ኢሳት ዜና (ሰኔ 12 2007)
ባለፈው ወር በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ለገዢው ኢሃዴግ ድምጽ አልሰጣችሁም የተባሉ የለገጣፎ ከተማ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸው ህገ-ወጥ ግንባታ ነው በሚል እየፈረሰባቸው መሆኑን ገለጡ።
በከተማዋ አባኪሮስ እና ገዋሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኙት ነዋሪዎች ኢሃዴግን አልመረጣችሁም የመረጣችሁት ተቃዋሚዎችን ነው በመባል መኖሪያ ቤታቸው መፍረሱን ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የምርጫው ሂደት መጠናቀቅን ተከትሎ ቤታቸው ቀይ ቀለም ሲቀባ መሰንበቱን የተናገሩት ነዋሪዎች በምርጫው ውጤት ቅር የተሰኙ ባለስልጣናት እርምጃውን መውሰድ እንደጀመሩ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ቤታችሁን እናፈርሳለን የሚል ዛቻ ሲቀርብባቸው መቆየቱን ያወሱት የአባ ኪሮስ እና ገዋሳ አካባቢ ነዋሪዎች ድርጊቱን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ከእነ ልጆቻቸው ጎዳና ላይ ወድቀው እንደሚገኙ መግለጻቸውን በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ሁኔታውን በፎቶ በማስደገፍ አቅርበዋል።
ግንቦት 16/2007 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ለገጣፎ አካባቢ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል አለመግባባት ተፈጠሮ እንደነበርም ታውቋል።
የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ ገዢው የኢሃዴግ መንግስት በተለያዩ አካላት ላይ የሚወሰደወን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ አንድ የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ እና የፖለቲካ ድርጅት አባል መገደላቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment