የወያኔ ስርዓት የኢትዮጵያን አስተዳደር ሲያዋቅር በህዝብ ታሪካዊ አብሮነትና ተዛምዶ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የብሔር ብሔረሰብ ልዩነቶችን በማጉላትና ልዩነቱም የርስበርስ ጥርጣሬና ግጭት ምንጭ እንዲሆን በማድረግ ነው። ልዩነቱ የእርስ በርስ ግጭትና የረጅም ጊዜ ቁርሾ እንዲፈጥር ተደርጎ ከመዋቀሩ በተጨማሪ፣ ግጭቱ በማንኛውም ጊዜ እንዲነሳ ፖለቲካዊ ግፊት ይደረግበታል ። አንዱ ብሔረሰብ በሌላው ብሔረሰብ ክልል ውስጥ ሲሆን ባዕድነት እንዲሰማውና እንዲሰጋ፣ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ለማድረግ ላለፉት 24 አመታት ሲገፋ ቆይቷል፤ እየተገፋም ነው። በዘመነ ወያኔ በየቦታው በብሔር ወይም ብሔርሰብ ስም የተነሱ ግጭቶች በሙሉ የተቀሰቀሱት በራሱ በአገዛዙ ባለስልጣኖች እንጂ በህዝቡ አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም። በተለያዩ የደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች የአማራ ተወላጆችን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ለማባረር የተወሰዱት እርምጃዎች በሙሉ ባለስልጣኖቹ ከፊትና ከጀርባ ሆነው የቀሰቀሱዋቸው ፣ ያቀነባበሩዋቸውና የመሩዋቸው ለመሆናቸው ተጎጂዎች በግልጽ ሲናገሩ ሰምተናል።
በቅርቡ በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በአስቃቂ ሁኔታ ተገድለውና ተጥለው የተገኙት የአማራ ተወላጆች የሥርዓቱን ባህሪይ ከሚያሳዩ መግለጫዎች አንዱ ነው ። እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ወያኔ ባስለጠናቸውና ባዘዛቸው ካድሬዎችና ባለስልጣኖች የተፈጸመ እንጂ በሕዝብ ተነሳሽነት የተፈጸመ አለመሆኑ ግልጽ ነው። በቅርብ የተፈጸመው ድርጊት ቀደም ሲል በመንግስት ደረጃ የተቀነባበረው አማሮችን የማፈናቀል ዘመቻ ተከታይ ስራ ነው። በወገኖቻችን ላይ በሚዘገንን መንገድ የተፈጸመው ይህ አሰቃቂ ግፍ ዘልቆ ይሰማናል። ቁጭታችንና ሀዘናችን ግን ወያኔ ወደሚፈልገው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት መንስኤ እንዳይሆን ከፍተኛ ትዕግስትና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።
ሰሞኑን እንደገና በታሪክ ሊዘገብ ከሚችል ልዩነት ውጭ ባኗኗር፣ በባህልና ቋንቋ የማይለያዩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች ቅማንትና አማራ በሚል ለማጋጨት ጥረት በማደረግ ላይ ይገኛል። ይህ ሰይጣናዊ አካሔድ በወያኔ የፖለቲካ ተንኮል እየተመራ እንዳለ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። አርበኞች ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ካላንዳች መድሎና ልዩነት ሀገሪቱ ላይ መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ሁሉም በየበኩላቸው የሚያደርጉትን ጥረትና ትግል ይደግፋል። በህዝባችን መካከል ያሉት ግንኙነቶች አንዱ አንዱን የሚያግዝና የሚደግፍ እንዲሆን እንጂ የእርስ በርስ የመጋጨትም ሆነ የመናቆር ምክንያት እንዳይሆን ተግቶ ይሠራል ።
ኢትዮጵያውያን ብሄርና ዘር ሳንለያይ ይህንን የወያኔ ተንኮል ችግሩ ወደባሰ ደረጃ ሳይሄድ መቋቋምና ማክሸፍ እንደሚኖርብን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። ይህ ታሪክዊ መተሳሰራችንንና ታላቅ ሕዝብነታችንን የማይመጥን አሳፋሪ የወያኔ ፖለቲካ እንደሀገር እንዳያጠፋን ሁላችንም በንቃትና በቁርጠኝነት መቋቋም ይኖርብናል::
አርበኞች ግንቦት ፯ ልዩነት ጌጥ እንጂ የጠብና የግጭት ምክንያት የማይሆንባት ሀገር ፥ የየብሔረሰቡ መብት ሁሉ የይስሙላ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠባት ሀገር ፥ ከነልዩነታችን በጋራ ራዕይ የምንተሳሰርባትና የምንገነባት ሀገር እንድትኖረን የሚያደርገውን ትግል ይቀጥላል። የቻልክ በአካል ተቀላቀለን። ያልቻልክ በያለህበት የወያኔ ዘራፊዎች ያሰቡትን የተንኮል ጉንጉን በመበጣጠስ ተሳተፍ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
No comments:
Post a Comment