‹‹የአሁን እኛ?››
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ምሽቶችን የሚያደምቁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጫወታዎን የሚታደሙ፣ ከዚያም አልፈው ጎራ ለይተው የሚሰዳደቡና የሚወቃቀሱ፣ የባሰ ዕለት ደግሞ በትልልቅ ጫወታዎች መልክ ጎራ ለይተው የሚቧቀሱ ወጣቶችን ማየት የከረመ አገራዊ ትዕይንት ሆኗል፡፡ ቅጥ ባጣ የፈረንጅ እግር ኳስ ፍቅር፣ ‹‹ከብርሃን ፍጥነት›› በላይ እየተስፋፉ ባሉ ‹‹የሱስ መሰረተ ልማቶች›› ውስጥ በመጥፋትና በቸልተኝነት የሚታማው ይህ ትውልድ ከላይ በተጠቀሱ ‹‹አደንዛዥ›› ጉዳዮች ተጠልፎ ካልወደቀም በጥልቅ ‹‹ራስን የማዳን›› ስሜት በመዋጥ አገሩን የረሳ፣ ፖለቲካ የማይገደው፣ ምርጫ የማያሳስበው ትውልድ ነው ተብሎ ይታማል፤ አለፍ ሲልም ደግሞ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስደት ወደተገኘው አገር ለመጓዝ ልቡ የቆመ፣ በአገሩ ተስፋ የቆረጠ፣ በየትኛውም አጋጣሚ አገር ጥሎ ለመሄድ ጓዙን ጠቅልሎ የተሰናዳ ወጣት እንዴት አገርን ይረከባል? ሊረከብስ ቢዘጋጅ ከማን እና እንዴት ይረከባል? ይህችን አገር ከእኛ የሚወስዳት ማነው የሚሉ ‹‹አባቶችም›› መኖር ሌላው ነባራዊ ሐቅ ነው፡፡
ለዚህ ዓይነቱን ትውልድ መፈጠር (ዓይነቱ ይሄ አይደለም ብለው የሚከራከሩ ባይጠፉም) ኃላፊነት የማይወስዱበት ‹‹የጎረቤት ልጅ›› ይመስል እዚህ ለመድረሱ ኃላፊነትን አንወስድም ዓይነት አንድምታ ያላቸውን ሐሳቦች መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደውም አልፈው፣ ተርፈው ‹‹በእኛ ዘመን ቀረ!››ን ልክ እንደ አንድ የታሪክ ኩራት መገለጫ ያደረጉና ትውልዳዊ ኃላፊነታቸውን የረሱ ፖለቲከኞች ስለምክንያቱ ከማውራት ይልቅ ውጤቱን መውቀስ ይቀናቸዋል፡፡
ለምን? ለምን? ለምን?
‹ዛሬ ያለው እውነታ ለምን እንዲህ ሆነ? ትውልዱ ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው? እውነትስ ጉዳዩ ‹‹የእሳት ልጅ አመድ›› ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ነውን?› የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳት የደፈረ፣ ለመመለስ የሞከረ ‹‹የእሳትም ሆነ የአመድ ትውልድ›› ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሰረቱ ትውልዶች የሚያልፉበት መንገድ እና ሁኔታ ከዘመን ዘመን በብዙ የተለያዩ መንስኤዎችና ምክንያቶች የተሞላ በመሆኑ የእያንዳንዱ ትውልድ መንገድ ከሌላው በእጅጉ ይለያል፡፡ ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ለመወራረስ ባንችል እንኳን የቀደመው ትውልድ በቀደደው መንገድ እያሰፉና እያጠበቡ፣ አቋራጭና ቅርንጫፍ እየጨመሩ መጓዝ የተከታይ ትውልድ ኃላፊነት ሲሆን መንገድን ማሳየትና መምራት ደግሞ የቀደመው ሥራ ነው፡፡ በአገራችን ነባራዊ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የተደናበረ፣ መንገድ የጠፋው መስሎ የሚታየው ወጣት ራሱ በቀየሰው አዲስ መንገድ ሳይሆን፥ ባሳዩት ጎዳና ላይ የሚጓዝ መሆኑን መካድ ኃላፊነትን ለመውሰድ ያለመፈለግ ስሜት ካልሆነ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡
የከሰረው ትውልድና የተቆራረጠው የትወልድ ትይይዝ
አንድ ትውልድ በዕድልም ሆነ በስርዓት አገርን ተረክቦ ከማስተዳደር (ከመግዛት)፣ ለአገር ከመጋደል፣ ከመወቃቀስና ለዓመታት ከመኮራረፍ በተጨማሪ የሚጠበቅበት ትልቁ የቤት ሥራ ተተኪና ያገባኛል የሚል ትውልድ መፍጠር ነበር፡፡ የቀድሞው (ከሠላሳ ዓመት በላይ በፖለቲካው ተሳታፊ የነበሩት) ትውልድ ዘመን ሰዎች ከከሰሩባቸው የተለያዩ ጉዳዮች በተጨማሪ ትልቁ ኪሳራ ‹‹የሚያገባው ትውልድን›› መፍጠር ያለመቻላቸው ጉዳይ ነው፡፡ በዘንድሮዋ ኢትዮጵያ ገዢውም ሆነ ተቃዋሚው የአንድ ትውልድ ቡድን ለስልጣን ቁምነገር የሚሰጡትን ትኩረት ያህል እነርሱ በቅርቡ ትተዋት ለሚሄዷት ኢትዮጵያ ተረካቢ ወጣት አንድም ቀን ተጨንቀው ሲያወሱ፣ ፕሮግራም ሲቀርፁና አዲስ መሪ ሲያበቁ አይስተዋሉም፡፡
አልፎ፣ አልፎ በሰሞንኛ ፋሽን መተካካት እና የወጣቶች ተሳትፎ ተብሎ ሲጠቀስ ወይ ስለ ስልጣን መረካከብ፣ ወይም ደግሞ የወጣት ፓርቲ አባላቶችን ቁጥር ስለማሳደግ ሆኖ ጉዳዩ ባጭሩ ይቀጫል፡፡ ትውልዱ ከታላላቅ ኪሳራዎቹ ‹‹ከቀይ ሽብር››፣ ‹‹ከኩርፊያው››፣ ‹‹ከደረቅ የማይለወጥ›› አቋም ባለቤትነቱ በተጨማሪ ‹እራሴ የጀመርኩትን የማስቀጥለው እኔ ነኝ› በሚል አቋሙ ሌላ ኪሳራ ላይ ወድቋል፡፡ ላለፉት አምስት አሥርት ዓመታት የአገሪቷ ፈላጭ ቆራጭ ትውልድ ከላይ በተጠቀሱት አገራዊ ቁስሎች እንጂ የትውልድ ቅብብሎሹን በመበጣጠሱ ብዙም ሲተች አይስተዋልም፡፡
‹‹ባለስልጣን›› ወይስ ‹‹ባለቤት››?
በገዢው ፓርቲ ጎራ ያሉ አካላት የአገር ባለቤትነት ጥያቄን ወደስልጣን ጥያቄ ለማሻገር በመካከሉ ለሰኮንዶች ማሰብ እንኳን አይጠይቃቸውም፡፡ ‹አገሬን ያለ ወንበሩን ያለ› እስኪመስል ድረስ ስለመተካካትም ቢሆን ሲወራ ስለስልጣን እንጂ ስለአገር ተነስቶ አያውቅም፡፡ የተቃዋሚ ጎራም በበኩሉ የወጣቱን የአገር ባለቤትነት ጥያቄ ‹‹እኛስ መች ገና ባለቤት ሆንን?›› በሚል ስሜት ችላ ሲለው ይታያል፡፡ ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ወጣት ገለል ያደረገ ስርዓት ዘርግቶ ‹‹መተካካት›› በሚል መሰላል ግለሰቦችን ወደላይ ማውጣት ‹‹ነባሩን ፊት በአዲስ›› ከመቀየር ውጪ የኢትዮጵያን ወጣት ምን ገዶኝ ከሚል ስሜት ለማላቀቅ ምንም ዓይነት አስተዋጽዖ አያደርግም፡፡
በመተካካት ‹‹የተስፋ›› መሰላሉ ላይ ይወጡ ዘንድ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጀምሮ በአባልነት እያሰለፈ ያለው ገዢው ፓርቲ የመንግስታዊ ሚናውን ተጠቅሞ የተሻለ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ‹የእኔ ናቸው› በሚል ፈሊጥ አገሪቷ ለሚቀጥሉት 40 ዓመታት ‹‹ያለምንም ችግር›› በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎዳና እንደምትጓዝ በእርግጠኝነት ይናገራል፡፡ ስልጣን በአንድ አገር መዋቅር ውስጥ የሚገኝ የመዋቅሩ አስተዳደራዊ አካል አንድ ቅርጽ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን መሰረታዊ ስርዓቶችን አስተካክሎ፣ ያለፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት ለሁሉም ወጣቶች ‹‹አገራዊ ቦታ›› የማይሰጥ ስርዓት በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን የጠፋውን የአገር ባለቤትነት ስሜት መፍጠር ይሣነዋል፡፡ የሁሉም የሆነ ስርዓት መፍጠር ደግሞ የአገር ባለቤትነት ጥያቄን ከስልጣን ባለቤትነት ጥያቄ ለይቶ ማየት ይጠይቃል፡፡ የአገር ባለቤት መሆን የስልጣን ባለቤት መሆን ብቻ አይደለምና! ይህንን ለመፍጠር ያልቻለ ባለስልጣን፣ ትውልድ እና የአገር መሪ የአገሪቷ ባለቤትነት ስሜት ላጡ ወጣቶች መፈጠር መውቀስም ሆነ መፋዘዝን ለመተቸት የሞራል የበላይነትን እንደሚያጣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የእኛ (የወጣቶች) ተግዳሮቶች
ይሄ ትውልድ አንድን ትውልድ በአንፃራዊ መልኩ በተሻለ ሁኔታ የሚገነቡ መሰረታዊ ግብአቶችን ያጣ ትውልድ ነው፡፡ ጠንካራ እና አቅምን የሚገነባ፣ ንባብን እና ማወቅን የሚያበረታታ ስርዓተ-ትምህርት የተነፈገው፣ ዓለም ወደፊት በምትገሰግስበት በዚህ ፈጣን ዘመን የሚያወራበት፣ የሚነጋገርበት ‹‹ቦታ›› ያጣ፣ መረጃ የሚሰጡ፣ ዕውቀትን የሚያጎለብቱ፣ የሚሰጡና የሚናገሩለት የሚዲያ ተቋማት የሌሉት (በስህተት ቢያገኝ እንኳን በቀላሉ የሚነጥቁት)፣ ዘመኑና አካባቢው ያልተገጣጠሙለት ትውልድ ነው፡፡
አንድን ትውልድ ለመቅረጽ ወሳኝ ተፅዕኖ ያላቸው ሚዲያ፣ ስርዓተ-ትምህርት፣ ስነጥበብ እና ወዘተ በዚህ ዘመን ‹‹ባዶ›› በሆኑበት ሁኔታ ታግለው ‹‹የይገባኛልን ስሜት›› ወደራሳቸው የሚያመጡ፣ የተነጠቁትን (ያልተሰጣቸውን) አገራዊነት የሚፈልጉ ለዚህም የሚተጋገዙ ወጣቶች ያስፈልጉናል፡፡ በከፍተኛ የወጣት ምሁራን ፍልሰት የምትጠቃው ኢትዮጵያ፣ በድንዛዜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶቿን ለማዳን ወጣቶቿን መጠቀም ይኖርባታል፡፡ ጩኸቱን (ብሶቱን) የሚሰማው ያጣው ትውልድ እርስበርሱ መነጋገር መጀመር ይኖርበታል፡፡
ዞን ዘጠኝ፤ እንደ አንድ መፍትሄ
ዞን ዘጠኝ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የመነጋገሪያ (public discoursing) ዞን ነው፡፡ የዞን ዘጠኝ አባላት ከላይ በተነሱት ሐሳቦች ላይ ተመስርተን መነጋገር ባለመቻል፣ ሐሳብን በነፃነት ለመግለፅ ዕድልና ምቹ መድረክ በማጣት ወደዳር የተገፋውን ወጣት በጋራ መወያያ መድረክ ወደመሃል ማምጣት ይቻላል ብለን በማመን ይህንን ጦማር ከፍተናል፡፡ ለዚህም ራሳችን ወደመሃል መጥተን እና ሐሳብ ሰጥተን፣ ሐሳብ ተቀብለን የጋራ የመወያያ መድረክ እንዲፈጠር የቻልነውን አስተዋፅዖ እናደርጋለን፤ ለዚህ ዓላማ ግብ መምታትም ይህንን ፅሁፍ አሃዱ ብለን አቅርበናል፡፡
ሕዝባዊ ውይይት ለተሻለች ኢትዮጵያ፤ እንኳን ወደዞን ዘጠኝ በደህና መጡ!!!
Source: Zone 9
No comments:
Post a Comment