለማቀፋዊው የነጻነት ፋኖ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ



ታሪክን የኋሊት 
የኔነህ ከበደ
(ስመ ገናናው ዓለማቀፋዊው የነጻነት ፋኖ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ በአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲ አይ ኤ የተገደለው የዛሬ 48 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡ ለመሆኑ ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ ማነው?)
አርጀንቲናዊው ኤርኔስቶ ቼጉቬራ በትምህርቱም በሙያውም፣ ሐኪም ቢሆንም ዓለም በብዙ የሚያወቅው በግራ ክንፈኛ ተዋጊነቱ ነው፡፡
ኤርኔስቶ ቼ ጉቬራ በዓለም ዙሪያ በነፃነት አላሚ ወጣቶች ልቦና ውስጥ እንዳደረ ቦሊቪያ ውስጥ በዓላማ ተፃራሪዎቹ እጅ የገባውና የተማረከው የዛሬ 48 ዓመት በዛሬዋ እለት ነው፡፡
ቼ ጉ ቬራ የቤተሰብ መሠረቱም ሆኖ ሲበዛ ለድሆች፣ ለተገፉና ለተጨቆኑ ተቆርቋሪ ሆኖ አደገ፡፡
በወጣትነት ዘመኑ፣ በብዙ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተዘዋውሯል፡፡
ይህም በዘመኑ፣ በየአገሩ መንግስታት የተጨቆኑ፣ የተገፉ፣ ፍትህ የራቃቸውና የተበደሉትን ዜጐች በቅርበት ለማየት አስችሎታል፡፡
ቼ ይሄን ካየ በኋላ የጭቆናው ቀንበር መሠባበር እንዳለበት አመነ፡፡
በዚያን ዘመን በሜክሲኮ በሙያው እየሠራና በዩኒቨርስቲ እያስተማረ በነበረበት ወቅት ከኩባውያኑ ወንድማማቾቹ ራውልና ፊደል ካስትሮ ጋር ተዋወቀ፡፡
እነሱም በአገራቸው የተንሠራፋውን ጭቆና መታገያ መላ ለመፈለግ በሜክሲኮ መገኘታቸውን ነገሩት፡፡ የቼጉቬራና የካስትሮ ወንድማማቾች እውቂያቸው ወደ ዓላማ አጋርነት ተሸጋገረ፡፡
ወደ ኩባ ለመዝመት የወታደራዊና የሽምቅ ውጊያ ልምምድ ውስጥ ገቡ፡፡
በልምምዱ ቼ ከሁሉም ብልጫ ያለውና የላቀ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡
ጊዜው ደረሰና 82 ሆነው በግራንማ ጀልባ ለታላቁ ተልዕኮ ወደ ኩባ ቀዘፉ፡፡
ጉዞው አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡
ይልቁንም ገና ከማለዳው በመስዋዕትነት የተሞላ እንጂ፡፡
ከባሕር ጉዞው በኋላ የኩባን መሬት ለመቆናጠጥ ባደረጉት ሙከራ ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ተሠዉ፡፡
ቼጉቬራ መድሐኒትና የሕክምና ቁሳቁስ መያዣ ሳጥኑን ጥሎ ቦምብና ጠመንጃውን ለመታጠቅ ተገደደ፡፡
ከገጠማቸው ውርጅብኝ በኋላ እነ ቼ ጉ ቬራ ፊደል ካስትሮና ከ20 ያልበለጡ የሐምሌ 26 ንቅናቄ ተዋጊዎች ነበሩ፡፡
በሴራ ማይስትራ ተራራ፣ ተገን ይዘው፣ በዓላማ ፅናት ተባባሪና ደጋፊዎቻቸውን አብዝተውና ተዋግተው፣ የጄኔራል ባቲስታን ጨቋኝ አስተዳደር አሸቀነጠሩት፡፡
ክስተቱም የኩባ አብዮትም ተባለ፡፡
ቼ-ጉቬራ ከአብዮቱ በኋላ ከስልጣኑም ከሹመቱም ባይቀርበትም ሌሎች ነፃነት የሚሹ ሕዝቦች አሉና እነሱን ልርዳ ብሎ ዴሴቲቱን ተሠናበተ፡፡
በኮንጐ ኪንሻሳ፣ በሞቡቱ ሴሴሴኮ ላይ፣ አምፀው የተነሱትን ወገኖች ለመርዳት ምስራቅ ኮንጐ ደረሰ፡፡
በዚያ የነበረው የትግል ዝግጅት የተዝረከረከ መሆኑ አላረካህ ቢለው፣ ከኮንጐ ወጥቶ ወደ ቦሊቪያ አመራ፡፡
ቦሊቪያ ውስጥ፣ እንደ ወንበዴ የቆጠሩት የዓላማ ተፃራሪዎቹ ማረኩት፡፡ የዛሬ 48 ዓመት በዛሬዋ እለት በአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት/CIA/ ቦሊቪያ ውስጥ ተገደለ፡፡
የዓላማ ተፃራሪዎቹ እንደ ሽፍታ የሚቆጥሩት ቼ ጉቬራ፣ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የነፃነት ተዋጊና ዓለም አቀፍ አርበኛ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡
Source: SHEGER FM 

No comments: