ኢህአዴግ አለብኝ የሚለው የአስተዳደር ብልሹነት ችግር ሀገር ለመምራት የሚያስችል ቁመና እንደሌለው ጠቋሚ ነው፡፡
(ዋዜማ ራዲዮ)- ሰሞኑን መንግስት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ያሉትን የኪራይ ሰብሳቢነት እና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለማወቅ ያለመ ሦስት ወር የፈጀ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን ገልጿል ፡፡ ለናሙናም በአራቱ አባል ድርጅቶች የሚተዳደሩት ትላልቆቹ ክልሎች እና አዲስ አበባ ተካተዋል፡፡
የጥናቱ ውጤትም በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱም በመንግስት ባለስልጣናት መካከል ተቃርኖዎች ተስተውለዋል፡፡ ጥናቱም መልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ ስርዓቱ ምን ዓይነት ቀውስ ውስጥ እንዳለ የሚያመላክቱ ግኝቶችን አቅርቧል፡፡
(የቻላቸው ታደሰ የድምፅ ዘገባ ጉዳዩን በጥልቀት ተመልክቶታል -አድምጡት)
መንግስት በቅርቡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ባካሄደው ጥናት ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ያደረጉት በዓይነቱ ለየት ያለ ውይይት በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ግርምት ማጫሩ አልቀረም፡፡ ውይይቱ ግን ተቃርኖዎችን ያሳየ፣ መንግስት ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ግልፅ መፍትሄ እንደሌለው እና በጠቅላላው ስርዓቱ የገባበትን አጣብቂኝ የሚያሳይ ነበር፡፡
እንደተለመደው የባለስልጣናቱን ውይይት የቀረፀው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ቢሆንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን ለህዝብ እንዲተላለፍ እንዳዘዙ የዋዜማ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ለህዝብ ጆሮ የደረሰው ግን በጥንቃቄ የተመረጠው የተወሰነው ክፍል ብቻ ነው፡፡
የዋዜማ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሙሉ ስልጣናቸውን በመተግበር ቁልፍ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ የአሜሪካ መንግስት ዲፕሎማቶች ግፊት ሲያደርጉባቸው ቆይተዋል፡፡ በውይይቱ መቋጫ ላይም “ከዚህ ከወጣን በኋላ የየራሳችንን መረብ እንዳይነካብን እንከላከላለን” በማለት በካቢኔ አባሎቻቸው ላይ ጣታቸውን መቀሰራቸው ይህንኑ ያሳያል፡፡
ይሁንና ገና ከጅምሩ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከስረ መሰረታቸው ለመፍታት እንዳልቆረጠ የሚያሳየው ጥናቱ በፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ኃይል ልማት ሚንስቴር እና በአቶ መለስ ዜናዊ ህለፈት ማግስት የተቋቋመው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በጋር እንዲያጠኑት ማድረጉ ነው፡፡ ከተቋቋመ ከሦስት ዓመታት በላይ የሆነው የመልካም አስተዳደር ክላስተር ምንም ለውጥ ባያመጣም ክላስተሩ ግን በፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ኃይል ልማት ሚንስቴር ስር ይገኛል፡፡
መንግስት በገለልተኛ ሙያተኛ ተቋም ወይም ቢያንስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስጠናት እየቻለ በመንግስታዊ ተቋማት ያውም ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች እንዲጠና ማድረጉ ችግሩ ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳልሆነ ለማሳየት ስለፈለገ ብቻ ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ ካድሬ የሆኑት ሴኮ ቱሬ ጌታቸው የጥናት ቡድኑ አባል እንደነበሩ በውይይቱ ወቅት ሲናገሩ መደመጣቸው የጥናት ቡድኑን የሰው ሃይል ጥንቅር የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የጥናቱን አካሄድና ውጤቱንም አመኔታ የሚያሳጣ ነው፡፡
በውይይቱ በመንግስት ባለስልጣናት መካከልም ተቃርኖዎች ቁልጭ ብለው ታይተዋል፡፡የመልካም አስተዳደር ችግሩ መፈታት ያለበት በዘመቻ ነው ወይስ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሚለው ጉዳይ ላይም በውይይቱ የተሳተፉት ባለስልጣናቱ ተቃራኒ አስተያየቶችን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡
በውይይቱ በመንግስት ባለስልጣናት መካከልም ተቃርኖዎች ቁልጭ ብለው ታይተዋል፡፡የመልካም አስተዳደር ችግሩ መፈታት ያለበት በዘመቻ ነው ወይስ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሚለው ጉዳይ ላይም በውይይቱ የተሳተፉት ባለስልጣናቱ ተቃራኒ አስተያየቶችን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡
ጥናቱን ያካሄደው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም አስተባባሪው በረከት ስሞን መፍትሄው በዘመቻ መጀመር እንዳለበት አቋም ሲይዙ በአንፃሩ የማዕከሉ ዋና አስተባባሪ አባይ ፀሃዬ ደግሞ ችግሩ የሚፈታው ተቋማዊ አሰራርን በመዘርጋት እንደሆነ በአፅንዖት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በመጨረሻ የበረከት ስምዖንን አቋም እንደሚጋሩ አሳውቀዋል፡፡
ከ1997ቱ ምርጫ ወዲህ በመንግስት እና በፓርቲው መካከል ያለው መስመር መጥፋቱን የሚገልፁት እነ ፕሮፌሰር ክርስተፈር ክላፋምና ጆን አቢንክ ገዥው ድርጅት ሙሉ ትኩረቱን የፖለቲካ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ብቻ በማግኘት ላይ ማድረጉን ያወሳሉ፡፡ አመራሮቹ ደግሞ የሚሾሙት በብሄር ወይም በድርጅት ተዋፅዖ ስለሆነ መንግስት የራሱን አመራሮች ተጠያቂ ማድረግ አይፈልግምም፤ አይችልምም፡፡
ጥናቱ ስለ መንግስት ጨረታዎች ብልሹነት አንስቷል፡፡ ሆኖም በሀገሪቱ ግዙፍ ጨረታዎች ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት በህወሃት ባለስልጣናት ድርሻ የተያዙት የህወሃት ኢንዶውመንቶች እና በመከላከያ ሰራዊቱ ይዞታ ስር ያሉ በርካታ ኩባንያዎች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡
በእርግጥ ሙሉ ጥናቱ ይፋ ስላልሆነ የእነዚህ ጣልቃ-ገብ ድርጅቶች አሉታዊ ሚና በጥናቱ ውስጥ ስለመንፀባረቁ አልታወቀም፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በተለይም ህወሃት እነዚህ ኩባንያዎች በመልካም አስተዳደር ላይ ስላላቸው አሉታዊ ተፅዕኖ በፍፁም መስማት እንደማይፈልጉ ግልፅ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ለመጋፋት መሞከር እሳት የመጨበጥ ያህል እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የመሬት ጉዳይም ቢሆን ጥሩ ፖሊሲ በማውጣት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የገዥው ድርጅት የስልጣንና ሃብት ማሰጠበቂያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በጥናቱ ቢነሱም ባይነሱም መንግስት የመልካም ምአስተዳደር ችግሮችን እፈታለሁ የሚለው ስራ አስፈፃሚው ህግን አክብሮ እንዲሰራ የሚያስገድዱት የፌደራል እና ክልል ህግ አውጭ አካላት፣ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የመንግስትም ሆኑ ነፃ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ የፍትህ አካላት፣ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የሙያ እና ሲቪል ማህበራት የመሳሰሉትን ተቋማት ነፃነታቸውን ነጥቆ እና ቀፍድዶ ይዞ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ የፀረ-ሽብር ህጉን ሽፋን በማድረግ የግሉን ፕሬስ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ባሽመደመደበት ማግስት ነው፡፡ በባለስልጣናቱ ውይይት ላይ ግን የዴሞክራሲያዊ እና ነፃ ተቋማት መጠናከር እንደ ወሳኝ መፍትሄ ተደርጎ ሲቀርብ አልታየም፡፡
ኢህአዴግ የግንቦቱን ምርጫ በመቶ ፐርሰንት ማሸነፉ ያስከተለበትን ትዝብት ለማካካስ ስለ መልካም አስተዳደር መስበክ አንድ አማራጭ አድርጎ የወሰደው ይመስላል፡፡ ስለሆነም እንደ እስካሁን በፊቱ ሁሉ በውይይቱ የተንፀባረቁት ሃሳቦች አፋዊ ሆነው ላለመቅረታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ በጠቅላላው መንግሰት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንዳይችል በመዋቅራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ተጠፍንጎ መያዙን መካድ አይቻልም፡፡ በህዝብ እና መንግስት መካከል ላለው ግንኙነት ዓይነተኛ ማሳያ የሆነው መልካም አስተዳደርም የኢህአዴግ መራሹ ዋነኛ ፈተና ሆኖ ይቀጥላል፡፡
Source: wazemaradio
No comments:
Post a Comment