Friday, November 20, 2015

ይድረስ ለሀፍረተ ቢሱ ብአዴን እና ለ35ኛ በዓል አክባሪዎች

(ግልፅ ደብዳቤ ከቂሊንጦ እስር ቤት)
ፅሁፍ ዝግጅት - ዘመነ ምህረት (የቀድሞው መኢአድ ም/ፕሬዝደንት)
(አቶ አሸናፊ አካሉ አበራ ሀሳብን በማንሳት አግዞኛል)
ይህንን ፅሁፍ በአማራ ስም አማራውን ለሚያቆስለውና ለህወሓት ስሪት ለሆነው ብአዴን አመራሮችና አባላት ልፅፍ ስሰናዳ ለፅሁፉ መነሻ የሆኑት ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነሱም፡-
1ኛ. አቶ አለምነው መኮነን (የአብአዴን የህዝብ ግንኙነት) በ01/02/08 ዓ.ም በአማራ ክልል ቴሊቪዥን ስለ 35ኛው የብአዴን በዓል አከባበር የሰጠው መግለጫ፤
2ኛ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ጭቆና፣ በደሉን የሚሰማና አለሁ ባይ ተቆርቋ ተቋምም ሆነ መሪ አለመኖሩን ለማሳወቅ ነው፡፡
የጥንታዊና የመካከለኛውን ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ባለበት ትተን ከዘመናዊው ታሪክ ብንነሳ አብዛኛው ዘመን ገዥና የገዥ መደብ ሆኖ ኖሯል ተብሎ የሚወቀሰው የአማራ ህዝብ ነው፡፡ እገሌ የሚባለው መሪ የእገሌ ብሄር ተወላጅ እንጅ የገሌ አይደለም የሚባለው ዘር ቆጠራ ውስጥ ለመግባት አይደለም አነሳሴ፡፡ በዚህ ፅሁፍ በገዥና የገዥ መደብ ስም በአማራው ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው ሰቆቃ እና አማራውን ወክዬ ስታገል 35 አመት አስቆጥሬያለሁ የሚለው ብአዴን ህዝቡን እንደማይወክል ለመሞገት ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ትናንት ‹‹አማራ›› በተባሉ ገዥዎች፣ ዛሬ ደግሞ ‹‹አማራ ጨቆነን›› ባይ ባለጊዜዎች የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኗል፡፡ እየሆነም ይገኛል፡፡ አጤ ምኒልክ በኦሮሞና ደቡብ ፈፀሙት በተባለው ግፍ በአማራ ህዝብ ላይ ጣት ሲጠቆም፣ አጤ ዮሃንስ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላ ምላሳቸውን ስለቆረጧቸው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ትግራይን በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ አይሆንም? ዛሬ እነ ጃዋር ሞሃመድ፣ መኩሪያ ቡልቻ፣ መሃመድ ሀሰን፣ የተባሉት ‹‹ምሁር›› ነን ባዮች በሚፈሰው የዘውግ ፖለቲካ ተንሳፍፈው በሚነፉት ድስኩር በስመ አማራ ስንቱ ከቤት ንብረቱ ተፈናቀለ፡፡ ተሰደደ፡፡ ተገደለ፡፡ ለሆነው ሁሉ ጥናት ተደርጎ የሚጠየቅ አካል ቢኖር የብአዴን አመራሮች ወክለንሃል በምትሉት ህዝብ ላይ ስለደረሰውና ስላደረሳችሁት ሁሉ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች በሆናችሁ ነበር፡፡ ከእናንተ ህሊና አልባ ህይወት የእኛ በአካል መታሰር በስንት ጣዕሙ! በእርግጥ ታሪክ ፍርዱን መስጠቱ አይቀሬ ነው፡፡
ጅብ ከሄደ....
አቶ አለምነው መኮንን በቴሊቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የ35ኛ ዓመት በዓልን ማክበር ያስፈለገበትን ዓላማ ሲዘረዝሩ ለእሳቸው እኔ አፈርኩ፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
• የኢህዴንን ወደ ብአዴን መቀየር አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ
• የአማራ ህዝብ ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ያደረገውን አስተዋፅኦ ለወጣቱ ለማሳወቅ፣
• የአማራ ህዝብ ጨቋኝ አለመሆኑን ለማስገንዘብ
ይህን ባየሁ ጊዜ ታዲያ ‹‹እኒህ ሰውዬ ከጤናቸው ይሆኑ?›› የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ ‹‹የትምክት ለሃጩን ሳያራግፍ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ....›› ብለው በአማራው ላይ የተፉት ምራቅ ሳይደርቅ ምን የሚሉት መገልበጥ ነው ለአማራው ተቆርቋሪ መምሰል? የአማራው ህዝብ ጨቋኝ አለመሆኑን ለማስገንዘብ ስትሉስ ጨቋኝ እየተባለ ይህን ያህል ጊዜ ፍዳውን ሲያይ፣ ሲረገጥና ሲሰቃይ የት ነበራችሁ? ጨቋኝ ላለመሆኑ ጥናት እያጠናችሁ? እነ በረከት ‹‹የአማራን ትምክት እናስታግሳለን›› ሲሉ የት ነበራችሁ? የአማራ ህዝብ ለአንድነት ያደረገው ተጋድሎስ የሚጀምረው ከ35ኛ በዓላችሁ በኋላ ይሆን?
በደል ለበዳዩ ምኑ ነው?
የብአዴን አባላት ሆይ! ወክለንሃል እያላችሁ የምትገድሉትና የምታስገድሉት፣ የምትጨቁኑትና የምታስጠቁት፣ የአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው ሁሉ ባይሰማችሁ አይገርምም፡፡ እናንተ የበዳዩ እንጅ የተበዳዩ፣ የጭቁኑ፣ የመከረኛው ህዝብ አካል አይደላችሁምና፡፡ በምቾትና በድሎት ችላ ብትሉትም እራሳችሁ የምታውቁትን የህዝብ በደል ላስታውሳችሁ፡፡
• ‹‹ኤርትራ/ትግራይ በገዥው የአማራ ህዝብ ቅኝ ግዛት ተይዟል›› የሚለውን የሻዕቢያንና የወያኔን ማንፌስቶዎች ተቀብላችሁ፣ አብራችሁ ለመስራት አልተስማማችሁም? ይህስ የዛሬው ፕሮፖጋንዳችሁ ጋር ሙሉ በሙሉ አይጣረስም?
• ኢህዴን ወደ ብአዴን ተቀይሮ የአማራ ህዝብ ወኪል መስሎ ሲቀርብ የትኛው የአማራ ተወላጅ ይሆን መሪ የሆነው? በረከት ስምኦን? ተፈራ ዋልዋ?..... ጀኔራል ኃይሌ ጥላሁን ጥርስ ተነክሶበት እንዲጉላላ የተደረገው በብአዴን ስብሰባ ላይ ‹‹ብአዴን ውስጥ የአማራ ተወላጅ የለም›› ብሎ በመናገሩ አልነበረም? በ1987 ዓ.ም ማርቆስ ላይ በተደረገው ስብሰባ ስንቱን የአማራ ተወላጅ ለህዝብ ይቆማል ተብሎ ከብአዴን አላባረራችሁም? ስለ ሙሉዓለም አበበ ግድያስ ምን እየተባለ ይሆን?
• ያለ ህዝብ ፈቃድ የወልቃይትና ሁመራ መሬት ከጎንደር፣ አላማጣ፣ ራያ ቆሞ፣ ኮረም፣ ከወሎ በመንጠቅ ለህወሓት ለመስጠት ሲወሰን፣ አብዛኛዎቻችሁ እሺ ብላችሁ አልተቀበላችሁም? የተላከላችሁን ውሳኔስ አላፀደቃችሁም?
• ጓንግና ጓንግ ባሻገርን፣ ኮር ሁመራን፣ ወደቁራን፣ ገላሎባን፣ ስፋዋን፣ ባህረ ሰላምን፣ መተማን፣ ቋራ ከቁጥር 1-8 እና ነብስ ገበያን ለሱዳን የሰጣችሁት ለአማራ ህዝብ ስለምትታገሉ ነው? በእናንተ ‹‹ጥረት›› ነገ ታሪክ መፅሃፍ ላይ የአጤ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታ ሱዳን ልታደርጉት ነው፡፡
• የአማራ ክልል ብቻ ተለይቶ በ1987 ዓ.ም አርሶ አደሩ በሙሉ በነፍስ ወከፍ የያዘውን መሳሪያ እንዲቀማ የተደረገው በሌሎች ክልሎች የተያዘው መሳሪያ ስለማይተኮስ ወይንስ አማራ በኢትዮጵያ ስጋት ስለሆነ ራቁቱን መቅረት አለበት ብላችሁ ስለምታምኑ?
• በ1989 ዓ.ም በአማራ ክልል በተካሄደው የመሬት ‹‹ሽግሽግ›› ቢሮክራትና ቅሬተ ፊውዳል በሚል ፍረጃ ብዙሃን መሬቱ ሲነጠቅ፣ በድህነት እንዲማቅቅም ሲደረግ፣ ያኔ ነጭ ለባሽ የነበረው የጎጃም ህዝብ ያቀረበው ቅሬታ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቀባይነት ቢያጣ ‹‹ጎጃም አዘነ›› የሚል ቅፅል የወጣለትን ልብስ መልበስ የጀመረው በእናንተው ዘመን አይደለም? ይህ ህዝብ መሬቱ ተነጥቆ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት ደርግ ይገዛ የነበረው አማራን ብቻ ስነበር ይሆን?
• አይናችሁ እያየ ንብረቶች ወደ ትግራይ አልተጋዙም? ሌላው ይቅር፤ ጣሊያን የሰጠውና ጎንደር ላይ ሀይል እንዳይቋረጥ ያግዝ የነበረው ግዙፍ ጀኔሬተር ተነቅሎ ሲወሰድ የት ነበራችሁ? ደርግ ለቴክኒሻኖች ማስተማሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ ዘመናዊ ማሽኖች፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙ የነበሩ ሜሪኩሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ወደ ትግራይ የተጓዙት እናንተ ‹‹የአማራ ወኪል ነን›› ባላችሁበት ወቅት አይደለም? አፈር ሳይቀር እንደተጫነ የማታውቁ ሆናችሁ ነው?
• የአማራ ተወላጅ ሴቶች መሃን የሚያደርግ ክትባት ሲሰጣቸው፣ ዘር ማጥፋት አንዱ አካል መሆኑን ከእናንተ የተደበቀ ነገር ኖሮ ነው?
• የምታመልኩት ህወሓት መራሽ መንግስት ነፍጥ አንጋቢዎቹ ሳንጃ፣ ጎርቢጥ ላይ የ14 ሰዎችን ደም ካፈሰሰ በኋላ ከግድያው ያመለጡ ሰዎች በምሬት የአርበኞች ግንባርን መመስረታቸው ለእናንተ ይጠፋችኋል? ምን አልባት በድሎት ከዘነጋችሁት በወቅቱ የአርማጭሆ አስተዳደርና በ2004 ዓ.ም የጎንደር ከተማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊን ጠይቁት፡፡ አስከሬናቸው ሳይቀበር ውሻ እንዲበላው ነበር የተደረገው፡፡
• በወቅቱ በምስራቅ አፍሪካ ከነበሩት ሁለት የቀዶ ጥገና ሀኪሞች አንዱ በኢህአዴግ እስር ቤት ማቅቀው የሞቱት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ጠንካራ የነበረው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት፣ አቶ አሰፋ ማሩን የመሰሉትን ምሁራን ማን ገደላቸው? ጭቆናን የተቃወሙ የአማራ ተወላጅ ምሁራን ሲሰደዱ፣ ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ እናንተ የት ነበራችሁ?
• በ1997 መለስ ዜናዊ ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ የአማራ ክልል የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ድሆችና መንገድ ላይ የወደቁት በሽተኞች ከባህርዳር ከተማ ተለቅመው፣ በመኪና ተጭነው የት እንደተጣሉ አታውቁም?
• ‹‹አማራ ጨፍጫፊ›› ነው በማለት ለዚሁ ቂም መፈልፈያ ይሆን ዘንድ የሲዳማ ባህል አዳራሽ፣ የአኖሌ ሀውልት ማቆም፣ በስርዓተ ትምህርት ደረጃም መቅረፅ፣ ማሰልጠኛ ማንዋል አዘጋጅቶ ጥላቻን በስልጠና መልክ መስጠት ምን የሚሉት ቢሂል ነው? በተለይ ተወካይ ነን ለምትሉት! እንደለመዳችሁት ‹‹አናውቅም!›› እንዳትሉ ደግሞ ስልጠናውን የሚሰጡት እነ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ በረከት ስምኦንና ፣......ሌሎችም አመራሮቻችሁ ናቸው፡፡
• በአርባጉጉ፣ በቴፒ፣ በጅማ፣ በበደኖ፣ በጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉል እና በጋምቤላ አማራ በመሆናቸው ብቻ የተፈናቀሉት፣የተገደሉት፣ ‹‹ሀገራችሁን ግቡ›› የተባሉት፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ሀገር አገኛችሁላቸው?
• የህዝቡን አንድነት ለማዳከም አብሮ የኖረውን የቅማንት፣ የአገው... ከፋፍላችሁታል፡፡ የቅማንት ማህበረሰብም በጣና አካባቢ የራሱ ግዛት እንዲኖረው እየሰራችሁ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ሴራችሁ የአማራ ህዝብ ወኪል ስለሆናችሁ ነው?
• የተለያዩ ፖሊሲዎች ሲሞከሩ የአማራ ህዝብ እንደ አይጥ መሞከሪያ ይሆናል፡፡ ‹‹ምርጥ ዘር››ም ሆነ የትምህርት ፖሊሲ (ስምንተኛ ክፍል ድረስ በአማርኛ) የሞከራችሁት የት ነበር? አብዛኛዎቹን ፖሊሲዎች በአማራ ላይ ሞክራችሁ አይደለም ድክመታቸውን ተለካ የተባለው?
• የንግድ ተቋማት፣ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች፣ በማን እጅ እንደሆኑ እናንተ አጥታችሁት ይሆን? ይህንን ለማወቅ ጎንደርን ብቻ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ ካፍቴሪያዎች፣ ሱቆች፣ ሆቴሎች፣ ህንጻዎች.. የሚተዳደሩት በህወሓት ደጋፊዎችና አባላት አይደለም? በአርማጭሆ፣ ቋራና መተማ ለም መሬቶች በህወሓት ቁጥጥር ስል አይደሉም? በክልሉ የጉምሩክ ቢሮ ቀዳሚዎቹ የስልጣን ቦታዎች ለማን የተተው ናቸው? ለዋቢነት ከ2004 -2005 በጎንደር ከተማ ንግድ ፅ/ቤት በመለስና በምክትሉ አባዲ መካከል ‹‹ለምን ከ500 በላይ የትግራይ ተወላጆች የያዟቸው የንግድ ተቋማት ያለ ፈቃድ ይሰራሉ?›› በሚል የተነሳውን ግጭት መለስ ብላችሁ አስታውሱ፡፡
• ሱዳናውያን ድንበር እየጣሱ የሚያቀጥሉትና የሚዘርፉትን የህዝብ ንብረት ቸል ማለታችሁ ሳይበቃ፣ በ2007 ዓ.ም ከእንፍራንዝ ወደ ሮሮታ አሳፍርሻለሁ በሚል ኩላሊቷን አውጥቶ፣ ገድሎ በመጣል፣ ሊሰወር ሲል ሀሙሲት ላይ በህዝብ ርብርብ የተያዘውን ሱዳናዊ በመቶ ሺህ ብር ክፍያ ያውም ጥቃት እንዳይደርስበት በመከላከያ ታጅቦ እንዲወጣ ያደረጋችሁት ለአማራ ህዝብ ወኪል ስለሆናችሁ ነው? ይህን ድርጊት የተቃወሙትን ወጣቶች ያሰራችሁት ለማን ስለቆማችሁ ይሆን?
‹‹አሸባሪው›› አማራ
ዛሬ አማራ ማለት አሸባሪ ተብሎ ተፈርጇል፡፡ ከደህንነት ቢሮዎች እስከ ቂሊንጦ እስር ቤት፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ፣..... ድረስ ያለውን አማራ በመሆኑ ብቻ እየተሰቃየ ያለውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እኔ በምገኝበት ቂሊንጦ፣ ዞን አንድ ዘርዝሬ የማልዘልቀው (ወጣቱን ልተወውና) ለአቅመ አዳም ያልደረሱት ገብናናው ጨቅሌ፣ አብዩ ተስፋ፣ ጀጃው ኃይሌ፣ ዶክተሩ ባዬ እድሜያቸው ከ14 አመት የማይበልጡ ህፃናት ናቸው፡፡
የ‹‹የዘርህ ያንዘረዝርህ››ን ብሂል የሚከተሉት የወቅቱ ገዥዎች መሰሪያዎቻቸው ደህንነት ተብዬዎቹ ጎንደር ብልኮ አካባቢ ከሚገኘው የደህንነት ፅ/ቤት፣ ባህርዳር ኢሜግሬሽን (ደህንነት) ፅ/ቤት፣ እስከ አዲስ አበባው ማዕከላዊ የሚያደርሱት ግፍና በደል ላየው ይቅርና ለሰማው የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ አማራ መሆን ወንጀል፣ ሽብር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ‹‹የምኒልክ ዘር፣ ጥንብ አማራ፣ ወራዳ አማራ....›› እያሉ ጉድጓድ ላይ ጥለው ሽንት መሽናትና ምራቅ መትፋት፣ ራቁትን መግረፍ፣ ‹‹የትምክተኛው አማራ ዘር መጥፋት አለበት›› እያሉ ብልትን መቀጥቀጥ፣ ‹‹አማራን ሱሪውን አስወልቀነዋል፣ ሱሪህን አውልቅ›› እያሉ ማንገላታት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ተቋማት ውስጥ በአማራ ላይ የሚደርሱ የዕለት ተዕለት ግፎች ፀሃይ ወጥቶ የመግባትን ያህል ተለምደዋል፡፡ ‹‹መለስ ጀግና፣ ታማኝ በየነ እና አበበ ገላው ውሻ ናቸው በል›› እንዲሁም፣ ‹‹ትግርኛ ተናገር!›› በሚል የሚደርሰው ድብደባ፣ የሰዎቹን የውስጥ ጭንቅላት አሳይቶናል፡፡
ይህ ሁሉ ጉድ የሚደርሰው የመተማ ተወላጅ በሆነው ደርሶ አያል (ባህርዳር ላይ)፣ እና አሸናፊ (የጣቁሳ ተወላጅ) በሆኑት የብአዴን /የህወሓት ተለጣፊዎች እንዲሁም በትግርኛ ተናጋሪ ደህንነቶች ነው፡፡ ባህርዳር ላይ በብአዴንና በህወሓት ደህንነቶች አማራ በግፍ ሲረገጥ እዛው ቁጭ ብሎ የአማራ ተወካይ ነኝ ማለት በጣም ያሳዝናል፡፡ ስላቅም ነው፡፡
ብአዴን፡- ሰው በላው ድርጅት
ይህንን ፅሁፍ ሳዘጋጅ ሞኝነት ቢጤ እንደተሰማኝ አልክድም፡፡ ለራሱ አባል ያልሆነው ብአዴን እንዴት የህዝብን ጥቅም ሊያስከብር ይችላልና የሚል መጠይቅ ውስጥ በመግባቴ፡፡ እስኪ ሰው በላው ድርጅት የበላቸውን አባላት ላስታውሳችሁ፡-
• መላኩ ፈንታ፡- የቀድሞ ጉምሩክ ዳይሬክተር የህወሓት የበላይነት ላይ ጥያቄ በማንሳቱ ዛሬ መገኛው ቃሊቲ እስር ቤት ሆኗል
• ብ. ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ብ. ጀኔራል አለማየሁ፣ ኮሌኔል አሳምነው ፅጌ፣ በ2001 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ልትፈፅሙ አሲራችኋል በሚል እስር ቤት ይገኛሉ
• ሙሉ ዓለም አበበ፡- በ1987ቱ የማርቆስ የብአዴን ስብሰባን ተከትሎ አይደለም የተገደለው?
• ብርሃኑ፡- የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረውና በአማራው ላይ የሚደርሰውን በደል ዘግይቶ በመንቃቱ በፖሊስ አባላት ‹‹የት ነበርክ›› የሚል የቅፅል ስም የተሰጠው፣ የአልማ ፅ/ቤት የተቃጠለበትን ሁኔታን ሲያጣራ ግልፅ ባልሆነ መንገድ መገደሉን ዘነጋችሁት? በዚህ ጉዳይ እነ አቶ ህላዊ የሆነ ነገር ማለት ይገባቸዋል፡፡ ጠይቋቸው!
• ጀኔራል አበባው ታደሰ፡- አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ሳይታወቅ፣ በከተማ የቁም እስር ተገሎ እንደሚኖር አታውቁም ይሆን?
• ነባር የተባሉት ‹‹የብሄር ተዋፅኦ›› በሚል፣ ለምሳሌ ያህል በ2005-2006 ከሻንበል በላይ ያሉት የሰራዊት አባላት መመንጠራቸው ለእናንተ ድብቅ ሆኖ ነው?
• በቅርቡ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አጃቢ የነበረው ኢንስፔክተር አበበ የኋላ ሶስት ራሱን አሸባሪ ተብሎ ቂሊንጦ ተቀላቅሏል፡፡ የታሰረበት ምክንያት አቶ ገዱም ሆነ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ዘውዱ ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ የክልሉ መንግስት አጣርቶ ‹‹ችግር የለበትም›› ብሎ ሲፈታው በፌደራል ደህንነቶች ጫና ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ታስሯል፡፡ በወልቃይትና ጠገዴ፣ በትግራይና አማራ ክልል መካከል በታህሳስ 2007 ዓ.ም ተነስቶ በነበረው ግጭት ተሳትፏል በሚል በህወሓት ጥርስ ውስጥ መግባቱን ብዙዎቻችሁ ታውቃላችሁ፡፡
ብአዴን እንደ ጉፈላ ላም
ታዲያ ብአዴን ማን ነው? ማንንስ ወክሎ ነው? ብዬ ሳስብ የጉፈላ ላም ትዝ ትለኛለች፡፡ አንዲት ላም ወልዳ ጥጃዋ ከሞተባት ገበሬው የጥጃዋን ቆዳ ይገፍና ቆዳው ላይ ሳር ሰግስጎ ጥጃ አስመስሎ ይሰፋዋል፡፡ ሰው ሰራሽ ጥጃዋ ላይ አሞሌ ይቀመጥና እናቷ ጨውን እየላሰች፣ በሰው ሰራሽ ጥጅ እየተታለለች ወተቷ ይታለባል፡፡ ለእኔም ገበሬው ህወሓት፣ ሰው ሰራሽ ጥጃው ደግሞ ብአዴን ነው፡፡ በሰው ሰራሽ ጥጃ ወተቱ የሚታለበው ደግሞ የአማራ ህዝብ ነው፡፡ አሁን ላሚቱ በሰው ሰራሽ ጥጃ መታለሏን አቁማ አዲስ ጥጃ ልትወልድ፣ የታሰረችበትን ገመድ በጥሳ የራሷን ልጅ ልታጠባ የግድ ነው፡፡ ሰዓቱም ነው፡፡
በተለይ ወጣቱ ጥጃ ሆነህ እንደ እናት ያቀፈህን ህዝብ ወክለህ የምትቆምበት፣ የተጠመደብህን ቀንበር ሰብረህ የምትጥልበት ወቅት ነው፡፡ የህወሓት ስሪት የሆነው ብአዴንን ‹‹አትወክለኝም፡፡ ነቅቼብሃለሁ›› የምትልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ግፍ፣ በደልና ጭቆና ይበቃል፡፡ አሁን የአማራ ህዝብ ጉዳይ የዴሞክራሲ ሳይሆን የመኖር ያለመኖር ጉዳይም ጭምር ሆኗል፡፡
በ1997 ዓ.ም ኢህአዴግ ‹‹ኢንተርሃምዌይ›› የሚለውን ክፉ ቃል ሲጠቀም ከራርሞ፣ ሰሞኑን ደግሞ እነ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተጠቅሞበታል፡፡ አሁንም ‹‹እገሌ ሲጨቁንህ ነበር›› እያሉ ነው፡፡ እናም ብአዴንን ሆይ! በጉፈላ ላም ስመስልህ ከገዳዮች ጋር አብረህ በመሆን የገደልከው፣ ያስጨረስከው፣ ታሪክና ማንነቱን ያዋረድከውን ህዝብ ከ35 አመት በኋላ አዳኝ፣ ወኪሉ መስለህ መቅረብህ ባይዋጥልኝ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ መፅሃፍ አርዕዮስ ሁለት ምላስ ሆናችሁ ትናንት ሌላ፣ ዛሬ ሌላ ትዘባርቃላችሁ፡፡ መዘባረቃችሁ ከውስጥ አለመሆኑንም እሩቅ ሳንሄድ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ‹‹ለሃጩን እያዝረከረከ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ ትምክት የሚተፋ›› ብሎ የተሳደበውን አቶ አለምነው መኮንን በአመራር ደረጃ ያውም የብአዴን የህዝብ ግንኙነት አድርጎ ማስቀመጡ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡ ጉዳዩ ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› ነው፡፡
በዓሉ የህወሓት ወይንስ የብአዴን
35ኛ በዓላችሁን ልታከብሩ ሸር ጉድ እያላችሁ መሆኑን እስር ቤት ሆኘም በቴሊቪዥን እየተከታተልኩ ነው፡፡ በዓሉ ከብአዴን ምስረታ ጀምሮ ተቆጥሮ መሆኑ ደግሞ ግርምትን ይጭራል፡፡ ለመሆኑ የኢህዴን/ብአዴን አላማና ተልኳቸው ለየቅል አይደለም? ኢህዴን ተቀጥቅጦ ብአዴን የተባለው መአህድ መመስረቱን ተከትሎ አልነበረም? እንደ እኔ በዓሉን ማክበር ያስፈለገው፡-
• የስልጣን እድሜን ለማራዘም
• ጭቆናው ያንገፈገፈውን ህዝብ ግፊት ለማቀዝቀዝ
• የኢትዮጵያ አንድነትን ወደኋላ ለመጎተት
• ከህወሓት ጋር ቁመት በመለካካት፣ እኩል እንደሆኑ ለማስመሰል ነው
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ ‹‹ኢህዴን/ብአዴን የማንም ውራጅ አይደለም፡፡›› ቢሉም አሁንም ግን ብአዴን የህወሓት ውራጅ ነው፡፡ በመሆኑም ብአዴን የአማራነትን ጭምብል አጥልቆ የቆመ በመሆኑ በዓሉ የህወሓት በዓል ነው፡፡ የህወሓትና የብአዴን ልደት በ11 የሚከበር በመሆኑም በአንድ ላይ ቢያከብሩትም ባልከፋ፡፡
ማን ይናገር......
የአማራ ህዝብ ይህን ያህል ገፈት ሲቀምስ ቆምኩለት የሚለው ብአዴን ዛሬ በአዲስ ስልት ‹‹ጨቋኝ አይደለህም›› ‹‹ለዴሞክራሲና አንድነት ትተጋለህ››....በሚል አዲሱን ወይን በአሮጌው አቅማዳ ይዞ፣ ከፊት ለፊት ቆሞ ሲያርድና ሲያሳርድ የነበረው ህዝብ በአዲስ ስልት ከጀርባ ቆሞ ሊያርደውና ሊያሳርደው መዘጋጀቱን የሚያሳይ ነው፡፡
ዛሬ በየሄደበት ‹‹ጡት ቆራጭና ጨቋኝ›› እየተባለ የሚሳደደውና የሚሰቃየው ህዝብ በአማራነቱ፣ በኢትዮጵያዊነቱ፣ ወኪል ቢኖረው ኖሮ ብአዴን ፅ/ቤት ላይ ተሰብስቦ ሲያለቅስ ምላሽ ባገኘ ነበር፡፡ እነ መላኩ ፈንታ ‹‹ምላሽ ይሰጣቸው›› በማለታቸው ወደ ዘብጥያ ተወርውረዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አማራ በመሆናቸው ብቻ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው (አማራ ማለት ሽብር ሆኗልና) ጥቂት የቂሊንጦ ነዋሪዎችን ስም ዝርዝር ላካፍላችሁ፡-
1. በእነ አለላቸው አታለለ የክስ መዝገብ 5 ሰዎች
2. በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
3. በእነ ዘመነ ምህረት የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
4. በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ 16 ሰዎች
5. በእነ አበበ ካሴ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
6. በእነ አስማረው አሰፋ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
7. በእነ ታደሰ ፈረደ የክስ መዝገብ 5 ሰዎች
8. በእነ ገ/ሚካኤል ገ/ስላሴ የክስ መዝገብ 9 ሰዎች
9. በእነ ነገደ ሸዋቀና የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
10. በእነ አጥናፉ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
11. በእነ አበበ ተመስገን የክስ መዝገብ 12 ሰዎች
12. በእነ መብራቴ ይርጋ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
13. በእነ ሁሴን አሊ የክስ መዝገብ 4 ሰዎች
14. በእነ አበበ የኋላ የክስ መዝገብ 4 ሰዎች
15. በእነ አዳሙ ታዬ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
16. በእነ ፀጋው አለሙ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
17. በእነ ቸሬ ተክሉ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
18. በእነ ሰጠኝ ሙሉ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
19. በእነ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
20. በእነ አንተነህ የክስ መዝገብ 2 ሰዎች
21. በእነ አቤል ከበደ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
22. በእነ አብርሃም ሞገስ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
23. በእነ ማስረሻ ታፈረ የክስ መዝገብ 9 ሰዎች
24. በእነ ሊጋባው ግርማ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
25. በእነ ፋንታሁን የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
26. በእነ ተፈራ በላይ የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
27. በእነ አስቻለው የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
28. .........እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ በታች የምዘረዝራቸው ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ የሚገኙ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ናቸው፡፡
1. አለማቸው ማሞ የ60 አመት አዛውንት
2. ፀጋው ካሳ የ78 አመት አዛውንት
3. ቢሆነኝ አለነ የ60 አመት አዛውንት
4. አዋጁ አቡሃይ የ75 አመት አዛውንት
5. የሻለቃ ሰጠኝ ሙሉ የ75 አመት አዛውንት
6. ወርቁ አያሌው የ67 አመት አዛውንት
7. ይርጋ አሳምረው የ68 አመት አዛውንት
8. በላይ ብሩ የ68 አመት አዛውንት ናቸው፡፡
ከላይ በስም ከጠቀስኳቸው ውስጥ ማስረሻ ሰጠኝ፣ አንተነህና አቤል ከበደ የአየር ኃይል አብራሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሌሎች ጋር የተከሰሱት የአማራ ተወላጆች፣ ከቂሊንጦ ውጭ የሚገኙት (በማዕከላዊ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ፣ አማራ ክልልና ውጡ እየተባሉ በሚባረሩባቸው አካባቢዎች) በስቃይ ላይ የሚገኙትን አይጨምርም፡፡ ይህን ፅሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት እንኳን አማራ ወደሚሰቃይበት ማዕከላዊ እስር ቤት ከ100 በላይ የሚሆኑ አዲስ ‹‹ሽብርተኛ›› ወጣቶች ከጎንደርና ጎጃም ተለቅመው እንደገቡ መረጃ ደርሶኛል፡፡ እና የ35ኛው የብአዴን በዓል ለአማራ ህዝብ ምኑ ነው? ህዳሴ? ኩነኔ?
አበቃሁ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments: