Saturday, October 3, 2015

የኢሕአዴጉ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት-ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ፣እና የሌቭ ቶልስቶይ ጄነራል

በዚህ ጽሑፍ የማነሣቸው ርእሰ ጉዳዮች በሦስት የተከፈሉ ናቸው፡፡ አንደኛው፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት መዳፍ ሥር ስለ መውደቅ፤ ኹለተኛ፡- የፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬን ገጸ ሰብእና (persona) በኹለት ወጎች ሥር ማብራራት ሲኾን፣ ሦስተኛው፡- የርእሰ ጉዳዮቹ ማጠቃለያ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲውን የመቆጣጠር ሒደት እና ሥልጠና
ኢሕአዴግ፣ ስለ ፖለቲካ ስትራቴጅ እና አቅጣጫ በ1997 ዓ.ም. ባወጣው ሰነድ ላይ፤ ስለ ሀገሪቱ ምሁራን ያለውን አስተያየት እንደ ሚከተለው አቅርቧል፡፡ እንደ ኢሕአዴግ አመለካከት፣ ምሁሩ ምንጊዜም ወደ ሥልጣን ማማተሩ ስለማይቀር በተቻለ መጠን የሥልጣን መወጣጫ መንገዱ ተዘግቶ መያዝ አለበት፡፡ ይህን ለማሳካት ምሁሩ የንዋይ ፍላጎቱ በተቻለ መጠን እንዲሟላለት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመኾኑም በሞያው ዙሪያ ባሉ ሳንካዎች እና ጥቅማጥቅሞች ተጠምዶ ወደ ሀገራዊ ጥያቄዎች ሳይሻገር በእዚያው ማጥ እየዳከረ እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ከዛሬ ስድስት መቶ ዓመት በፊት፣ ታላቁ ኢትዮዮጵያዊ ሊቅ፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ከደረሷቸው መጻሕፍት መካከል ‘መጽሐፈ ምስጢር’ ብለው በሰየሙት ድርሳናቸው ውስጥ፣ ሳይማሩ እናስተምራለን ብለው ስለተነሡ የቤተ መንግሥት ባለሟሎች አቅርበውት የነበረውን ትችት አኹን ኢሕአዴግ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ እያደረገ ካለው ሥልጠና ጋር በማነጻጻር “የዩኒቨርስቲው በር ተሰብሯል፤ ዐምዶቹም ተነቃንቀዋል” በሚል ርእስ ባለፈው ሳምንት በሌላ ኅትመት በተስተናገደ ጽሑፍ ማቅረባቸን ይታወሳል፡፡ በዚህ ዝግጅት የጽሑፉ የተወሰነ ክፍል ለአጽንዖተ-ነገር ሲባል ተዳሷል፡፡
የቅዱሱን ተግሣጽ በኹለት ምድብ በመክፈል በመጀመሪያ፣ የትዝብታቸውን መነሻ ቀጥለን ደግሞ፤ ድርጊቱ ያስከተለውን አሉታዊ ዉጤት እናያለን፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ትንተና
የተወሰኑ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት በመፈለግ ወደ ዋሻ፣ አድባራት እና በረሓ ገቡ፡፡ መንፈሳዊ ተጋድሎ አልኾንላቸው ሲል በረሓውንና ዋሻውን ለቀው ወደ ቤተ መንግሥት ጠጋ አሉ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም አዘውትረው መመላለስ ጀመሩ፡፡ ከማዘውተራቸው ብዛት የቤተ መንግሥቱን አመኔታ እና ይኹንታ ተቀዳጁ፡፡ የሹማምንቱን ቅቡልነት ቢያገኙም በየበረሓው ወጣትነታቸውን በከንቱ አባክነው በዘመኑ ከቤተ ክርስቲያን ብቻ ይገኝ የነበረውን ትምህርት ሳያገኙ ስለቀሩ፣ የቤተ መንግሥት ባለሟልነታቸውን ተጠቅመው ያልተማረውን ምእመን እናስተምራለን ብለው ተነሡ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ኹኔታው ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት በኹለት ዘይቤ (Metaphor) ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም፡- “በሮቿ ተሰበሩ” እና “አዕማዷ ተነቃነቁ” የሚሉት ናቸው፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አቀራረብ፣ አኹን በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ የሚካሔደውን ኹኔታ በሚገባ ለመረዳት እንደ መነጽር ይኾነናል፡፡ ከኹሉ አስቀድሞ፣ የአባ ጊዮርጊስ ‘መምህራን’ እናስተምራለን ብለው የተነሡት ራሳቸው ሳይማሩ ያልተማሩትን ሰዎች ለማስተማር ነው፡፡ በእኒህ ኹለት ዓመታት ውስጥ፣ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እናሠልጥን ብለው የተነሡት የመንግሥት ሹመኞች ራሳቸው በሚገባ ሳይማሩ፣ አልተማሩም የሚሏቸውን ሳይኾን፣ የተማሩትን ክፍል ለማስተማር መነሣታቸው ነው፡፡
ከዚኽ አንጻር አባ ጊዮርጊስ የታዘቧቸው መምህራን ከአኹኖቹ እናስተምር ባዮች በእጅጉ የተሻሉ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይኸውም የቀድሞዎቹ፣ ራሳቸው ባይማሩም እናስተምር ያሉት ያልተማሩትን ሲኾን የእኛዎቹ ግን እናስተምር ብለው የተነሡት የተማሩትን በመኾኑ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በዚህ ዘመን ቢኖሩ ኀዘናቸው ምን ያኽል በበረታ ነበር!!
አባ ጊዮርጊስን በእጅጉ ያሳዘናቸው እና ያስገረማቸው፣ ቤተ መንግሥት በፍጥረቷ የአስተዳደር መንገድ መቀየስ እንጂ የዕውቀት ምንጭ ወይም የምሁርነት ምኩራብ ሳትኾን ዐዋቂዎች ነንና እናስተምር እያሉ የሚነሡባት ማእከል ኾና ስላገኟት ነው፡፡ አኹን ወዳለንበትም ጊዜ ስንመጣ፣ ብዙዎችን እያሳሰበ ያለው በየዩኒቨርስቲው እናሠልጥን እያሉ የሚመጡት ሰዎች አኳኋን ነው፡፡ ልክ እንደ አባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’ አስቀድመው ወደ በረሓ ከወጡ በኋላ ተመልሰው ቤተ መንግሥቱን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ፡፡ ከዚያም ቤተ መንግሥቱም ዩኒቨርስቲውም አይቅርብን ብለው የዩኒቨርስቲውን መምህራን እናስተምራለን ብለው ብቅ አሉ፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ኀዘን የበረታው፣ እኒኽ ‘ምሁራን’ ቤተ ክርስቲያን እንደ በሮቿ የምታያቸውን የነቢያት አስተምህሮ ስለሰበሩ እና በምሰሶ የተመሰሉትን የሐዋርያትን ዶግማ እና ቀኖና ስላነቃነቁ ነው፡፡ ብዙዎችን ታዛቢዎች በእጅጉ እያሳሰባቸው ያለው በአስተማሪነት እና በአሠልጣኝነት ስም፤ ዩኒቨርስቲው የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የምርምር እና የመሳሰሉት ዕሴቶች ገዳም ኾኖ ሳለ፤ ሊቃነ ማእምራኑ (ፕሮፊሰሮቹ) ያስቀመጧቸውን ሚዛኖች (በሮች) በመስበር አዕማዷን ስላነቃነቁት ነው፡፡
የቤተ ክህነቱ በር እንደተሰበረው ኹሉ፣ የየኒቨርሲቲውም በር ተሰብሯል ስንል ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹንም ኾነ መምህራኑን መርጦ የመቀበል መብቱ ተገፍፎ በፖለቲካ ትእዛዝ እንዲሞላ በመደረጉ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት ኾኗል ማለታችን ነው፡፡
የአዕማዷን መነቃነቅ በምናነሣበት ጊዜ በዋናነት የምናቀርበው፣ ዩኒቨርስቲው የነበረው የማስተማር ሥነ ዘዴ ተሽሮ ከፖለቲካ ኃይሉ በመጣ ማዘዣ፣ እነርሱ ይበጃል የሚሉትን አካሔድ ተግባራዊ እንዲያደርግ መገደዱን ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው፣ ከቢፒአር እስከ ቢኤስሲ እና አንድ ለአምስት አደረጃጀትን መምህራኑ ሳይመክሩና ሳይዘክሩበት ዩኒቨርስቲው እንዲከተል መደረጉ ነው፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’፣ የመንግሥትን ኃይል እና ቤተ ክርስቲያንን ገና በሚገባ ያልተቆጣጠሩ ሲኾን፣ የአኹኖቹ ምሁሮች ግን ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ ለያዙ ኃይሎች ተጠሪዎች ናቸው፡፡ በመኾኑም ከንኡሳን (ደቃቂን) ሓላፊዎች እስከ ዐቢይ አለቃው - ፕሬዝዳንቱ፣ ድረስ ለቤተ መንግሥቱ የፖለቲካ ቀኖና ተገዥ እና ተኣማኒ በኾኑ እሺ ባዮች እንዲያዝ ተደርጓል፡፡
እውነተኛ ዩኒቨርስቲያዊ ይትበሃል ተሽሮ፣ የበረሓ ጀግኖች እንዳፈተታቸው የሚናኙበት ኾነ፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱንም፣ ዩኒቨርስቲያዊ ልዕልናው ስለ ተገፈፈ ሳይንሳዊ እና ሞያዊ አሠራሩ ተሻረ፡፡ በቦታውም ከፖለቲካው ጽሕፈት ቤት በሚመነጭ ኢሕአዴጋዊ ትእዛዝ በሩን አፈረሱት፤ ዐምዱንም አነቃነቁት፡፡ ካርል ያስፐርስ የገለጹት ‘አማናዊው ዩኒቨርስቲ’ እና እውነተኞቹ ምሁሮቿ ስለ እነዚህ ሰዎች አድራጎት አብዝተው ያዝናሉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሲቋቋም፣ ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የበሩን ኹለት አዕማድ ‘በዕውቀት’ እና ‘በሠናይት’ (Virtue) በመመሰል የዘመሩለት፣ ማንም ሰው ሊያየው በሚችለው መልኩ መሠረቱ ተናጋ፤ ውድቀቱም ተቃረበ፡፡

የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ገጽታ ከኹለት ትረካዎች አንጻር ሲፈተሽ
ፕሬዝዳንት አድማሱ ለአራት ዓመታት የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራር ኾነው በቆዩባቸው ጊዜያት፣ እኔም እንደ አንድ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ አባል ኾኜ በማገለግልበት ወቅት ስለ ሰውዬው ያየኹትንና የታዘብኩትን ጉዳይ በሚከተሉት ወጋዊ ትረካዎች ለማቅረብ እሞክራለኹ፡፡ ይህንንም ለመተግበር ፕሬዝዳንቱ በተለያዩ ወቅቶች በዩኒቨርስቲው ውስጥ ካደረጉት ንግግር፤ በየጊዜው የዩኒቨርስቲውን አስተዳደር እና ሒደት በሚመለከት ጽፈው ወደተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በላኳቸው ሰነዶች እናም በመጨረሻም ዩኒቨርስቲው ልማታዊ ወይም ተግባራዊ መንገድ ይዞ መጓዝ አለበት ብለው ደጋግመው ካቀረቡት ዕቅድ በመነሣት ነው፡፡
ሀ. ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እና የካውንት ሌቭ ቶልስቶይ ጀነራል
ከዚህ የሚከተለውን ትረካ የወሰድኩት፣ ከሌቭ ቶልስቶይ “ጦርነት እና ሰላም” ከሚለው ታላቁ ድርሳን ነው፡፡ ለአንባብያን እንዲመች ለማድረግ ሐሳቡ ላይ ትኩረት በመስጠት እና በማገናዘብ እንደሚከተለው አቀርባለኹ፡፡
የታሪኩ መቼት፣ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “የናፖልዮኒክ ጦርነት” ተብሎ በሚጠራው እና ናፖሊዮን ቦናፓርት ሩስያን ወርሮ ለመያዝ ባካሔደው ጦርነት ወቅት ነው፡፡ የፈረንሳይ ሠራዊት በዚያን ጊዜ በጦርነት ዐውድማ ማንም ተፎካካሪ ኃይል ስላልነበረው፣ የወረራ አቅጣጫውን ወደ ሩስያ ባደረገበት ወቅት ትልቅ መደናገጥን እና ፍርሀትን በመላው ሀገሪቱ አሳደረ፡፡
የወራሪውን ሠራዊት ለመቋቋም በአንድ የተወሰነ ግንባር ያሉ የሩስያ ጀነራሎች የመከላከል ዕቅድ ለመንደፍ እና በአጠቃላይ የጦርነት ስልት ለማዘጋጀት ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ከቶልስቶዩ ጀነራል በስተቀር ኹኔታውን በጥሞና በመከታተል የተቻላቸውን የሐሳብ አስተዋፅኦ ለማበርከት ሞክረዋል፡፡ በአንጻሩ ግን ጀነራሉ ስለ ውጊያው ስትራቴጂ የበኩሉን ድርሻ ማቅረብ ከመዘንጋቱም በላይ የጉዳዩ ክብደት ሳያሳስበው እያንቀላፋ ነበር፡፡ የጀነራሎቹ ስብሰባ አልቆ ኹሉም የድርሻቸውን የውጊያ ሚና ከተከፋፈሉ በኋላ ተለያዩ፤ ጀነራሉም የተወሰነ ድርሻውን በሓላፊነት ተረክቦ ወደ አንደኛው ግንባር ተላከ፡፡
በበነጋው ይኼው ጀነራል የዕዙን ወታደሮች ይዞ ከጦር ሜዳው ደረሰ፡፡ በሥሩ ያሉት መኮንኖች ጦሩን ቦታ ቦታ ካስያዙ በኋላ ፍልሚያ ሊጀምር ትንሽ ሲቀረው ጀነራሉ ከቦታው ተሰወረ፡፡ አብረውት የነበሩት የጦር አመራሮች በመገረም የጀነራሉ ምክትል ዕዙን ተረክቦ እንዲመራ በመስማማት በጣም ከከረረ ውጊያ በኋላ ሩስያውያኑ ድል ቀንቷቸው የወራሪውን ኃይል ለመመለስ ቻሉ፡፡
ከጦርነቱም በኋላ ባገኙት ድል በመደሰት ሞቅ ያለ ግብዣ ተደርጎ በትልቅ ድግስ ላይ እንዳሉ ጀነራሉ በነጭ ፈረስ ላይ ኹኖ ከግብዣው አካባቢ ብቅ አለ፡፡ ይህን ያዩ መኮንንኖች ወደርሱ ቀርበው፣ “በጣም የምታስገርም ሰው ነህ፡፡ ከትላንት ወድያ የጦርነቱን ፕላን ስናወጣ አንተ ታንቀላፋ ነበር፤ ትላንት ጧት ደግሞ እንድታዋጋ ተሰጥቶኽ ከነበረው ግንባር ተሰወርክ፡፡ እንደዚህ ዐይነት ድርጊት ወደ ጦር ፍርድ ቤት እንደሚያስወስድኽና ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያሰጥኽ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡” በማለት በቁጣ ተናገሩት፡፡
ጀነራሉ፣ ተናደው በቁጣ ላናገሩት መኮንኖች የሚከተለውን መልስ ሰጣቸው፡፡ “ከኹሉ አስቀድሞ ንዴታችኹ ይገባኛል፡፡ኾኖም ግን አንድ ለናንተ የተሰወረ እና እኔ ደኅና አድርጌ የማውቀው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸዉም ከእናንተ ይበልጥ እኔ ራሴንና ማንነቴን ጠንቅቄ ስለማውቅ ነው፡፡ እኔ የጦርነቱ ፕላን ሲወጣ ሙሉ ለሙሉ ተካፋይ ብኾን ኖሮ ዛሬ ድል ከእናንተ ጋር አትኾንም ነበር፡፡ ትላንትናም ቢኾን በጦር ሜዳው ግምባር ዋናው አዋጊ ብኾን ኑሮ ከድል ይልቅ ዕጣችኹ እንዲኽ አያምርም ነበር፡፡ ዐያችኹ፤ ከኔ ይልቅ ምክትሎቼ የተሻሉ አዋጊዎች ናቸው ብዬ ስላመንኩ ሓላፊነቱን ለእነሱ ትቼ ዘወር አልኩ፡፡ በእኔ ዐተያይ ሀገር መውደድ ማለት የራስን አቅምን ሳይፈትሹ አደርገዋለኹ በሚል ድፍረት መንቀሳቀስ ሳይኾን የራስን ችሎታ እና አቅም በሚገባ አጢኖ የተሻለ ሰው ከተገኘ የሥራ ምድቡን ለቆ ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ለሀገር እና ለወገን ሲባል ከቦታው ዘወር ማለት ነው፡፡”
በዚህ ትረካ ያየነው፣ የቶልስቶዩ ጀነራል ችሎታ ባይኖረውም ሀገሩን የሚወድ እና የሞራል ላቂያ ያለው ሰው ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ በእሱ አስተያየት፣ ሀገር መውደድ ማለት ከኹሉ አስቀድሞ ችሎታም ባይኖር የያዙትን ሹመት የሙጥኝ ብሎ አልለቅም ከማለት ለተሻለ ሰው ቦታውን መልቀቅ ማለት ነው፡፡
ወደ ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ስንመለስ፤ ራሳቸውን ከማወቅ አንጻርም ኾነ ለያዙት ቦታ ከእርሳቸው የተሻለ፣ እዚኹ ግቢ ውስጥ፣ በርከት ያለ ሰው መኖሩን እያወቁ እንደ ቶልስቶዩ ጀነራል ዘወር አለማለታቸውን ስንታዘብ ስለ ራሳቸው የተሳሳተ ግምት እንዳላቸውና ሀገር ወዳድነታቸውን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል ብለን እናስባለን፡፡
ምናልባት በዚህ ድምዳሜ ላይ ፕሬዝዳንቱ፣ ሀገሪቱን በበላይነት ከሚያስተዳድሩት ውስጥ ለሥራቸው የማይመጥኑ መኖራቸው እየታወቀ፣ ምነው እኔ ብቻ ተነጥዬ ቦታህን ለሚችል ሰው ልቀቅ መባሌ፤ ብለው ይጠይቁ ይኾናል፡፡ ጥያቄያቸው የተወሰነ እውነታ አለው፡፡ ኾኖም ግን፣ በሀገራችን የቅርብ ታሪክ ውስጥ ለሀገር እና ለወገን ሲሉ ቦታቸውን የለቀቁ እንዳሉ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሚለው አስደማሚ መጽሐፋቸው ላይ ስለ ቦታ መልቀቅ የሚከተለውን ታሪክ ያጫውቱናል፡፡
ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የአፍሪካን የግብርና ሚኒስትሮች በአጠቃላይ ወደ አሜሪካ መጥተው እንዲወያዩ የስብሰባ ጥሪ አቀረቡ፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ቢኾኑም ከሩዝቬልት ጋር ተገናኝቶ ስለ እርሻ ብቻ ሳይኾን እንግሊዞችን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ለማውረድ ትብብራቸውን እንዲለግሱ ለመጠየቅ ታስቦ ነበር፡፡ ለዚህ ሥራ ብቁ የሚኾኑት ከአቶ መኮንን ይልቅ አቶ ይልማ ደሬሳ መኾናቸውን አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ከወንድማቸው ከአቶ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ጋር ተመካክረው ሐሳቡን ለጃንሆይ አቅርበው በማስወሰን አቶ ይልማ ደሬሳ ሔደው ከሩዝቬልት ጋር በመነጋገር ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ አግኝተው ተመልሰዋል፡፡
ለ. ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እና የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች
“ሐኪሞች በሌሉበት ምግብ አብሳዮች የጤና አማካሪ ኾነው ብቅ ይላሉ፡፡”
ፕሌቶ
ፕሌቶ “ሪፐብሊክ” በሚለው መጽሐፉ ከሞያቸው ውጭ ጣልቃ እየገቡ ችግር ስለሚፈጥሩ ሰዎች በሚከተለው ትረካ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡

አልፎ አልፎ ትልቅ ግብዣ በሚካሔድበት እና ተጋባዡ ቦታ ቦታውን ይዞ በሚታደመበት አዳራሽ ውስጥ ምግብ የሚያበስሉ ወጥ ቤቶች እንግዶቹ ወዳሉበት ሥፍራ በመሔድ ራሳቸውን እንደ ሕክምና ባለሞያ በመቁጠር የጤና አማካሪ ኾነው ይቀርባሉ፡፡ በመኾኑም ከጠረንጴዛ ወደ ጠረንጴዛ በመዞር “ይቺን ብትበላ ትስማማኻለች፤ ይኼኛውን ምግብ ብዙ አትድፈር፤ በተለይ ደግሞ ይህ ዐይነቱ ምግብ ለደም ብዛት አና ለኩላሊት ፈውስ ነው፤” ወዘተ የሚል ምክር ይለግሳሉ፡፡ በእንዲህ ዐይነት ከሞያቸው የራቀ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳሉ ወደ ግብዣው ቦታ እውነተኞቹ ሐኪሞች ወይም ዶክተሮች ብቅ ሲሉ ወጥ ቤቶቹ ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሳሉ፡፡
የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች ሐኪም መስለው መቅረባቸው ጥፋተኛ ቢያሰኛቸውም እውነተኞቹ ሐኪሞች ሲመጡ ቦታውን ለቀው ወደ ማዕድ ቤት መመለሳቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ከዚህ ትረካ ስንነሣ የፕሌቶ ምግብ አብሳዮች እንደ ቶልስቶዩ ጀነራል ለተሻለ ሰው ቦታ መልቀቃቸውን እንገነዘባለን፡፡
ከሞያ እና ችሎታ ዉጭ ቦታን መያዝ በተመለከተ፣ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ዕውቁ የአሜሪካን ፈላስፋ፣ ዊሊያም ጀምስ፣ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ለእኔ የተሰጠኝን አብዛኛውን የሀርቨርድ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍ ባነበብኩ ጊዜ ይህች ሀገር ስንት ገበሬ እንዳጣች ሳስብ አዝናለሁ፡፡” አሉ፡፡ እኔም የፕሬዝዳንት አድማሱን ኹኔታ ሳስብ ሰውዬውን አለቦታቸው በመክተት በሞያቸው ተሰማርተው የጀመሩትን የግብርና ምርምር ቢቀጥሉ ኖሮ ሀገሪቱ ከረኀብ ለመውጣት እና በምግብ እህል ምርት ራሷን ለመቻል ታደርገዋለች ለሚባለው ተጋድሎ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ማጠቃለያ
ጹሑፋችንን የምናጠቃልለው በሚከተሉት ሦስት ጉዳዮች ዙርያ አጠር ያሉ ነጥቦችን በማንሣት ነው፡፡ እነዚህንም ነጥቦች “ዕውቀት”፣ “ጥቅም” እና “እብሪት” በተሰኙ ሦስት አርእስት ከፍለን እናቀርባለን፡፡
ሀ. ዕውቀት
የአንድ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ አመራር ለመኾን የሰውዬው ወይም የሴትዬዋ የዕውቀት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያለ መኾን አለበት፡፡የዛሬ ኃምሳ ዓመት ገደማ በአሜሪካን ሀገር በምሁራኑ አካባቢ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሚኾን ሰው ምን ዐይነት መሥፈርት ማሟላት አለበት? አንድንስ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ብቁ የሚያሰኘው ነገር ምንድር ነው? ፕሬዝዳንትን ለመሠየም የሚያስችሉ ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያላቸውን መመዘኛዎች ማስቀመጥ ይቻላል ወይ? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሣት ረዘም ላሉ ጊዜያት ከተወያዩ በኋላ አምስት ወይም ስድስት መሥፈርቶችን ለይተው አወጡ፡፡
ከተስማሙባቸው ወሳኝ ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ከኹሉም በላይ የተጠናከረ ምሁራዊ ዝንባሌ እና ርእይ ያለው መኾን እንዳለበት፤ በኹለተኛ ደረጃ የአመራር እና የአስተዳደር ችሎታ ያለው መኾን እንደሚገባው ካቀረቡ በኋላ ሌላው ነጥባቸው፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ባለትዳር እና ቤተሰብ ያለው ቢኾን ይመረጣል የሚል ነው፡፡
ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ የአሜሪካን ምሁራን ለፕሬዝዳንትነት አስፈላጊ ናቸው ብለው ከዘረዘሯቸው መሥፈርቶች ውስጥ፣ በእኔ አተያይ፣ ባለትዳር ቢኾን ይመረጣል ያሉትን መለኪያ ብቻ እንደሚያሟሉ ጥርጥር የለኝም፡፡ ዶ/ር አድማሱ ግን ለፕሬዝዳንትነት የበቁት ከላይ በከፊል የተጠቀሱትን መሥፈርቶች በማሟላት ሳይኾን ለፓርያቸው ያላቸው ታማኝነትና ከመጡበት ብሔር ለዚህ ሹመት ፖለቲካዊ አስፈላጊነታቸው ታይቶ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጠንካራ ምሁራዊ እና የአስተዳደር ክህሎት ስለሚጎድላቸው፣ ዩኒቨርስቲው የራሱን ዕቅድ ነድፎ እንደ አንድ አካዳሚያዊ ተቋም ከመተግበር ይልቅ ከመንግሥት ሥራ እየተቆጠረ የሚሰጠው ኾኗል፡፡
ስለኾነም ፕሬዝዳንቱ ምንጊዜም የመንግሥትን ፖሊሲ እና ፕላን ወደ ዩኒቨርስቲ አምጥተው ማስፈጻም ስለሚፈልጉ፣ አኹን ባለበት ኹኔታ የጥናት እና ምርምር ማእከል መኾኑ ቀርቶ “ልማታዊ ዩኒቨርስቲ” ተብሎ እስከ መጠራት ደርሷል፡፡ ከዚህ ላይ እንደ ማሳያ ለማቅረብ የምፈልገው፣ ከስድስት ወራት በፊት ጋዜጠኞችን ሰብስበው በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች መግለጫ ሲሰጡ፤ለዩኒቨርስቲው እንደ ርእይ እና እንደ ግብ አድርገው ካቀረቧቸው አንዱ፣ የበሬ ማድለብን ፕሮጀክት ነው፡፡
እዚህ ላይ በጣም የሚያስገርመው፣ አንድ ዩኒቨርስቲ በዋናነት የአእምሮ ማድለቢያ እንጂ የበሬ ማድለቢያ እንዳልኾነ ብዙ ሰዎች ያውቁታል፡፡ እርሳቸው ግን ይህን መሳታቸው ከግል ድክመት የመነጨ ሳይኾን ወደ እውነተኛ የሞያ ጥሪያቸው ከማዘንበል የተነሳ ነው፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት ያደረጓቸውን ንግግሮች ያዳመጠ ሰው ሊስተው የማይችለው ነገር ቢኖር፣ ፕሬዝዳንቱ ኹልጊዜም ሪፖርት አቅራቢ ኾነው መገኘታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እንዴት ካለፉት ዓመታት ለዘንድሮ ዩኒቨርስቲው የተማሪውን ቅበላ እንዳሳደገ፤ ምን ያህል ዐዲስ ሕንፃዎች እንደ ተሠሩ፤ ስንት የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንደገቡ፤ ስንት ዐዲስ የትምህርት ክፍሎች እንደተከፈቱ… ወዘተርፈ በቁጥር ማቅረብ ነው፡፡ እንደዚህ ዐይነት ዘገባዎች፣ በዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ወይም በየትምህርት ክፍሉ ሊቀርብ ሲችል የፕሬዝዳንቱ ተቀዳሚ ሥራ ኾኖ መገኘቱ በእጅጉ አስገራሚ ነገር ነው፡፡
በመጨረሻም ፕሬዝዳንት ኾነው ባገለገሉባቸው ጥቂት ዓመታት፣ የተለያዩ ጥያቄዎች ወደ እርሳቸው በሚቀርብበት ጊዜ ቶሎ ብሎ የሚቀናቸው፣ ጉዳዩ በኮሚቴ እንዲታይ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በኮሚቴ ማየቱ ተገቢ ቢኾንም የቀረበውን ጥያቄ ኹሉ ወደ ኮሚቴ ማስተላለፍ በራስ ያለመተማመንና ሓላፊነትን ለመሸሽ የሚደረግ አዝማሚያ መስሎ ይታያል፡፡ ለማሳያ ያኽል፣ በቅርቡ የሪፖርተር ጋዜጠኛ፣ “የክብር ዶክትሬት ለመጠሪያነት ይውላል ወይ?” በሚል ለጠየቃቸው ሲመልሱ፤ “በእኔ እምነት ይቻላል፤ ነገር ግን መጠራት ይቻላል ወይስ አይቻልም ለሚለው ጉዳይ የመጨረሻ ዕልባት ለመስጠት እንዲረዳ ኮሚቴ አቋቁመን እንዲወሰን እንደርጋለን፡፡” በማለት መልሰዋል፡፡
ለ. ጥቅም
የፕሬዝዳንት አድማሱ አካሔድ በጥቅሉ ሲታይ የዕውቀት ማነስ (Epistemic) ጉዳይ ብቻ ሳይኾን ጥቅምንም ከመፈለግ እና ከማስጠበቅ የሚመነጭ ክሥተት ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ይኼን በምንልበት ጊዜ፣ ጥያቄው የእውነት ወይም የሐሰት ሳይኾን ጥቅም የሚያስገኘው የትኛውን መንገድ ብከተል ነው ከሚል ስሌት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ የሰባት ዓመት ልጅ መደበኛ ሒሳብ ሲማር አስተማሪው፣ ኹለት ጊዜ ኹለት ብሎ ሲጠይቀው እንደ አምስት፣ ሰባት ወይም ስምንት ብሎ የተሳሳተ መልስ በመለሰ ቁጥር የሎሊ ፖፕ ጉርሻ መምህሩ የሚሰጠው ከኾነ ልጁ ልቡናውም ቢያውቀው፣ አራት የሚል ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት አይፈለግም፡፡
ፕሬዝዳንቱም ከፖለቲካ ሥርዓቱ ትእዛዝ እየተቀበሉ የሚያስፈጽሙት፣ ለዩኒቨርስቲው ይበጃል ወይም አይበጅም ከሚል በመነሣት ሳይኾን ያሉኝን ብፈጽም የእኔ ጥቅም ይከበራል ወይስ አይከበርም ከሚል ስሌት ስለሚኾን ለዩኒቨርስቲው ፋይዳ ባይኖረውም ምንጊዜም ጥቅም የሚያገኙበትን አካሔድ ይመርጣሉ፡፡
ከዚህ ቀደም አንድ ጸሐፊ፣ ከእርሳቸው በፊት ከነበሩት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንቶች፣ እርሳቸው በቁመት አንደኛ ናቸው ብሎ ነበር፡፡ እኔም ደግሞ ተጨማሪ አንደኝነታቸው በቁመት ብቻ ሳይኾን ምናልባት እስከ ዛሬ ከተሾሙት ፕሬዝዳንቶች ቀዳሚው ባለሀብት መኾናቸውን ነው፡፡
ሐ. እብሪት
እብሪት ብቻውን የሚከሠት ነገር አይደለም፡፡ ዕውቀት በሌለበት ቦታ፣ ንዋይ በበዛበት መንደር እብሪት መፈልፈሏና ማበቧ አይቀርም፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ያልኾነውን ነገር መኾን ሲከጅል በእብሪት አዙሪት ውስጥ ይወድቃል፡፡ ጥንታውያኑ የግሪክ ጸሐፍት እብሪትን ሲገልጹት፣ ከአማልክቱ ጋር ለመወዳደር መሻት ነው ይሉታል፡፡ ይህ ውድድር በመጨረሻም ለእብሪተኛው ውድቀት ይኾነዋል፡፡
ያለ ማወቅ እንዴት ፕሬዝዳንት አድማሱን ወደ እብሪት እንደወሰዳቸው ማሳያ ይኾነን ዘንድ “የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ከአጼ ዮሐንስ እስከ ኢሕአዴግ” የሚል መጽሐፍ ታትሞ ለገበያ እንደዋለ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ተመረቀ፡፡ በምረቃው ዕለትም የክብር እንግዳው ፕሬዝዳንቱ ነበሩ፡፡ ስለ መጽሐፉ ምርቃት ዜና ሲተላለፍም፣ መጽሐፉን በእጃቸው ይዘው በአድናቆት ሲያገላብጡም በቴሌቪዥን ታይታዋል፡፡ ይኹን እንጂ ምርቃቱ በግቢው እንዲከናወን የተፈቀደው እና እሳቸውም የተሳተፉት፣ ከደራሲዎቹ አንድኛው በዩኒቨርስቲው መምህር ቢሆንም በዋናነት እና የብአዴን አባል ስለኾነ የእኛው ነው በማለት ያደረጉት ትብብር እንደኾነ ግልጽ ነው፡፡
ኾኖም ግን መጽሐፉ ተመርቆ ለሽያጭ ከዋለ በኋላ የህወሃት የፖለቲካ ኃይሎች በይዘቱ ስለተቆጡ ወዲያዉኑ እንዲታገድ አስደረጉ፡፡ ይሄንንም ሲሰሙ ፕሬዝዳንቱ ተደናገጡ፡፡ ህወሃት የማይደግፈውን የፖለቲካ መስመር የያዘ መጽሐፍ ግቢው ውስጥ እንዲመረቅ ማስደረጋቸው እና እራሳቸውም በክብር እንግዳነት መገኘታቸው በእጅጉ አሳፈራቸው፡፡ወትሮውንም የፕሬዝዳንቱ ድጋፍ የመነጨው ባላቸው ፖለቲካዊ ቀረቤታ እና አመኔታ እንጂ መጽሐፉን ከማንበብ ተነሥተው አልነበረም፡፡ ኋላ መጽሐፉ በፖለቲካ የሚያስጠይቃቸው መስሎ ስለታያቸው ደራሲውን ከዩኒቨርሲቲው እንዲባረሩ ከጀርባ ኾነው ጥረት አድርገው ነበር፡፡
ከዚህ ማሳያ የምንረዳው ነገር ቢኖር ፕሬዝዳንቱ በፖለቲካ የማይስማማቸውን ሰው በቂ እና ተገቢ ያልኾነ ምክንያት እየፈለጉ በማንአለብኝነት እና በእብሪት የያዙትን ሥልጣን በመጠቀም በተደጋጋሚ ሰዎችን ሲጎዱ ታይተዋል፡፡
የፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ እብሪቶች፣ በተለያዩ ጊዜያት የታዩ ቢኾንም፤ በእኔም ላይ የደረሰውን እብሪታዊ ድርጊት እንደ ተጨማሪ ማሳያ አድርጌ ላቅርብ፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በዩኒቨርስቲው ላስተማርኩበት የጠየቅኹት የሰባቲካል ፈቃድ ስለተነፈገኝ ሥርዓቱንና ዕርከኑን ጠብቄ ቅሬታዬን ለፕሬዝዳንቱ አቀረብኩ፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ላስገባኹት በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች ያሉት አቤቱታ በማግስቱ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.፣ “በጥልቅ መርምረን እንዳረጋገጥነው፣ የኮሌጁ ውሳኔ የሚለወጥበት ምክንያት የለም” የሚል መልስ በቆራጣ ደብዳቤ ላኩልኝ፡፡
የእብሪቱ ጫና ባይኖር እና እንደ ደንቡ ቢኾን ኖሮ፣ ከትምህርት ክፍሉ ጀምሮ እስከ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ድረስ ያሉትን ሓላፊዎች እንዲኹም የሕግ አማካሪዎቸቻቸውን ሳያማክሩ እና በማስረጃነት ያቀረብኋቸውን ሰነዶች ሳይመረምሩ በሰዓታት ውስጥ መልስ ባልሰጡ ነበር፡፡
ደብዳቤው እንደ ደረሰኝ፣ በነገሩ ተገርሜ ለፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ፣ ብረቱ ከሰሜን ሹመቱ ከደቡብ ኾነባቸው እንጂ የኹለቱ ግጥምጥሞሽ በእጃቸው ቢኖር ኖሮ እኔ ላይ ሰኔ እና ሰኞ ይገጥም ነበር፡፡

Source: Dr Dagnachew Assefa (ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ)

No comments: