Friday, November 20, 2015

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብሪታኒያ ከኢትዮጵያውያን ጎን እንድትቆም ጥሪ አቀረቡ

• ‹‹የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ ኢትዮጵያን ከመፍትሄ አካልነት ወደ ችግርነት እያንደረደራት ነው››
• ‹‹በቀጠናው የሚደረገው የእሳት ማጥፋት ፖለቲካ ኢትዮጵያን ወደ አለመረጋጋት እየመራ ነው›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት የብሪታኒያ አምባሳደር የሆኑትና የስራ ዘመናቸውን አጠናቀው የሚመለሱት አምባሳደር ግሪጎሪ ጋር ህዳር 9/2008 ዓ.ም ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ የሆነችው ብሪታኒያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያውያን ጎን እንድትቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ከሊቀመንበሩ ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል ውይይት ያደረጉት የብሪታኒያ አምባሳደር በወቅታዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተነጋግረዋል፡፡
ከ2007 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ያለውን የኢትዮጵያን ሁኔታ በስፋት ያስረዱት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የወጣቱ ስራ አጥነት፣ የፖለቲካው አፈና፣ ሙስና፣ የኑሮ ውድነቱና ሌሎችም ችግሮች በመቀጠላቸውንና በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ርሃብም የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ድምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ዜጎች ከቀያቸው ያለ አግባብ እንደሚፈናቀሉ፣ ይህንንም ሲክድ የነበረው መንግስት የተወሰኑትን መክሰሱን በጋምቤላ ክልል ዜጎችን ያፈናቀሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ላይ ራሱ መንግስት የመሰረተውን የክስ መዝገብ አስደግፈው ለአምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህ ሁሉ ችግር ውስጥ እያለች ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በቀጠናው ያለውን ችግር ለማብረድ ሲባል ለአጭር ጊዜ ጥቅም ከአገዛዙ ጋር በፈጠሩት ግንኙነት፣ ለኢትዮጵያ ችግር የበኩላቸውን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሊቀመንበሩ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ በሚወሰደው የእሳት ማጥፋት እርምጃም የአጭር ጊዜ ጥቅምን እንጅ የረዥም ጊዜ ስትራቴጅካዊ ግንኙነትን ያላገናዘበና ኢትዮጵያንም ወደ አለመረጋጋት እየመራ እንደሆነ ለአምባሳደሩ ገልፀውላቸዋል፡፡ በአጭር ጊዜ መፍትሄ ላይ ትኩረት እያደረገ የሚገኘው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ ኢትዮጵያን ከመፍትሄ አካልነት ወደ ችግርነት እያንደረደራት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ብሪታኒያ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ በመሆኗም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከአገዛዙ ይልቅ ከኢትዮጵያውያን ጎን እንድትቆምም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


No comments: