(ነፍስ ይማር ~ Rest In Peace/R.I.P)
በአካል ባላውቀውም በሚያደርጋቸው የሃገር ትግል ፅኑ አቋም ይዘው ከሚጓዙት ወጣት ፖለቲከኞች ውስጥ አንዱ ነበር ሳሙኤል አወቀ አለም። በአካል ባላውቀውም እንቅስቃሴውን እከታተል ስለነበር አውቀው ነበር። ይህ ወጣት በቅርቡ በተካሄደው የ2007 ብሄራዊ ምርጫ ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደረ እጩ ተወዳዳሪ ነበር። በምርጫው ወቅት በወያኔ ደህንነቶችና ካድሬዎች ድብደባ ተፈጽሞበታል። ሆኖም ለሃገሩ ካለው ጽኑ ፍቅርና የጠራ አቋም ከእምነቱ ሊያፈገፍግ አላስቻለውም። በዚህ የተበሳጩ የወያኔ ጀሌዎች በተለይ ደህንነቶቹ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርሱበት ነበር። በመጨረሻም ቤቱ ሲገባ ቀጥቅጠው ገደሉት።
ይህ እንደሚመጣበት ያውቅ የነበረው ወጣት ሳሙኤል አወቀ አለም የሚከተለውን መልዕክት በፌስቡክ ገፁ ለህዝብ አሳውቆ ነበር።
"ውድ የደብረማርቆስ ከተማ ኗሪዎች፤ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ 25,000 በላይ መራጮች(ኮረጆውን) እርሱት እና በተጨማሪም በ31 ዩኒቨርስቲ ምትገኙ 14,000 በላይ ሰማያዊ ፓርቲ የመረጣችሁ ሌሎች ደጋፊዎች እና የኢሕአዴግ አባላትም የማያፍረው ብአዴን/ኢህአዴግ ድምፅ መቀማቱ ሳያንስ በ21/08/2007 ዓ.ም አፍነው ደብድበው ከሞት መትረፌ ቆጭቷቸው እስር ቤት ለመወርወር ያለመከሰስ መብቴን እንኳን ተዳፍረው የሃሰት ክስ እየፈጠሩ ነው!!!! በስልኬም እንደተደወለም ያለ ፍላጎቴ ደህንነት እያሳደደኝ ይገኛል!!!! ተገደልሁም ታሰርሁም ነፃነት አይቀርም እና ለማስረጃነት የደህንነቶችን ስም፣ ፎቶግራፍ፣ እና አድራሻ እንዲሁም በሃሰት ምስክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አስመዘግባለሁ ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለሃገሬ እና ለነፃነት ነው። ከታሰርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ!!!! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን ዘላለማዊ ነው!!!! (ከሳሙኤል አወቀ አለም ~ የሰማያዊ ፓርቲ የደብረማርቆስ የሕዝብ ተወካዮች እጩ ተወዳዳሪ)"
ምንም ወንጀል ሳይሰራ የታሰረ ሰው በአካል ቢታሰርም አላማውና አቋሙ አንድ ነውና ህሊናው ግን አይታሰርም። ይህ ያውቅ የነበረው የልጅ አዋቂው ሳሙኤል ብታሰርም ህሊናዬ አይታሰርም ብሎ ነበር። ነገር ግን ይደርስበት የነበረው ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም በምርጫው ሰሞን የተፈፀመበት ከፍተኛ የሆነው ድብደባ የተገነዘበው ሳሙኤል ከመግደል ወደ ኋላ እንደማይሉ በመገንዘብ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ ብሎ ነበር። እኔ አደራህን ዳር ለማድረስ ከመቼውም በላይ ጠንክሬ ለመስራት ቃል እየገባሁ ፈጣሪ ነፍስ በገነት እንዲያኖራት ፀሎቴ ነው።
ታጋይ ይገደላል ትግል ግን መግደል አይቻልም። የወያኔ ካድሬዎችም ሆኑ ደህንነቶች ሳሙኤልን ቢገድሉም ትግሉን ቢያጠነክሩት እንጂ መግደል አደለም አያቀጭጩትም። በዲሞክራሲ ስም እየነገደ በሰላማዊ መንገድ የሚታገለውን እያደነ የሚገለውን የወያኔ አንባገነን ስርዓት ማስወገድ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው። አምርሮ መታገል ግድ ይላል!።
ሳሙኤል ~ ነፍስ ፈጣሪ በገነት ያኑራት!
No comments:
Post a Comment