Saturday, June 13, 2015

ሕወሃት አይኑን በጨው አጥቦ፣ ራሱ መራጭ፣ ራሱ ተመራጭ፣ ራሱ ታዛቢ፣ ራሱ ምርጫ ቦርድ (ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበራት የተሠጠ መግለጫ)


udj
አንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር
ANDENET NORTH AMERICA ASSOCIATION OF SUPPORT ORGANIZATION
8121 Georgia Avenue, Silver Spring, MD 20910 ste 10, Tell: (301) 585-7700
ሰኔ ፲, 2007 ዓ/ም (June 12, 2015)
የደርግ ስርዓት ሲገረሰስ ሕወሃት/ኢሕአዴግ የዲሞክራሲ ስርዓት እንደሚገነባ ቃል ገብቶ ነበር። ሆኖም፣ ይኸው ሃያ አራት አመታት አለፈ፤ ኢትዮጵያዉያን የግፍ ቀንበር በላያቸው ላይ ተጭኖ፣ መብታቸዉንና ነጻነታቸውን ተገፈው፣ በአገራቸው በፍርሃትና በሰቀቀን እየኖሩ ነው። ምንም እንኳን እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ የስርአቱ ተጠቃሚዎች ቢከብሩም፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የኑሮ ዉድነት፣ ዜጎችን ከቅያቸው የማፈናቀል ተግባራት፣ አድልዎና ዘረኝነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያን ለብዙዎች ሲኦል እያደረጋት ነው።
ምርጫ ዜጎች ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚረዳ እንደመሆኑ አገር ቤት ያሉ የሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ምርጫውን ተጠቅመው ለዉጥ ለማምጣት በርካታ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ሆኖም አገዛዙ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ከፍተኛ ጫና እያደረገ አላሰራ እንዳላቸው የአደባባይ ሚስጠር ነው። ጫና ከማሳደር ባለፈም፣ የሚዘረጋበትን መሰናክል በማለፍ፣ ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር የዘረጋዉንና በሕዝቡ ዘንድ በሁሉም ክልሎች ተቀባይነት ያገኘውን የአንድነት ፓርቲ፣ አገዛዙ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ እስከማገድም ደርሷል። ብቸኛ ተቀናቃኝ የሆነዉን እና ምርጫውን ሊያሸንፍ የሚችል ድርጅት በታገደበት ሁኔታ የተደረገ ምርጫ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በምርጫው ወቅትም፣ ምርጫ ሳይሆን የድምጽ ዘረፋ በይፋ እንደደተደረገ፣ የምርጫ ጣቢያዎች የጦርነት ቀጠና ይመስሉ እንደነበረ፣ ኮረጆዎች እንደተገለበጡ በስፋት ተዘግቧል። ምርጫዉን የአዉሮፓ ሕብረትም ሆነ የካርተር ማእከል ያልታዘቡት ሲሆን፣ የአሜሪካን ኤምባሲም የምርጫውን ሂደት ለመከታተል ሰራተኞች ለመላክ ቢጠይቅም ፍቃድ አላገኝም። በብዙ ቦታዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች አልተገኙም። በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የታዘበው፣ የአገዛዙ አጋር ተደረጎ የሚቆጠረው የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ ምርጫው ሰላማዊ ነበር ቢሉም፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።
ሕወሃት አይኑን በጨው አጥቦ፣ ራሱ መራጭ፣ ራሱ ተመራጭ፣ ራሱ ታዛቢ፣ ራሱ ምርጫ ቦርድ ፣ ራሱ ፖሊስ፣ ራሱ ዳኛ ሆኖ ባደረገው የምርጫ ድራማ፣ መቶ በምቶ አሸነፍኩም ብሎ አውጇል። የሕወሃት ቅርንጫፍ የሆኑት የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎችም የምርጫው ዉጤት አለመቀበል በሕግ እንደሚያስቀጣ በመግለጽ እያስጠነቀቁ ነው።ሆኖም፣ የብዙ ድርጅቶች ግንባር የሆነው መድረክ፣ ኢዴፓ፣ ሰማያዊ፣ መኢአድ እና ኢራፓ ምርጫውን እንደማይቀበሉ በይፋ አሳወቀዋል።
አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች፣ በምርጫውው ሂደት ላበረከቱት አስተዋጾና ለከፈሉትን መስዋትነት ያለንን አክብሮት እየገለጽን፣ ምርጫውን እንደማይቀበሉ በመግልጽ የወሰዱትን አቋም እንደምንደገፍ ለመገልጽ እንወዳለን። እኛም ከዚህ ምርጫ የሚገኝ ምንም አይነት ሕጋዊነት እንደሌለ በማስረገጥ፣ ሕወሃት ያለ ህዝብ ፍቃድ በጉልበት የሚገዛ ግፈኛ አገዛዝ እንደመሆኑ የምንታገለው መሆናችንን እናረጋግጣለን።
አለም የትናይት በደረሰበችበት፣ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩና እኛ ስንረዳቸው የነበሩ እንደ ጋናና ናይጄሪያ ያሉ አገራት የዲሞክራሲና የነጻነት አየር እየተነፈሱ ባለበት ዘመን፣ ሕወሃት መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ ማወጁ፣ ምን ያህል ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ንቀት እንዳለው በግልጽ ያመላከተ ሲሆን፣ ይሄን ሕዝብን የሚንቅ አገዛዝ የመሸከም ትከሻ ማንም ኢትዮጵያ ሊኖረው አይገባም ብለን እናምናለን።በመሆኑም ለዉጥ እንዲመጣ የለዉጥ እንቅስቃሴን ለማገዝ ማድርረግ ያለብንን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለን ልናረጋግጥ እንወዳለን።
አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች፣ ትግሉ የርዮት አለም ሳይሆን የነጻነት መሆኑን ተረድተው፣ ኃይላቸውን በማስተባበር በጋራ እንዲንቀሳቀሱም በአጽንኦት እናሳስባለን። ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ያላቸው ወደ ዉህደት፣ ካልሆነም ደግሞ መስማማት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንባር በመፍጠር፣ መግለጫ ከማውጣትና ብሶት ከማውራት አልፎ በመሄድ፣ ስርአቱን የሚያስጨንቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ማድረግ እንዲሸጋገሩ እየጠየቀን፣ በማንኛው ጊዜ በጋራ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊ አጋርነታንን እንደማይለያቸው ቃል እናሳውቃለን።
ድል ለኢትዬጵያ ሕዝብ!
የአንድነት ድጋፍ ማህበሮች በሰሜን አሜሪካ አስተባባሪ ኮሚቴ
Source: Zehabesha

No comments: