በኢዮኤል ፍሰሐ
በቀዳሚዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ፤ በ1951 ዓ.ም ወደ ሐረር ጦር አካዳሚ በማቅናት ለሶስት ዓመታት በዚሁ አካዳሚ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በ1954 ዓ.ም ከአካዳሚው በምክትል መቶ አለቃነት ተመረቁ፡፡ ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ በአካዳሚው ውስጥ በአልጣኝነት ተመድበው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ ረዳት ሆነው ሰርተዋል፡፡ ቀጥሎም በምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ የትምህርትና ዘመቻ መምሪያ የትምህርት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በ1970 ዓ.ም ውጪ ጉዳይ ሚኒስተር መ/ቤት ተመድበው በጅቡቲ ለ10 ዓመታት ያህል በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ ከጅቡቲ መልስ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ዋና ክፍል ኃላፊ ሆነው ለሀገራቸው ግልጋሎት ሰጥተዋል፡፡ በ1988 ዓ.ም በገዛ ፍቃዳቸው ጡረታ የወጡ ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ አንስቶም በግል ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ የዚህ ሁላ ልምድ ባለቤት የትላንትናው መኮንን እና ዲፕሎማት የዛሬው ፖለቲከኛ፤ አርጋው ካብታሙ ናቸው፡፡
የሻለቃው የፖለቲካ ተሳትፎ መችና እንዴት ተጀመረ?
ሻለቃ አርጋው፣ የፖለቲካ ተሳትፎዋቸውን አሃዱ ብለው የጀመሩት በ1996 ዓ.ም መኢአድን በመቀላቀል ነው፡፡ ወደ ሰላማዊ ትግል የገቡበትን ምክንያት ሲያስረዱም፡- ‹‹አምባገነንነት በጣም ስላማረረኝና ስለከነከነኝ የተቃውሞ ፖለቲካ ጎራውን ለመቀላቀል ወሰንኩ›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳት የሚፋጀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ረመጥ፣ ሻለቃውን ለመጎብኘት ጊዜም አልፈጀበትም፡፡ መንግስት በዝረራ በተሸነፈበት ምርጫ 97 የቅንጅት አመራሮችን ወደ እስር ቤት ሲያግዝ፤ ወደ እስር ቤት ከተጋዙት የቅንጅቱ አመራሮች መሃል ሻለቃ አርጋው አንዱ ናቸው፡፡ በማዕከላዊ ለሁለት ወራት በጭለማ ቤት የታሰሩ ሲሆን፤ ከማዕከላዊ እንደወጡም በአለምበቃኝና ቃሊቲ ወህኒ ቤቶች ታስረዋል፡፡ ለ 1 ዓመት ከ6 ወር ያህል ከታሰሩ በኋላ የቅንጅቱ አመራሮች ከእስር ሲፈቱ ከእስር ተለቀዋል፡፡ ከወህኒ ቤት እንደወጡም በመኢአድ ውስጥ በሥራ አስፈፃሚነት የፖለቲካ ተሳትፎዋቸውን የቀጠሉ ቢሆንም፤ በፓርቲው ላይ አንዳንድ የአካሄድ ችግሮች ስላስተዋሉ፤ ፓርቲውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ ይታወቃል፡፡ መኢአድን ለቀው አፍታም ሳይቆዩ፤ በ2002 ዓ.ም አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲን (አንድነትን) ተቀላቀሉ፡፡ ፓርቲው ለአገዛዙ ሎሌዎች ተላልፎ እስከተሰጠበት፣ ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በፓርቲው ውስጥ ከተራ አባልነት እስከ ብሔራዊ ምክር ቤት ድረስ በመዝለቅ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡
ከሀገር እንዳይወጡ ስለተደረገበት ቀንና ስለቀረበላቸው ምክንያት
ሻለቃ አርጋው ካብታሙ፣ ሚያዚያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም በሀገረ አሜሪካ የሚገኘው ልጃቸው ጋብቻ ሊፈፅም መሆኑን ተከትሎ፤ የጋብቻው ሥነ ሥርአት ላይ ለመገኘት አስፈላጊ የሚባለውን የወረቀት ሥራ አጠናቀው፤ ቦሌ ዓለም-ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ደረሱ፡፡ በወቅቱ የያዟቸው ሻንጣዎች ወደ አውሮፕላኑ ከተጫኑ በኋላ፤ ወደ አውሮፕላኑ በማቅናት ላይ ሳሉ፤ የኢሚግሬሽንና ደህንነት መ/ቤት ሰራተኞች የሻለቃውን ፓስፖርት በመንጠቅ ከሀገር መውጣት እንደማይችሉ ገለፁላቸው፡፡ ምክንያቱን ቢጠይቁም ከኢሚግሬሽን ኃላፊዎች በኩል አንድም ምክንያት አልተሰጣቸውም፡፡ ፓስፓርታቸውን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም፤ ሙከራቸው አልተሳካም፡፡ የዚህ ፅሑፍ ፀሐፊ ይህን በማስመልከት ሁለት የሕግ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ከሀገር እንዳይወጣ እንዴትና በምን መልኩ ይታገዳል፤ የሚያግደው አካልስ ማን ነው?›› ፣ ‹‹የኢሜግሬሽንና ደህንነት መ/ቤት አንድን ሰው ከሀገር እንዳይወጣ የማገድ ስልጣን ተሰጥቶታል ወይ?›› በሚሉት ነጥቦች ላይ የሕግ ባለሙያዎቹ አስተያየት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
በጥብቅና ሙያ የተሰማሩት የቀድሞ አንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ገበየሁ ይርዳው፣ ‹‹ፍርድ ቤት አንድን ሰው፣ ከሀገር እንዳይወጣ በተለየ ሁኔታ የሚገድብባቸው ሁኔታዎች አሉ›› ይላሉ፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ፡- ‹‹በፍርድ ቤት ክስ የቀረበበትና በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እስኪጣራ ድረስ ከሀገር እንዳይወጣ ይደረጋል›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በአንፃሩ ሻለቃ አርጋው በወንጀል የማይፈለጉ እንዲሁም ፍርድ ቤት ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ የጣለባቸው ሰው እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ ፓስፖርታቸውን የተነጠቁትም ሆነ ከሀገር መውጣት እንደማይችሉ የገለፁላቸው የኢሚግሬሽንና ደህንነት መ/ቤት ሰራተኞች መሆናቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ገበየሁ ይርዳው፣ ይህንን በማስመልከት እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹ኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት አይደለም! አንድን ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ሊያግድ የሚችለው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ኢሚግሬሽን ይህን ካደረገ፤ ሕገመንግስታዊ መብት ጥሰት አካሂዷል ልንለው እንችላለን›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በሌላ በኩል በጥብቅና ሙያ የካበተ ልምድ ያዳበሩትና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ክሶች በመያዝ ለተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ በመሆን የሚቆሙት፤ ጠበቃ አምሃ መኮንን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
‹‹በሕግ ጥበቃ የተደረገለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከሀገር የመውጣት፣ ወደ ሀገር የመግባት በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጠ መብት አለው፡፡ ይሄ መብት በሕገ-መንግስቱ ላይ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ አልተቀመጠለትም፡፡ በዚህና በዛ ምክንያት ወይም በልዩ ሁኔታዎች ይሄ መብት ሊገደብ ይችላል ተብሎ የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ የለም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ኢሚግሬሽን ፓስፖርት ነጥቆ፤ አንድን ሰው ከሀገር እንዳይወጣና ወደ ሀገር እንዳይገባ ክልከላ ወይም እንቅፋት ከፈጠረ የሰውየውን፣ ከሀገር የመውጣትና ወደ ሀገር የመግባት መብት ብቻ ሳይሆን ቀጥታ ሕገ-መንግስቱን የሚጣረስ ድርጊት ነው እየፈፀመ ያለው›› በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ጠበቃ አምሃ፣ የኢሚግሬሽን መ/ቤት ኃላፊነት ሲያስረዱም፡- ‹‹የኢሚግሬሽንና ደህንነት መ/ቤት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ፓስፖርት መስጠት፣ ማደስና የመሳሰሉትን ከመከወን ባለፈ ሌላ ሚና የለውም›› ይላሉ፡፡
ሻለቃ አርጋው ካብታሙ፣ ይህ ፅሁፍ ተጠናክሮ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ከኢሚግሬሽን ኃላፊዎች በኩል ከሀገር መውጣት የማይችሉበት ምክንያት እንዳልተገለፀላቸውና ፓስፖርታቸውም እንዳልተመለሰላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዚህ ፅሑፍ ፀሐፊ በቀጣይነት፣ ፓስፖርታቸውን እንደ ሻለቃ አርጋው የተነጠቁ፤ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባላትን፣ የሚመለከታቸውን የኢሚግሬሽን ኃላፊዎችና የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎችን በማነጋገር ትንታኔያዊ ሐቲት (Feature Article) አዘጋጅቶ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋል፡፡
No comments:
Post a Comment