በፍቃዱ ዘ ኃይሉ
‹‹…ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ
አንድ የሚጠላ፣ አንድ የሚወደድ…››
ሕይወት መንገድ ነች፡፡ በየመንገዱ ከሰው ታወዳጀናለች፤ ከተወዳጀናቸው ታለያየናለች፡፡ እኔም በሕይወቴ ጎዳና በገጠመኝ የእስር ሕይወቴ ካፈራኋቸው ወዳጆቼ ዘላለም ወርቅአገኘሁ አንዱ ነው፡፡ ሁሌ ‹‹ለምን ሳንታሰር አልተዋወቅንም?›› እንባባላለን፡፡ ቀድሞ መተዋወቁ የተለየ ነገር ይፈጥር ይመስል፡፡
ዘላለም ወርቅአገኘሁ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው ሐምሌ 1፣ 2006 ነበር፡፡ ልክ ከእኛ ውስጥ (ከአቤል በቀር) ወንዶቹ ሁሉ ‹‹ሳይቤሪያ›› ከሚባለው ቀዝቃዛ የምድር ክፍል ወጥተን ‹‹ሸራተን›› ወደሚባለው አንፃራዊ ምቹ ክፍል የተዘዋወርን ዕለት ማለት ነው፡፡ እኛ ወደ‹‹ሸራተን›› የተዛወርነው ለካስ እሱን ጨምሮ ለነሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ እንዲሁም ለነባሕሩ፣ ዮናታን፣ አብርሃም እና ሌሎችም ቦታ መልቀቅ ስላለብን ነበር፡፡ አንድም እንዳንቀላቀል፣ አንድም ምሥጢር እንዳንለዋወጥ መሆኑ ነው፡፡ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የገባው፣የኛው ዘላለም ክብረት ወደነበረበት 5 ቁጥር ነበር፡፡ እዚያ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ከዚያ ክፍል ወጥቶ ጭራሹኑ መብራት ወደሌለውእና ከአንድ ሰው በላይ በማያሳድረው ጭለማ ክፍል (ስምንት ቁጥር ) ውስጥ ገብቷል፡፡ ስምንት ቁጥር ውስጥ 41 ቀናት ቆይቷል፡፡
በጨለማ ቤት 24 ሰዓት፣ ለብቻ መቆየት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ መገመት ይከብዳል፡፡ ለተወሰኑ ቀናት ከአብርሃ ደስታ ጋር ተጎራብተዋል፡፡ ከዚያ በፊት ባይተዋወቁም(ዘላለም በሥም ያውቀው ነበር) ግድግዳ እየደበደቡ ይነጋገሩና ማፅናኛ ቃላትም ይለዋወጡ እንደነበር ሁለቱም ነግረውኛል፡፡ ዘላለም ከታሰረ ዓመት ሲሞላው ‹‹በእስር ቆይታዬ የተረዳሁት የ24 ሰዓትን ርዝመት፣ የዓመትን እጥረት ነው›› አለኝ፡፡ ‹እንዴት?›አልኩት፤ ‹‹ስምንት ቁጥር እያለሁ 24 ሰዓት ማለት ፈፅሞ የማያልቅ ረዥም የጊዜ ዓይነት ነው፡፡ ዓመት ደግሞ በእስር ዓይን መለስብለህ ስትመለከተው በጣም አጭር ነው፡፡ አሁን ሳስበው የገባኝ የሁለቱ አያዎ (paradox) ነው›› አለኝ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ‹‹በእስር ቤት አንዱ ቀን ከሌላኛው ቀን፣ አንዱ ሳምንት ከቀጣዩ ሳምንት፣ ወሩ ከሚቀጥለው ወር ጋር አንድ ዓይነት ናቸው›› ብለው ጽፈዋል፡፡ እውነት ነው፤ ስለዚህ መለስ ብለው ሲመለከቱት ዓመቱ በጣም አጭር ይመስላል፡፡ ዘላለም የተረዳው ያንኑነው፤ የጨለማ ቤቷን ተሞክሮ የገለፀልኝ ደግሞ እኔ ልገልፀው ስቸገር የነበረውን ነው፡፡
ዘላለም ወርቅአገኘሁ ካየኋቸው ክሶች ሁሉ የተንዛዛ ክስ ነው የተመሠረተበት፡፡ ክሱ ብቻውን ዘጠኝ ገጽ ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ያደረገው ቻት፤ ቤቱ የተገኙ የትምህርት እና ሌሎችም ጽሑፎች በሙሉ ክሱ ውስጥ ተተንትነዋል፡፡ ማስረጃ ተብለው ተያይዘዋል፡፡ ከተያያዙበት የሰነድ ማስረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን ለትዝብታችሁ ያክል ልንገራችሁ፡፡
አንድ ገጽ ሙሉ በእስኪርቢቶ የተጻፈ ጽሑፍነው፤ እንዲህ ይነበባል፣
“If Blogging is a Crime,
then I am a Blogger too.
Free Zone9 Bloggers”
እንዳየሁት በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ብዙ ሰዎች በእጃቸው ‹‹መጦመር ወንጀል ከሆነ እኔም ጦማሪ ነኝ፤ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ይፈቱ›› የሚል ጽሑፍ ይዘው ፎቶ እየተነሱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየለጠፉ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን የሽብር ክስ ማስረጃ ሰነድ ሆኖ ይመጣል ብዬ ግን ጠርጥሬ አላውቅም፡፡ ኢሕአዴግ ብዙ ጊዜ ያስገርመኛል (surprise ያደርገኛል)፡፡ በዚህም አስገረመኝ ከማለት ውጪ ቋንቋ የለኝም፡፡
ሌላም በጣም አስገራሚ ሰነድ ‹‹የሠራኸውን ወንጀል›› ያስረዳል ተብሎ ቀርቦበታል፡፡ ሰነዱ አንዳንዶች እንደሚሉት ‹‹ለኢሕአዴግ ብሉይ ኪዳኑ ነው››፡፡ ሰነዱ “On the Questions of Nationalities in Ethiopia” ይላል፡፡ የብሔር ጥያቄን በወረቀት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አቀንቅኗል የሚባልለት የዋለልኝ መኮንን መጣጥፍ ነው፡፡ ታዲያ የዚህ መጣጥፍ ገጽ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ክስ ላይ ማስረጃ ሰነድ ተብሎ ተያይዟል፡፡ይህንን ሰነድ ምን ብለው ያስተባብሉታል?
እነዚህም ብቻ አይደሉም፡፡ ዘላለም በታሰረበት ወቅት በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ማስተርሱን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እያጠና ነበር፡፡ ታዲያ በወቅቱ ያገላብጣቸው የነበሩ ጥናቶችምማስረጃ ተብለው ከክሱ ጋር ተያይዘው ቀርበውበታል፡፡ ለምሳሌ የሚከቱሉት ርዕሶች ያሏቸው ጽሑፎች አሉ፤ “Academic freedom” (የትምህርት/ማስተማር ነጻነት)፣ “University for Society” (ዩንቨርስቲ ለማኅበረሰብ)፣ እና “Social Service” (ማኅበራዊ አገልግሎት)፡፡ እንግዲህ እነዚህ በይፋ የሚታወቁ ትምህርት ነክ የሆኑ አጀንዳዎችን የሚታወቁ ጥናቶችን ማስረጃ ብሎ የሽብር ክስ ላይ ማያያዝ አንድም የከሳሾቹን አላዋቂነት ያሳብቃል፡፡ ያውቃሉ ቢባል እንኳ እያወቁ አጥፊነታቸውን ይናገራል፡፡ በተጨማሪም፣ የኔልሰን ማንዴላ ‘Long Walk To Freedom’ የተሰኘውና ከዋናው እትም አጥሮ የተጻፈው መጽሐፍ ገጽ 25 ላይ የሰፈረው፣ ኔልሰን ማንዴላ ‹የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ›፣ ፓርቲያቸው ‹የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ› ለሚያደርገው ትግል አርኣያ እንደሆነው የሚያትቱበት ጽሑፋቸው ዘላለም ላይ ማስረጃ ተብሎ ተጠቅሶበታል፡፡
ዘላለም በዐቃቤ ሕግ ምስክር ሳይቀር የተነገረበት አንዱ ‹‹በሽብር ተፈርዶበት ውጪ አገር ከሚኖር የግንቦት 7 አመራር ገንዘብ ተልኮለታል›› የሚለው አንዱ ሲሆን፣ ይህንኑ ያስረዳል ተብሎ የተያያዘው ሰነድ ግን የሚያስረዳው ሌላ ነገር ነው፡፡ ሰነዱ የሚያስረዳው ተድላ ደስታ የተባለ ሰው ሦስት መቶ ዶላር እንደላከለት ነው፡፡ ተድላ ደስታ የ‹ደ ብርሃን› ጦማር ጸሐፊ ሲሆን፣ የግንቦት 7 አመራር ቀርቶ አባል ስለመሆኑ ምንም መረጃ ያልቀረበ ከመሆኑም በላይ ‹‹የተፈረደበት›› የሚለው ገሀድ ውሸት ነው፡፡
እንዲህ እና መሰል ክሶችን ታቅፎ የቆየው ዘላለም ነሐሴ 14/2007 ቀድሞ የተከፈተበት አንቀጽ 4 (ሲያንስ 15 ዓመት፣ ሲበዛ ሞት የሚያስቀጣ) ተቀይሮለት በአባልነት ብቻ፣ማለትም 7/1 (ቢበዛ 10 ዓመት የሚያስቀጣ) አንቀጽ ተደርጎለት እንዲከላከል ተወስኖበታል፡፡ የዛኑ ዕለት በእሱ መዝገብ የተከሰሱትአራቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አብርሃም ሰለሞንም ‹‹ነጻ›› ተብለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በማለቱና የፍቺእግድም ከጠቅላይ ፍ/ቤት በማሳዘዙ እስከዛሬ አልተፈቱም፡፡ ሌሎቹ የዘላለም ጓደኞች ባሕሩ እና ዮናታንም ቀድሞ በተከፈተባቸው አንቀጽ7/1 እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል፡፡ የዘላለም ጓደኞች የተያዙት ከዘላለም ጋር በመሆን ወደውጭ አገር በመጓዝ የኢንተርኔት ደኅንነትሥልጠና ሊወስዱ በተለዋወጡት ኢሜይል ሳቢያ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሥልጠናውን እያመቻቸላቸው የነበረው በስደት ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ ሲሆን፣ አርጋው በክሱ መዝገብ ላይ ‹‹የግንቦት 7 አመራር›› ተብሎ ነው የተጠቀሰው፡፡ አርጋው አሽኔም እንደ ተድላ ደስታ ሁሉ እንኳን የግንቦት 7 አመራር ሊሆን አባል መሆኑንም የሚያስረዳ ማስረጃ የለም፡፡ ዛሬ ዘላለምና አራቱ ፖለቲከኞች በወኅኒ 500ኛ ቀናቸውን ያከብራሉ፡፡ ያከብራሉ ይባላል ወይ ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ! ሌሎቹም በዘላለም ሥም በሚጠራው መዝገብ ላይ ያሉ የሕሊና እስረኞች ከሰሞኑ 500 ቀን ይሞላቸዋል፡፡
እኛ ስንያዝ የተረፉ (እና የተሰደዱ)ጓደኞቻችን ሰው ሊረዳላቸው ያልገባቸው ፈተና ውስጥ እንደነበሩ ሲያደርጉ ከነበሩት እና ሲልኩብን ከነበሩ መልዕክቶች ሰምተናል፣ ተረድተናል፡፡ፈረንጆች ይህ ዓይነቱን ጉዳይ ‘survival’s guilt’ (‹የተራፊዎች የጥፋተኝነት ስሜት› እንበለው?)ይሉታል አሉ፡፡ ከዚያ ደግሞ ድንገት ክሳቸው ተቋርጦ የወጡት አባሪዎቻችን እኛን የከዱን ዓይነት ስሜት ይንፀባረቅባቸው ነበር፤ ይኸው‹የተራፊዎች የጥፋተኝነት ስሜት› ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቀሪዎቹም ተራችን ደረሰና ተንጠባጥበን ስንወጣ እኔ የጓደኞቼን ሕመም በከፊልም ቢሆን የተረዳሁት የመሰለኝ ዘላለምን ተሰናብቼ ስወጣ ነው፡፡
ዘላለም እስሬን ካቀለሉልኝ ሰዎች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡ ውይይታችን፣ ንትርካችን ሁሉ የማይዘነጋ ነበር፡፡ ማታ፣ ማታ መታጠቢያ ክፍሉ ውስጥ ካለች ጠባብ ኮሊደር ውስጥ የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን እስከ ሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት የምንቆይበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ አምስቱ አባሪዎቼ ድንገት የወጡ ጊዜ የነበረውን የሐሳብ ውዥንብር እና የእንቅልፍ መዋዠቅ ከእሱ ጋር በማውራት ነበር ሰውነቴን ያላመድኩት፡፡ በእስር ቤት ቋንቋ ገበታ በጋራ የሚቋደሱ ሰዎች፣ መቅዱስ ነበር የሚባሉት፡፡ ዘላለም መቅዱሴ ብቻ አልነበረም፡፡ ወኅኒ የሰጠኝ ጓደኛዬም ነው፡፡ አሁን እቤቴቁጭ ብዬ አስበዋለሁ፡፡ ሳያመሽ መተኛት አይችልበትም፤ በጣም ያመሻል፡፡ ለቆጠራ 12፡30 በራችን ሲንኳኳ ‹ሀንጎቨር› እንዳለበትሰው ዓይኑ ቅልትልት ብሎ፣ ፎጣ ደርቦ ሲወጣ ይታወሰኛል፡፡ ኳስ ጨዋታ ሲኖር (እኔ ባልወድም) ከጎረምሳው ሁሉ ጋር ሲሟገት ይታየኛል፡፡ ሰው መንከባከብ ይችልበታል፤ ሲንከባከበኝ ትዝ ይለኛል ልበል? አዎ፣ እንደሚንከባከበኝ ስለማውቅ እኔም እቀብጥ ነበር፤ እሱም ሲንከባከበኝ አስገራሚ ነው፡፡
ዘላለም ወርቅአገኘሁ እና ጓደኞቹ (5ሆነው) የመጪው ሰኞ፣ ሕዳር 13፣ 2008 ራሳቸውን ለመከላከል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ እኔም እንደተመልካች ላያቸው እሄዳለሁ፡፡አልጨብጣቸውም፡፡ እጄን የማውለበልብላቸው ከሆነ እንኳን ፈራ ተባ እያልኩ ነው፡፡ እኔ ከትልቁ እስር ቤት ሆኜ፣ እነርሱ ደግሞ ከጠቧቧሁነው ያዩኛል፡፡ ‹ሁላችንም ነጻ ካልወጣን፣ አንዳችንም ነጻ ወጣን ማለት አይቻልምና!›
መልካም ዕድል ከመመኘት በላይ ምን አቅም አለኝ፡፡ መልካም ዕድል፣ የክፉ ቀን ጓዴ! መልካም ዕድል!
Source: Zone9
No comments:
Post a Comment