Friday, June 12, 2015

በኢትዮ ሶማሊያ ድንበር የሚካሄደው ግጭት አለመብረዱ ታወቀ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 4 2007 ዓም)
ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ ሲካሄድ የቆየውን ግጭት ተከትሎ የሶማሊያ መንግስትን የሚቃወም ታጣቂ ቡድን አካባቢውን መቆጣጠሩ ተገለጠ።
ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኘውና ሰሞኑን ግጭቶች ሲካሄድ የቆዩበት የጋልጋዱድ ግዛት ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ በሚደረግላቸው የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ስር ቆይቶ እንደነበረ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል ።
ለሁለት ሳምንት ያህል በኢትዮጵያ ልዩ ሀይሎችና የሶማሊያ ጎሳ ታጣቂዎች ሲካሄድ የቆየውን ግጭት ተከትሎም አህሉ ሱናህ ዋልጀማ የተሰኘ ታጣቂ ቡድን አካባቢውን እንደተቆጣጠረው የሶማሊያ መገናኛ ብዙሀን ረቡእ እለት ዘግበዋል ።
ከሰባት አመት በፊት ጀምሮ የትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኘው ይኸው ታጣቂ ሀይል፣ በኢትዮጵያ መንግስትና በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ የተሰጠውን የሶማሊያ መንግስት እንደሚቃወም ቡድን ይገልጻል።
በስልጣን ላይ ያለው እና ከአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ተጋርጦበት የሚገኘው የሶማሊያ መንግስት የጋልጋዱድን ግዛት በክልል የፌደራል መንግስት ለማስተዳደር ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት አህሉ ሱናህ ግዛቲቱን መቆጣጠር እንደቻለ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ከሶማሊያ የጎሳ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ቆይተው የነበሩት የኢትዮጵያ ልዩ ሀይሎችም አሁንም በአካባቢው ሰፍረው እንደሚገኙና ውጥረቱ አለመርገቡን ነዋሪዎች ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የተካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የጦር ሰራዊቱን ወደ ሶማሊያ ድንበር ማስጠጋቱ የድንበሩ ግጭት እንዲባባስ ማድረጉን የሶማሊያ ባለስልጣናት የገለጹ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያም ምክክር እየተካሄደ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።
በግጭቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በርካቶች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ የሶማሊያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሀገሪቱ ባለስልጣናት በአካባቢው በልዩ ሀይሎች ተፈጽሟል ያሉትን የዘር ማጥፋት ድርጊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምርመራ እንዲካሄድበት ጥሪ ማቅረባቸውን ሆርሴድ የተሰኘ የሶማሊያ ጋዜጣ ዘግቧል ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር ዙሪያ የተቀሰቀሰውን ግጭት ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የጸጥታ ሀይል በአካባቢው አስፍራ እንደሚገኝ ተነግሯል።

No comments: