Monday, November 9, 2015

እኔ ምን አይነት ሰው ነኝ???



"እሱ ምን አይነት ሰው እንደሆነ እያወቃችሁ፣ ከእሱ ጋር መቀራረብና አብሮ መስራታችሁ በእናንተና በቤተሰባችሁ ላይ የሚያስከትለውን ችግር ተረድታችኃል? መኖር አትፈልጉም? ………"

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ኢህአዲግን ከተጠናወተው መጥፎ አባዜ ሁሉ የከፋው የሀሳብና የፓለቲካ አቋም ልዩነት ኖሯቸው ስርአቱን የተቃወሙን ሁሉ በጠላትነት መፈረጁ ነው። ፈርጆም አያቆምም። ተፎካካሪ ወይም "ተቃዋሚ" (ተቃዋሚ የሚለው ቃል ለእኔ አይመቸኝም) የሆኑን ግለሰቦችና ተቋማት ሁሉ እያሳደደ፣ ያለ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም ለማጥፋት፣ለማሸማቀቅ፣ለማስፈራራት፣ለመግታት፣……………… የማይፈነቅለው ዲንጋይ የለም። ለዚህም ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስውርና ግልፅ የአፈና መዋቅሮችንና ስልቶችን ይጠቀማል። ለዚህም ሀገራችን አሁን የምትገኝበት በወረቀት የገዘፈ በተግባር እንደ ካሮት ወደታች የሚያሽቆለቁለው የዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ ሂደት አንዱ ማሳያ ነው። በተጨማሪም ኢህአዲግ ላለፋት አስርት አመታት ሌት ተቀን አስፋፍቶ በገነባቸው ቃልቲና ቂሊንጦን መሰል አሸን እስር ቤቶች በሀሳብ ልዩነታቸው፣በፓለቲካዊ አቋማቸው፣ ሀሳብን በነፃነት በመግለፃቸው፣……… ወዘተ በግፍ የታሰሩና በስቃይ ላይ ያሉ / ወገኖቻችንን ለአፍታ በአይነ ህሊናችን ቃኘት ማድረጉ የስርአቱን መጥፎ አባዜ ለማወቅ ከበቂ በላይ ነው። ይህ ለመሆኑ ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ኢህአዲግን የተጠናወተው "የእኔ ብቻ ልወቅላችሁ አባዜ" ነው። እንግዲህ ይህ አባዜ ነው ስርአቱን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሞገትን፣የተቃወምን፣የህዝብን ብሶትና እሮሮ ያስተጋባን፣ አማራጭ ፓሊሲ አለን ያልን፣ ህገ መንግስታዊ መብታችንን የጠየቅን፣…………… ወዘተ ሰላማዊ ታጋዮች ለእስር፣ ለስውር አፈናና ስቀይ፣ ለስደት፣ ለማህበራዊ መገለል፣ ለኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ፣ ለዛቻና ማስፈራሪያ ብሎም ለተቀነባበረ ሞት የዳረገን።

××× ××× ×××
እኔም እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ባለኝ የፓለቲካ አቋምና ለህገ መንግስታዊ መብቴ መከበር የማደርገውን ሰላማዊ ትግል ተንተርሶ ከተራ ማስፈራራትና ተዘዋዋሪ አሉታዊ ተፅእኖ እስከ ከፍተኛ የአፈና ተግባር ተፈፅሞብኛል፣እየተፈፀመብኝም ይገኛል። በቅርቡ እንኳ የመንግስት ሀይሎች ነን በሚሉ አካላት ከተሳፈርኩበት አውቶብስ ላይ ታፍኜ ያለምንም ክስ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ባልታወቀ ድብቅ ማሰቃያ እስር ቤት ለወራት የተፈፀመብኝ ግፍ አንድ ማሳያ ነው። ነገርግን ይህ ሁሉ ለቆምኩለት አላማ የማደርገውን ጉዞ በይበልጥ እንድገፋበት ያጠነክረኝ እንደሆነ እንጂ አንዲት ስንዝር ወደኃላ አይመልሰኝም። በዚህ ፅሁፌም እንደምሳሌ እንጂ የደረሰብኝን መንግስታዊ በደል መዘርዘር አላማዬ አይደለም። ምክንያቱም እንደዚህ ባለው "የሀሳብ ልዩነት ጠል" አንባገነናዊ ስርአት ውስጥ ስለሀገሬ እኔም ያገባኛል፣ መብትና ነፃነታችን ይከበር ብለን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ስንወስን አልጋ በአልጋ የሆነ ጉዞ እንደማይገጥመን አውቀንና ተረድተን የሚከፈለውን ሁሉ መስዋትነት እየከፈልን እንደሻማ ቀልጠን በሀገራችን የሚፈለገውን የነፃነትና የዴሞክራሲ ጮራ እንዲፈነጥቅ የበኩላችንን ለመወጣት ወስነን ነውና ነው። ነገርግን የሰሞንኛው በስርአቱ ባለሟሎች እየተፈፀመብኝ ያለው ሰው የማሳጣትና ማህበራዊ መገለል ለማድረስ እየደረገ ያለው አስቂኝና የወረደ ዘመቻ እጅግ ስላስገረመኝና በህሊናዬ ጥያቄን ስለጫረብኝ ለመላው ኢትዮጵያዊና ለታሪክ ለማስቀመጥ ብሎም ለድርጊቱ ፈፃሚዎች አንድ ጥያቄ ለመጠየቅ ወደደሁና ሀሳቤን በፌስቡክ ገፄ እንዳሰፍር ተገደደሁ።

××× ××× ×××
ሰሞኑን በሚገርም ሁኔታ ከእኔ ጋር የሚቀርቡ በተለይም ባለችኝ አነስተኛ ድርጅት ውስጥ የስራ እድል ፈጥሬላቸው በሚሰሩ ሰራተኞቼ የሞባይል ስልኮች ወቅቱን ያልጠበቀ (ሌሊት) ካልታወቁ ነገርግን የመንግስት ሀይሎች ነን ከሚሉ ሰዎች ስልክ ይደወላል። የሚገርመው ደግሞ በሁሉም ስልኮች ላይ የሚተላለፈው መልእክት አንድ አይነት መሆኑ ነው። "ቆይ አንተ/አንች ምን እያደረክ/ እንደሆነ ታውቃለህ? መኖር አትፈልጉም? የምትቀርቡት ሰው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ከእሱ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ካላቆማችሁ በእናንተና በቤተሰባችሁ ምን ሊደርስ እንደሚችል እንድታቁት። ስራ ከፈለጋችሁ (በተለይ ለአንደኛው) ልንሰጣችሁ እንችላል። አለበለዚያ ለየት ያለሁኔታ ብናይ መውጫ መግቢያችሁን አውቀናል።………ወዘተ" የሚሉ ማስፈራሪያ አዘል ዛቻዎች ናቸው። እናም በሁኔታው ባልረበሽም በግለሰቦቹ ላይ የፈጠረውና የሚፈጥረው ተፅእኖ አስቤ መጨነቄ አልቀረም። ነገርግን ይሄም በመክፈል ላይ ያለሁት አንዱ መስዋትነት ነውና እራሴን ይበልጥ አጠነክርበታለሁ። ይሁን እንጂ በሰላምና በህጋዊ መንገድ ሰላማዊ ማህበራዊ ህይወቱን የሚመራን አንድን ግለሰብ ማህበራዊ መገለል እንዲሰማውና ሰው እንዳይቀርበው ለማድረግ ተራና ሀላፊነት አለብኝ ከሚል አካል የማይጠበቅ የወረደ ተግባር ለሚፈፅሙት አካላት "………… ምን አይነት ሰው እንደሆነ ታውቃላችሁ?" ብለው ሰዎችን ለማሸማቀቅ ሲሞክሩ፣ ምን የምትል ካባ ሊደርቡልኝ አስበው ነው ደግሞ፣ የሚለው ሀሳብ አግራሞት ፈጠረብኝና እንዲህ ልላቸው ወደደሁ። …………

××× ××× ××× 
እናንት ባለግዜዎች ሆይ! ሁሉን ማድረግ እንችላለን ብላችሁ የምታስቡ! መጠሪያችን በእናንተ ፈቃድ ነውና… … ለመሆኑ! እኔ ምን አይነት ሰው ነኝ??? ……… ሰላም። አንዲት / ለዘላለም ትኑር!!!

No comments: