Sunday, September 1, 2013

ሙስሊም ወገኖች ሆይ!


ሙስሊም ወገኖች ሆይ!

ላለፈው አንድ አመት ተኩል ያደረጋችሁት ሰላማዊ እንቅስቃሴ በተለያየ እምነት ያለነውን ሁሉ አኩርቶናል:: ወያኔ ዛሬ ህዝብ 

በነቂስ ወጥቶ እንዲያወግዛችሁ ፈልጎ የነበረው እናንተን ለመምታት ለሚወስደው እርምጃ ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚያስችል 

ድጋፍ ፈልጎ ነው እንጂ የት አገር ነው መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍ አደራጅቶ ሽብርተኝነትን አውግዙልኝ የሚለው? ሰማያዊ 

ፓርቲን አግቶ በጠራው ሰልፍ ላይ የፈለገውን ድል እንዳያገኝ ሆ ብላችሁ ወጥታችሁ ስላደናቀፋችሁበት ቂም እንደተያዘባችሁ 

አትዘንጉ:: 

ወያኔ ሥልጣን ላይ ከመጣበት ዕለት ጀምሮ የሃይማኖት ተቋሞች የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው አስፈጻሚ አካላት መካከል አንዱ 

ሆነው ቆይተዋል:: ጳጳስ በህይወት እያለ ሌላ ጳጳስ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመሾም እስከዛሬ ያልበረደ ክፍፍል 

በተከታዮቹ መካከል መፍጠሩን ታውቃላችሁ:: ውሎ ይደር እንጂ በእናንተንም ላይ የተወሰደው የመከፋፈል እርምጃ ቀደም 

ብሎ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከተወሰደው የሚለይ አልሆነም:: ልብ ባንለው ነው እንጂ እየተደረገብን ያለው መከፋፈል 

ያለምክንያት አይደለም:: በዘርና በቋንቋ አልከፋፈል ያለን ህዝብ ለመለያየት ከሃይማኖት የተለየ ምን ሊመጣ ? ::

በመሠረቱ "መንግሥት በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ አይግባ" የሚል ጥያቄ ከመብቶች ጥያቄ አንዱ ቢሆንም በሃይማኖት ጉዳይ 

ጣልቃ የማይገባ መንግሥት የዜጎቹን መብት ለማክበር ግዴታ ያለበት መንግሥት ብቻ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም :: 

የዚህ አይነቱ መንግሥት ቀድሞውኑም ወደ መንግሥት ሥልጣን የሚመጣው በህዝብ ድምጽ ስለሆነ ወደሥልጣን ያመጣውን 

ህዝብ መብት ረግጦ አንድም ቀን ሥልጣን ላይ መቆየት አይችልምና በተዘናጋባቸው ጉዳዮች ህዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ያቀረበው 

ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለማግኘት ጊዜ አይወስድበትም:: ምክንያት የህዝብ ጥያቄ የማይመልስ መንግሥት በቀጣዩ ምርጫ እዚያች 

ስልጣን ቦታ ድርሽ እንደማይል ስለሚያውቅ:: በኛ አገር እየሆነ ያለው ተቃራኒ ነገር ነው:: 

በጠመንጃ ሃይል ሥልጣን መቆናጠጡን ሊዘነጋ ያልቻለን ቡድን እርሱ ራሱ ለፈረንጆች ፍጆታ ሲል በየ5 አመቱ በሚያዘጋጀው 

የምርጫ ቲያትር ላይ ተገደን ስለተሳተፍን ብቻ የሥልጣን መሠረቱ የህዝብ ድምጽ በሆነበት አገር እንደሚሆነው "ድምጻችን 

ይሰማ " ብለን በመጮህ ለውጥ የምናመጣ እየመሰለን መጥቶአል::
ላላፈው አንድ አመት ተኩል እያነሳነው ያለነው " መንግሥት በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ አይግባ" ጥያቄ የሃይማኖት 

(የእምነት) ነጻነት ጥያቄ አካል ነው:: የሃይማኖት ነጻነት ደግሞ ዜጎች በአገራቸው በህግ ሊከበርላቸው ከሚገባቸው መብቶች 

አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም:: ለምሳለ የዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብት ፤ የመጻፍ፤ የመሰብሰብ ፤ የመደራጀት፤ 

ተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ የመሳሰሉት መብቶች ሳይከበሩ የሃይማኖት ነጻነት ተነጥሎ ሊከበር እንደማይችል እየገጠመን ካለው 

ችግር መረዳት ይቻላል::
የመንግሥትን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት እርምጃ ለማስቆም የተቃውሞ ድምጻቸውን በአደባባይ ያሰሙና ሠላማዊ 

ሠልፍ ያስተባበሩ ወንድሞቻችን ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ ያደረጉት ሙከራ እንደወንጀል ተቆጥሮባቸው ከርቼሌ 

ከተወረወሩ ቦኋላ "ጀሃዳዊ አራካት" የሚል የፈጠራ ፊሊም ተቀነባብሮባቸው "ሽብርተኝነት" የሚል ታርጋ የተለጠፈላቸው ፡ 

የእምነት ነጻነት ሌሎች መሰረታዊ የፖለቲካ መብቶች ባልተከበሩበት ብቻውን ሊቆም ወይም ሊከበር አለመቻሉን አመልካች 

ነው:: ነጋ ጠባ እስኪሰለቸን ድረስ ስለ” ሽብርተኝነት” በመንግሥት ሚዲያዎች የሚላዘንብንም ህገመንግሥታዊ መብታችን 

የሆኑትን እነዚህን የማይነጣጠሉ መብቶቻችንን ለማፈን እንደሆነ አውቀናል:: "ድምጻችን ይሰማ" ብለው በቅርቡ በአርሲ 

አሳሳና በደሴ በወጡት ወገኖቻችን ላይ የተወሰደው ድብደባ ፤ግድያና እስራት በምርጫ 97 "በመረጥናቸው የህዝብ 

ተመራጮች እንመራ " ብለው ጥያቄ ባነሱት ዜጎቻችን ላይ ከተወሰደው ጭካኔያዊ እርማጃ የሚለይ አይደለም::

ስለዚህ ወያኔ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ጡንቻውን ተራ በተራ እያፈራረቀ አንድ ባንድ ከሚደፈጥጠን ጥያቄያችንና 

ዋንኛው የመታገያ መፈክራችን መሆን ያለበት በአገራችን የተሟላ የዜጎች መብት የሚያከብር መንግሥት በአስቸኳይ ቋቋም ! 

ነው:: ለዚህ ሁላችን በጋራ ከታገልን ክርስቲያን ፤ ሙስሊም፤ አይሁድ፤ ዋቄፋታ ፤ ወይም እምነት የሌለው ሁሉ አንድ ላይ 

አርነት ይወጣል :: ይህ ሲሆን እስከ ዛሬ የምንታወቅበት ችጋር፤ ኋላቀርነትና እፍትሃዊነት ተወግዶ በምትኩ ፍትህ፤ እኩልነትና 

ነጻነት የሰፈነበት የበለጸገችና የተከበረች አገር ይኖረናል::
አላህ አንድ ያርገን
ኢትዮጵያ አገራችንን ይጠብቅልን

No comments: