Monday, September 16, 2013

734 ሚሊዮን 600 ሺ ብር የመዘብሩ የስራ ሃፊዎች አለመቀጣታቸውን መረጃዎች አመለከቱ

734 ሚሊዮን 600 ሺ ብር የመዘብሩ የስራ ሃፊዎች አለመቀጣታቸውን መረጃዎች አመለከቱ

1111111111111
መስከረም ፮(ስድት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አዲስ ከስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሺን የተገኝው መረጃ እንደሚያመለክተው ከተለያዩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች 734 ሚሊዮን 6 መቶ ሺ ብር የመዘብሩ የስራ ሃፊዎች በተጣራ መረጃ ክስ ቢመሰረትባቸውም የውሳኔ ቅጣት እንዳልተላለፈባቸው ታውቋል።
ለረጅም ጊዜ በተደረገ ምርመራ ተጣርቶና መስረጃ ተገኝቶባቸው ከ2004 ዓም ጀምሮ ክስ የተመሰረተባቸው የተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የውሳኔ ሀሳብ እንዳልተላለፈባቸው ከመሰሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ላይ 94 ሚሊዮን 300 ሺ ብር ከትምህርት ተቋማት ግንባታ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ የሙስና ወንጀል ምርመራ ተጠናቆ ክስ ቢመሰረትም በቂ ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቷል።
ከአራዳ ክ/ከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ህገወጥ የካሳ ክፍያ በመፈጸሙ ሦስት የምርመራ መዝገቦች ተጠናቀው በ2004 ዓ.ም ክስ ቢመሰረትም የቅጣት ውሳኔ አላገኝም።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀራጅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የ12 ሚሊዮን ብር እና የ34 ሚሊዮን ብር ህገወጥ ብድርን እንዲፈፀም ያደረጉ አካላት በቂ የሰነድ ማስረጃ እንደተገኘባቸው ቢገለጽም እርምጃ ሳይወሰድ ቀርቱዋል፡፡
በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ከመመሪያና አሰራር ውጪ ለግለሰቦች የስልክ መስመር እንዲዘረጋ በማድረግ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ስልክ በማስደወል በመስሪያ ቤቱ ላይ 14 ሚሊዮን ብር ጉዳት መድረሱን የተመለከተ ሁለት ምርመራዎች ተጠናቀው በክስ ሂደት ላይ ሲሆኑ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በሚፈጥሩት ጫና ክሱ እየተጓተተ ነው።
በትግራይ ክልል የሚገኘው በሼባ የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ለፋብሪካው የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ቆጣሪ መሳሪያ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በማድረግ መብራት ሀይል ከሽያጭ ማግኘት ይገባው የነበረውን ገቢ በማስቀረት በአገር ላይ 65 ሚሊዮን 300 ሺ ጉዳት በመድረሱ ምርመራው ተጣርቶ ለወሳኝ አካል ቢተላለፍም ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቷል።
በተመሳሳይ በኦሮምያ ክልል በደብረዘይት የሚገኝ የግል የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ለፋብሪካው የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ቆጣሪ መሳሪያ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከሽያጭ ማግኘት ይገባው የነበረውን ገቢ በማስቀረት በአገር ላይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረሱ ምርመራው አጣርቶ የፀረ ሙስና ኮሚሺን ቢልክም የፍትህ መጓተት ታይቶበታል።
በመብራት ሀይል አላግባብ በ 248 ሚሊዮን 900 ሺ ብር የተፈጸመ የ4 ሺ4 መቶ 70 ትራንስፎርመሮች አለም አቀፍ ግዢ በሁለት የምርመራ መዝገቦች የተጣራ ቢሆንም ውሳኔ አልተሰጠበትም።
ንብረቱ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ የሆነ ግምቱ 4 ሚሊዮን 7 መቶ ሺ የሆነ የብርና የነሃስ ሜዳልያ ከግምጃ ቤት በመጥፋቱ ተመርምሮ የተረጋገጠ ቢሆንም ውሳኔ አላገኘም።
በተንዳሆ ፕሮጀክት ከግብር ጋር በተያያዘ በመንግስት ላይ ጉዳት በመድረሱ ምርመራው ተጠናቆ ክስ ተመስርቷል። በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ በሊዝ እንዲስተናገድ የተወሰነለትን የመኖሪያ ቤት ኅ/ሥ/ማ ያለ ሊዝ በማስተናገድ የተሰጠ 30 ሺ 3 መቶ 32 ካ/ሜ ቦታ ምርመራ ተጠናቆ ክስ የተመሰረተ ቢሆንም ውሳኔ አላገኘም።
ለብሄራዊ ባንክ በሽያጭ ከሚቀርብ ወርቅ ጋር በተያያዘ የባንኩ ሰራተኞችና ነጋዴዎች በመመሳጠር 63 ሚሊዮን ብር በመመዝበር አስቀድሞ ተከሰው የነበሩ አሁን ጥፋተኛ ተብለው ጉዳዩ ለቅጣት ውሳኔ ተቀጥሯል።
በቂርቆስ ክ/ከተማ በልማት ተነሺዎች ስም ከመመሪያ ውጪ ግምቱ 13 ሚሊዮን 3 መቶ ሺ የሆነ 2, ሺ 1 መቶ 45 ካ/ሜትር ትርፍ መሬት አላግባብ በተሰጣቸው እና ከካሳ ክፍያም ጋር በተያያዘ 5 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ብር በትርፍ የተከፈላቸው ግለሰቦች ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሀዋሳ ቅርንጫፍ በእምነት ማጉደል ወንጀል ግምቱ ብር 1 ሚሊዮን 7 መቶ ሺ የሆነ መድሃኒት ተመዝብሮ ለግል ጥቅም መዋሉ እና በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በተደረገ የ100 ሚሊዮን የእህል ግዢ ጨረታ ግለሰቦች ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ጨረታውን ያሸነፉ መሆኑ በተደረገው ምርመራ በመረጋገጡ ጨረታው እንዲሰረዝና በግለሰቦቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት የተደረገባቸው በጥቅሉ ከህዝብ በግብር የተሰበሰበ በርካታ ገንዘብ በአንድም በሌላ መልኩ በከፍተኛ አመራሮች ተጽእኖ በ2004 እና በ2005 ዓ.ም ተጣርቶ ለፍርድ ሰጭው አካል ቢተላለፍም ውሳኔ ሳይሰጥባቸው ቀርተዋል፡፡
ከ 7 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የመዘበሩ የስራ ሃፊዎች አልተቀጡም ሲል ከፀረ ሙስና ኮሚሺን የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ አሀዙ በ2005 የተፈጸመውን ሙስና አላካተተም።
ባለፉት 22 የኢህአዴግ የአገዛዝ አመታት የተፈጸሙና በጸረ ሙስና ኮሚሽን ያልተጣራ በሙስና የተዘረፈ ገንዘብ በቢሊዮኖች እንደሚቆጠር ይገመታል።

No comments: