Saturday, October 10, 2015

ጥፋተኞች ነን የዞን9 ጦማርያን የጥፋተኝነት ቃል

የተጻፉ ሕጎች ለዶክመንተሪ ግብዓት ብቻ የሚውሉበት፣ በተግባር የማይታዩበት፣ የተለየ ኃሳብ ያላቸው ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ለማጥቃት በተዘጋጀ ሕግ በተለጠጠ ትርጉም እና ከሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ-መንግስት ጋር ሳይጋጭ የሚያስፈጽም ፍርድ ቤት በሌለበት፤ ደጋፊ ጋዜጠኞች ሌሎችን ካላሰራችሁ ብለው በሚጮሁበት - ሕገ-አራዊት በነገሰበት ሕገ-መንገስት ይከበር በማለታችን ጥፋተኞች ነን፡፡
በተለያየ ጊዜያት የሚታሰሩ የሚገደሉ እና የሚሰደዱ ግለሰቦችን እያየን ዝም ማለት ትተን አጋርነታችንን በማሳየታችን ጥፋተኞች ነን፡፡
የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብት ለሚጥሱት ጥብቅና ቆሞ ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቋማትን ስም ለማጥፋት የሚራውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን እንደመስማት በግልም ሆነ በቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለሚመለከተው ሁሉ በማድረሳችን ጥፋተኞች ነን፡፡
ጋዜጠኞች በነጻነት ይሰሩ ዘንድ እኛም እንደጦማሪ እና ዜጋ ጋዜጠኞች ሰነዶቻችንን በሚስጥር እንዴት መያዝ እንደሚገባን ለማወቅ መታተራችን ያወቅነውንም ለሌሎች ለማካፈል በመሞከራችን ጥፋተኞች ነን፡፡
በኢቲቪየሚተላለፈውን የመንግስት ዘገባ ችላ ብለን መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር ተፋጠን መንግስትን በመተቸታችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
ትውልድ በፕሮፓጋንዳ እንዲናውዝ ሁሉን ይረሳ ዘንድ የሚደረገውን የተቀናጀ የመንግስት ጥረት ችላ ብለን ዜጎች እንዲነቁ በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል እንዲሉ በማሰብ መሰባሰባችን በማያገባን መግባታችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
መንግስት ዳቦ ሲል ዳቦውም ያለፍትሃዊነት ለተመረጡት ዜጎች ቅድሚያ ሲታደል እኛ ዳቦም ነጻነትም ለሁሉም እኩል በማለታችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
-በአገራችን ሕግ ለገዢዎቻችን ዱላ ሆኖ እያለ ሕግ ምርኩዝ ነው ዱላ ብለን ያላአዋቂ ጥያቄ በመጠየቃችንና በማስጠየቃችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
የገዥው ፓርቲ የፓርቲ ተወዳጅነት ማግኛ የሆነውን የአባይ ግድብ፣ የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ አታድርጉት ሁላችንም አሻራችንን እናሳርፍ ዘንድ አባይን መልሱልን ገዢውን ፓርቲ ያልወደደም ጭምር እንደ ዜጋ የራሱ ያድርገው ብለን የመንግስትን ምርጉዝ የሆነውን ፕሮፓጋንዳ ልንቀማው በመሞከራችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች የሆኑት በግፍ መታሰራቸውን ተቃውመን አጋርት በማሳየታችን፣ ‹‹እስላማዊ መንግስት ሊመሰርቱ ሲሉ›› የሚለውን የጸሀዩ መንግስታችንን ፓሮፓጋንዳ ተቃውመን በተደጋጋሚ በመናገርና በመጻፋችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
ዴሞክራሲ በሰፈነባት እነ ሚሚ ስብሃቱን የመሰሉ ጋዜጠኞች የራሳቸውን ራዲዮ ጣቢያ አቋቁመው በነጻነት በሚሰሩበት አገር ሃሳብን የመግለጽ መብታችን ይመለስ ሳንሱር ይቁም ብለን በመጠየቃችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
ልክ ነው ህዳሴ እና ጂቲፒን የመሳሰሉ የመንግስት ፕሮፓጋንዳዊ ቅዥቶች እያሉልን የኢትዮጵያን ሕልም እናልም ብለን በጋራ በማለማችን አዎ ጥፋተኞች ነን፡፡
Source: Zone9

No comments: