Monday, June 15, 2015

እነ ወይንሸት ሞላ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ


መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰሩት ወንይሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬና ዳንኤል ተስፋዬ ዛሬ ሰኔ 8/2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ተያዙ በተባሉበት ወቅት መስቀል አደባባይ ላይ እንዳልነበሩ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተዋል፡፡ ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ወረታው ዋሴን እና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ወጣት እያስፔድ ተስፋዬን በመከላከያ ምስክርነት አቅርባለች፡፡ አቃቤ ህግ ወይንሸት ሞላ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም ከቀኑ አራት ሰዓት ተኩል ላይ መስቀል አደባባይ ላይ በፖሊስ እንደተያዘች ክስ መስርቷል፡፡ ሆኖም ወጣት እያስፔድ ተስፋዬ በወቅቱ ከጠዋቱ 2 ሰዓት አካባቢ ከወይንሸት ጋር በስልክ እያወሩ በነበረበት ወቅት ላይ መያዟን እንደገለጸችለትና ስልኳ ክፍት ስለነበር ደህንነቶቹ ሲይዟት የነበረው ሁኔታ ማዳመጡን ይህንን የስልክ ንግግርም ፍርድ ከቴሌ አስመጥቶ ሊሰማው እንደሚችል ገልጾአል፡፡ በተጨማሪም ወይንሸት መያዧን ለፓርቲው አመራሮችና ለነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ደውሎ በመንገሩ ከሶስት ሰዓት በፊት ወይንሸት መታሰሯ መዘገቡን ገልጾአል፡፡ አቶ ወረታው ዋሴ በበኩሉ ወጣት እያስፔድ ወይንሸት መታሰሯን በነገረው መሰረት ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ መታሰሯን ማረጋገጡንና ምግብም ማስገባቱን ጠቅሶ መስክሯል፡፡
በተመሳሳይ በዕለቱ ከቀኑ አራት ሰዓት ተኩል ላይ በፖሊስ እንደተያዘ ክስ የተመሰረተበት ኤርሚያስ ፀጋዬ ተያዘበት በተባለበት ሰዓት በቦታው እንዳልነበር አስመስክሯል፡፡ በመከላከያ ምስክርነት የቀረቡት አባቱና ጓደኛውም በወቅቱ ከኤርሚያስ ጋር የገበያ ጥናት ላይ እንደነበሩና የተያዘውም ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ካፌ ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በእነ ወይንሸት መዝገብ ክስ የተመሰረተበት ሌላው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ዳንኤል ተስፋዬም በፖሊስ የተያዘው አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ባስቀመጠበት ሰዓት ሳይሆን 6 ሰዓት ተኩል ላይ እንደሆነ፣ የተያዘውም መስቀል አደባባይ ላይ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላይ መሆኑን እንዲሁም በተያዘበት ወቅትም ደህንነቶች ሲደበድቡት ማየቷን እህቱ የመከላከያ ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችና አቃቤ ህግ መፋረጃ እንዲያቀርቡ ያዘዘ ሲሆን ጉዳዩን ለማየትም ለሰኔ 15 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ ዜና በሰልፉ ወቅት ከ200-300 ያህል ሰዎችን በማደራጀትና በመምራት ሁከትና ብጥብጥ ፈጥራለች ተብላ ከግንቦት 4/2007 ዓ.ም ጀምሮ ታስራ የነበረችው ሜሮን አለማየሁ በዛሬው ዕለት በዋስ ተለቃለች፡፡ በተመሳሳይ መዝገብ ተከሶ የነበረው አቶ ዳዊት አስራደም ሰኔ 5/2007 ዓ.ም በዋስ መለቀቁ ይታወሳል፡፡

No comments: