Monday, November 2, 2015

እነ የሺዋስ ለሁለተኛ ጊዜ ባልቀረቡበት ቀጠሮ ተሰጠባቸው

የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት 19 ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ከተበየነላቸው በኋላ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ዛሬ ጥቅምት 22/2008 . በሌሉበት ለጥቅምት 29/2008 . ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ጥቅምት 17/2008 . እንዲሁም ዛሬ ጥቅምት 22/2008 . እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው ለሁለተኛ ጊዜ በሌሉበት ቀጠሮ የተሰጠባቸው አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ሀምታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሽበሺና አብሯቸው ይገብኝ የተጠየቀበት አቶ አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡
በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ማስረጃ ዝርዝር ከብይን ጋር ተያይዞ ባለመቅረቡ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ መርምሮ ለመወሰን ስላልቻለ፤ ይግባኝ ያስቀርባል አያስቀርባል የሚለውን ለመወሰን በእስር ፍርድ ቤቱ ያሉ ዝርዝር የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ተያይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የእስር ፍርድ ቤቱ ላይ የቀረቡ የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች፤ በዋናነት የተከሳሾች ሞባይሎች፣ ከብሔራው ደህንነት ተገኙ የተባሉ ማስረጃዎች እንዲሁም በአብርሃም ሰለሞን ላይ የቀረበው የተከሳሽነት ማስረጃ ሲሆኑ አቃቤ ህግም ‹‹ማስረጃዎቼ በእስር ፍርድ ቤት ስለሚገኙ በቀጣይ ቀጠሮ አሟልቼ አቀርባለሁ›› ብሏል፡፡
በዛሬው ቀጠሮ ተከሰሾቹ ለምን እንዳልቀረቡ ምንም አይነት ምላሽና ትዕዛዝ አልተሰጠም፡፡ እነ የሽዋስ አሰፋ ጥቅምት 17/2008 . ባለመቅረባቸው ፍርድ ቤቱ ‹‹አቅርቧቸው ብለን አዘን ነበር፡፡ እኛ ነን የምናዛችሁ ወይስ ማን ነው? አሁንም ለቀጣይ ቀጠሮ አቅርቧቸው፡፡›› ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ባልቀረቡበት ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ


No comments: