Thursday, June 25, 2015

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

ሰኔ ፲፰ (አስራ ሰምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ አንዳርጋቸው የህግ ድጋፍ በማያገኙበትና ይግባኝ ሊጠይቁ በማይችሉበት ሁኔታ በአስከፊ ሁኔታ መታሰራቸውን የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሀሞንድ አውግዘዋል።
የአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ እና ደህንነት እንደሚያሳስበን በተደጋጋሚ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም ብንገልጽም ከቃል ያለፈ መልስ አለገኘንም፣ የምክር እና ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበት መብትም አላገኙም ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በተደጋጋሚ ለቀረበው ጥያቄ ኢትዮጵያ መልስ መንፈጓ ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጠው የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ጥላ አደጋ ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸው በአስቸኳይ የህግ ድጋፍና ምክር እንዲያገኙ፣ በቤተሰቦቻቸውም እንዲጎበኙ መንግስት እንዲፈቅድ ለቴዎድሮስ አድሃኖም መናገራቸውንም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጠው መግለጫ ጠቅሷል።
አቶ አንዳርጋቸው በየመን ተላልፈው ከታሰሩ ልክ አንደኛ ዓመት መሆናቸውን አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባው መንግስት የተወሰደው እርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው በግልጽ ያመላከተ ነው ተብሏል።
የውጪ ጉዳይ ቢሮው ጉዳዩን ከዲፕሎማሲያው ልውውጥ በላይ በማድረግ ለአደባባይ ማብቃቱን ዘጋርዳያን ዘግቧል።
ከእንግሊዝ መንግስት ከፍተኛ እገዛ የሚያገኘው ኢህአዴግ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለሰጡት ማስጠንቀቂያ የሰጠው መልስ በመግለጫው አልተጠቀሰም።
ኢህአዴግ በውጭ ሃይሎች ግፊት እንደማይንበረከክ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የኢህአዴግን እጅ ሊጠመዝዙ የሚፈልጉ ሁሉ ገንዘባቸውን ይዘው በሊማሊሞ መሄድ ይችላሉ ብለው ነበር።
Source: Ethsat

No comments: